1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጋዜጠኛ ዳዊት ኢስኃቅ በህይወት ይገኛል መባሉ

ዓርብ፣ ጥር 23 2006

ትውልደ ኤርትራዊው የስዊድን ዜጋ፣ ጋዜጠኛ ዳዊት ኢስኃቅ ድንገት ተይዞ ወዳልታወቀ ስፍራ የተወረወረው የዛሬ 13 ዓመት ገደማ ነበር እጎኣ መስከረም 23 ቀን 2001 ዓ ም። ከሚኖርበት ስዊድን ወደ እናት አገሩ ኤርትራ ተመልሶ ኣሁንም እጎኣ በ 1997 ዓም መሆኑ ነው፣ ሰቲት የተባለ ነጻ የግል ጋዜጣ ማዘጋጀት የጀመረው ዳዊት ኢስኃቅ የተወነጀለው

https://p.dw.com/p/1B0BZ
Dawit Isaak

በመንግስት ላይ ተገቢ ያልሆነ ትችት ኣስነብበኃል በሚል ሲሆን ከ 9 ዓመታት በኃላ በ2010 ዓ ም ነበር ለመጨረሻ ጊዜ የታየው። ከዚያ በፊትም ሆነ ከዚያ ወዲህ የት እንደሚገኝ ብቻም ሳይሆን በህይወት መኖሩም ኣይታወቅም ነበር።

በእስራኤል ኣገር የኤርትራ ኣምባሳደር የሆኑት ተስፋማሪያም ተከስተ ደባስ በዚህ ሳምንት ለጋዜጠኞች እንደነገሩት ከሆነ ግን ጋዜጠኛ ዳዊት ኢስኃቅ በህይወት መኖሩ ታውቐል። የኤርትራ እና የስዊድን ጣምራ ዜግነት የያዘው ጋዜጠኛ ዳዊት ኢስኃቅ አምባሳደሩ እንደሚሉት የኣገሪቱን ህግ በመተላለፍ ነው እየተቀጣ ያለው። የት እና በምን ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ ግን አምባሳደር ተስፋማሪያም ያሉት ነገር የለም።

የዳዊት ኢስኃቅም ሆነ የሌሎች በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞችን ሁኔታ ለማወቅ መቀመጫውን ፓሪስ ያደረገው ድንበር የለሽ ዘጋቢዎች የተሰኘው የጋዜጠኞች መብት ተንከባካቢ ድርጅትም ተደጋጋሚ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። ሚስ ክሊኣ ካን የድርጅቱ የኣፍሪካ ክፍል ኃላፍ ናቸው።

«የዳዊት ኢሳቅን ጉዳይ በተመለከተ እንደሚታወቀው በመስከረም ወር 2001 ዓ ም የኤርትራ መንግስት ጋዜጠኞችን በጅምላ የማሰር ጭፍን እርምጃ በወሰደበት ወቅት ነበር ከሌሎች 11 ጋዜጠኞች ጋር የታሰረው። እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስም ይኸው እንደታሰሩ ነው።»

Unruheviertel Bagnolet in Paris
ምስል picture-alliance/dpa

እነዚህ ጋዜጠኞች ዓለም ዓቀፍ ተቐማትን ጨምሮ ቤተሰቦቻቸው እና የህግ አማካሪዎቻቸው እንዳይጎበኙኣቸው ተከልክሏል። ዓለም ዓቀፍ ህግጋትንም ሆነ የኣገሪቱን ህግ ተላልፏል ከማለት ያለፈ ሚስ ካን እንደሚሉት የተመሰረተባቸው ክስም የለም።

«አምባሳደሩ የኤርትራን ህግ በመተላለፋቸው ነው የታሰሩት ይሉናል። በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ታዲያ የኤርትራ መንግስት እራሱ «እስረኞች በህግ ፊት ፍትህ የማግኘት እድል ይኖራቸዋል» የሚለውን የራሱን ህግ እያከበረ ኣለመሆኑን ነው የተረዳነው።»

ጋዜጠኛ ዳዊት ኢስኃቅ በህይወት መኖሩን ይጥቀሱ እንጂ አምባሳደር ተስፋማሪያም እራሳቸውም ቢሆኑ የት እና በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ማወቃቸውንም እጠራጠራለሁ ያሉት የድንበር የለሽ ዘጋቢዎች የኣፍሪካ ክፍል ኃላፊዋ ሚስ ክሊኣ ካን እስከ ኤርትራ ጠ/ፍ/ቤት አቤቶታ ኣቅርበው ምላሽ በማጣታቸው ድርጅታቸው ለኣፍሪካ የሰብዓዊ እና የህዝብ መብቶች ኮሚሺንም አቤቶታ ማቅረቡን ኣውስቷል።

«ድንበር የለሽ ዘጋቢዎች ሶስት ጠበቆቹን ወደ ኣፍሪካ የሰብዓዊ እና የህዝብ መብቶች ኮሚሺን ፊት ቀርበው እንዲያመለክቱ ከማድረጉም በለይ ኤርትራ ፍትህ በመከልከሏ ተጠያቂ ትሆን ዘንድ ተጨማሪ የህዝብ ፊርማዎችንም ኣሰባስቦ ኣቅርቧል። ኤርትራ ግን በህዳር ወር 2013 በገኃድ ውድቅ ከማድረጉዋም በላይ እስከ ኣሁንም ድረስ የሰጠችው ምላሽ የለም።»

21.01.2013 Karte Eritrea Asmara deu

ሆኖም ግን ቀጣይነት ያለው ጥረት ከማድረግ ድርጅታቸው፤ ድንበር የለሽ ዘጋቢዎች እንደማይቆጠብ የኣፍሪካ ክፍል ኃላፊዋ ሚስ ክሊኣ ካን ኣረጋግጧል። ኤርትራ ለቀረቡላት ጥያቄዎች ምላሽ እንድትሰጥ እና በህገ ወጥ መንገድ የያዘቻቸውን ጋዜጠኞችም እንድትለቅ በዚሁ ኣጋጣሚ ጥሪ ኣድርገዋል።

በዚህ ዘገባ ላይ የኤርትራ ባለስልጣናትን ለማነጋገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት ግን ኣልተሳካም።

ኤርትራ በመስከረም ወር 2001 ዓም ይዛ ካሰረቻቸው 11 ጋዜጠኞች መካከል፤ ድንበር የለሽ ዘጋቢዎች እንደሚለው፤ ቢያንስ ሶስቱ በማጎሪያ ካምፑ ውስጥ ሳይሞቱ ኣልቀሩም። ኤርትራ 28 ጋዜጠኞችን በማሰር በ2013 በኣፍሪካ ትልቐ የጋዜጠኞች እስር ቤት ተብላ መፈረጇ የሚታወስ ሲሆን ካለፉት 7 ዓመታት ወዲህ ደግሞ፤ በድንበር የለሽ ዘጋቢዎች የደረጃ ሰንጠረዥ መሰረትም በዓለም የመጨረሻዋ መሆኗ ኣይዘነጋም።

ጃፈር ዓሊ

ሂሩት መለሰ