1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግብጽ እና ህዝባዊ አመፅ

ዓርብ፣ ጥር 20 2003

ዛሬም በቀጥለው የግብፅ ህዝባዊ አመፅ በፖሊስና በተቃዋሚዎች መካከል ግጭት ተፈጠረ።

https://p.dw.com/p/QwVQ
ምስል AP

ህዝቡን ለማገድ በብዛት የተሰማራው የግብፅ ወታደር ካይሮ እና አሌክሳንድሪያ ከተሞች አደባባይ የወጡ ተቃዋሚ ሰልፈኞችን በአስለቃሽ ጢስና በፕላስቲክ ጥይቶች ለመበተን ሞክሯል ። ፖሊስ ከአርብ የፀሎት ስርዓት ፣ በኃላ በህዝባዊ ሰልፍ ላይ ሊገኙ የተዘጋጁትን የኖቤል የሰላም ተሸላሚ መሀመድ ኤል ባራዳይንም ወደ ሰልፉ እንዳያቀኑ ከልክሏል ። በዛሬው ታላቅ የተቃውሞ ሰልፍ የሀገሪቱ ዋነኛ ተቃዋሚ ንቅናቄ «የሙስሊም ወንድማማቾች » ተካልፍለዋል ። ኤል ባራዳይ ለዚሁ ዓላማ ግብፅ መዲና ካይሮ በገቡበት በትናንትናው ዕለት እንደተናገሩት ወደ ሀገራቸው የሄዱት ሁሉም ነገር በሰላማዊ መንገድ መከናወኑን ለማረጋገጥና ሰለማዊ የተቃውሞ ሰልፎችን ለመሩት እና ላደራጁት ወጣቶች የፖለቲካ ፣ የመንፈስ እና የሞራል ድጋፍ ለመስጠት ነው ። አዲሲቷን ግብፅ ማየት እሻለሁ ያሉት ኤልባራዳይ በእስከዛሬዎቹ የትግል ስልቶች ውጤት ሊገኝ አለመቻሉንም ገልፀዋል ።

ግብፅ ውስጥ ከትናንት ምሽት አንስቶ በአጠቃላይ የቴሌኮሚኒኬሽን አገልግሎት ማለትም የኢንተርኔት እና የሞባይል ስልክ እንዲሁም የ SMS አገልግሎቶች ተቋርጠዋል ። ቁጥራቸው 20 የሚደርስ የሙስሊም ወንድማማቾች ንቅናቄ አባላት ትናንት ለሊት ከየቤታቸው ተወስደው ታስረዋል ። ከመካከላቸው 5 የቀድሞ የህዝብ ዕንደራሴዎች ይገኙበታል ። የቱኒዝያውን የጀስሚን አብዮት ተከትሎ በካይሮ ከሱዌዝ በአሌክሳንደሪያ እና በሌሎችም ከተሞች በተቀሰቀሰው የግብፁ ህዝባዊ አመፅ ሂዩመን ራይትስ ዎች እንደሚለው እስካሁን 8 ሰላማዊ ሰልፈኞችና አንድ ፖሊስ ተገድለዋል ። የግብፅ ህዝባዊ አመፅ በተቀጣጠለበት በዚህ ወቅት ላይ አሜሪካን አመፅ ለችግሩ መፍትሄ አይሆንም አይደለም ስትል አስጠንቅቃለች ። በሌላም በኩል የአሜሪካን ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ትናንት ባስተላለፉት መልዕክት የግብፁ ፕሬዝዳንት ሆስኒ ሙባረክ የፖለቲካ ተሀድሶዎችን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል ። መንግስት ም ሆነ ህዝቡ የየበኩላቸውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል ።