1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግብፅ-መሐል መንገድ ላይ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 8 2005

ሰኔ አጋማሽ።የግብፅ ሕዝብ ለመጨረሻዉ ዙር ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ካለፉት እጩዎች አንዱን ለመምረጥ ሁለት ቀን ሲቀረዉ፥-በሙባረክ የተሾሙ፥ የተሸለሙት የሐገሪቱ ሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ዳኞች በሞተ-ሥርዓታቸዉ ላይ እስትንፋስ ለመዝራት ሐያል-ጠንካራ ጥይታቸዉን ተኮሱ።

https://p.dw.com/p/1741L
A huge number of people went to vote on the referendum. 15.12.2012, Heliopolis Copyright: DW/A. Hamdy
የሕዝበ-ዉሳኔዉ ሰልፍምስል DW/A. Hamdy


የግብፅ ሕዝብ ባለፈዉ ሰኔ የመረጣቸዉን ፕሬዝዳንቱንና የፕሬዝዳንቱን የቀድሞ ፓርቲ በመደገፍና በመቃወም በየአደባባዩ እንደተሰለፈ፣ እንደተጋጨ እንደ ዲሞክራሲዉ ወግ፣ ለረቂ ሕገ መንግሥቱ ድምፁን ሰጠ።ቅዳሜ።የጥንታዊቱ ሥልጡን ሐገር ደፋር ሕዝብ አምባ ገነን ገዢዉን መቃወም ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ እርምጃዎችን በመቃወምና በመደገፍ ሲሰለፍ-ሲጋጭ፣ በሰልፍ-ግጭቱ መሐል ድምፁን ሲሰጥ ያሁኑ ስድሰተኛዉ ነዉ።ያሁኑ የተቃርኖ-ሰልፍ ግጭት ሰበብ-ምክንት፣ ሕዝብ የመረጣቸዉ መሪ-ፖለቲከኞች፣ ሕዝብ በድምፁ የሚያፀድቅ-የሚሽረዉ ረቂቅ ሕገ-መንግሥት መሆናቸዉ ነዉ ዚቁ።ረቂቅ ሕገ-መንግሥቱ ያስከተለዉ ልዩነቱ መነሻ፣ የግብፅ አብዮት ሒደት ማጣቀሻ፥ እድምታዉ መድረሽችን ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።


የመፀሐፍት፥ ጋዜጣ፥ መፅሔት መሸጫ መደብሮች፥ቋሚና ተንቀሳቃሽ ኪዮስኮች አዲስ በታተመዉ የረቅቂ ሕገ-መንግሥት ጥራዝ ተጨናንቀዋል።የካይሮ ጋዜጣ፥ መፅሔት እና የአነስተኛ ሸቀጥ አዟሪዎች አዲስ ገበያ አግኝተዋል።ዑም መሐመድ አንዷ ናቸዉ።

«ይሕ አዲሱ ሕገ-መንግሥት ነዉ።እንዴት ያምራል።በጉዳዩ ላይ ሥለሚደረገዉ ዉይይት ለማወቅ የሚፈልጉ ሰዎች ይገዙታል።ካነበቡት ጥሩዉንና ትክክለኛዉን ነገር ይረዳሉ።»

ጥራዙን የሚገዛ፥ የሚያነብ፥ ትክክለኛዉን ነገር ለመረዳት የሚፈልግ፥ የሚጥርም በርግጥ በሽ ነዉ።ጋዜጣ አዟሪዋ ያሉትን ባሉበት ሳምንት ረቂቁን ሕገ መንግሥት፥ አርቃቂ፥ደጋፊዎችን በመቃወምና በመደገፍ የካይሮ፥የአሌክሳንደሪያ፥ የጂዛ፥ የፖርት ሰኢድ አደባባዮችን ካጥለቀለዉ ሕዝብ አብዛኛዉ ግን ረቂቁን እንዲያነብ ፖለቲከኞች ጊዜ አልሰጡትም።የገለልተኛ ባለሙያዎችን ምክር አልሰማም።ወይም ለመስማት አልፈለገም።

በየሠልፍ-ግጭቱ መሐል ግን፥-

«ለረቂቁ የ«አዎ» ድምፅ መሰጠት አለበት» አሉ እሳቸዉ፥- «ሐገሪቱ በስተመጨረሻዉ የተሻለች እንድትሆን። መሐመድ ሙርሲይ ጥሩ ሰዉ ናቸዉ።እስልምና ምን ማለት እንደሆነ በትክክል ያዉቃሉ።ተቃዋሚዎቻቸዉ አሉባልታ ነዉ የሚነዙት።ማደናገር ነዉ-የሚፈልጉት።እኛ ግን ሙርሲ የሚሉት ጥሩ መሆኑን እናዉቃለን።»

ከግብፅ ሕዝብ አርባ-ዘጠኝ በመቶዉ ያንን የዚያን ረቂቅ ሕገ-መንግሥ ጥራዝ መግዛት ቢፈልግ፥ ቢችል፥ ቢገዛ እንኳን የረቂቁን ይዘት፥ ትርጓሜ፥ ገቢራዊነቱን ቀርቶ ጥሬ-ሐሳቡን እንኳን መረዳት አይችልም።ማንበብና መፀሐፍ አይችልምና።ግን ብዙ ነዉ።እናዉቃለን ባዮች ለየሚሹት ዓላማ በቀላሉ የሚያሰልፉት ትልቅ ሐይል።

ደይሊ ቴሌግራፍ የተሰኘዉ ጋዜጣ ዘጋቢ ያነጋገራቸዉ የኢማም አል-ሻፊያ መንደር ነዋሪ፥ «እኔ ማይም ነኝ አሉት-ባለፈዉ ቅዳሜ።ሥም ሌይላ ከዲራ።እድሜ ሰላሳዎቹን ያጋመሱ።ድምፅ ለመስጠት ተሰልፈዋል።ቀጠሉ ሴትዮዋ።«የምሰጠዉ ድምፅ ግን «አይ» የሚል ነዉ።«ምክንያቱም ረቂቁ ከፀደቀ፥ የሸቀጦች ዋጋ ካሁኑ የበለጠ ያሻቅባል።ሴቶች ከቤት መዉጣት አይፈቀድላቸዉም ሲሉ ሰምቻለሁ።ይሕን አልቀበልም።» አከሉ ለይላ።

እኝሕኛዋ የሚኖሩ-ድምፅ የሰጡበት፥ ወይዘሮ ለይላ ከሚኖሩ-ድምፅ ለመስጠት ከተሠለፉበት መንደር ራቅ፥ ፀዳ፥ ዘመን፣ መጠቅ ባለዉ የካይሮ መንደር ነዉ።በኑሮ-ዕዉቀት ከለይላ ብዙ የሚበልጡ፥ የራቁ-የመጠቁ፥ በእድሜ የበቁ፥ በፖለቲካዉ የነቁ-ናቸዉ።በትክክለኛዉ አገላለፅ የነቁ-ይመስላሉ።እንደ ወይዘሮ ለይላ ሁሉ ረቂቅ ሕገ-መንግሥቱን ይቃወማሉ።


«በዚሕ ሕገ-መንግሥት፥ እኛን ባስጠሊታ መንገድ አስገድደዉ፥ በጣም አክራሪ ወደሆነች ሐይማኖታዊት ሐገር ሊወስዱን ነዉ።ከኢራን የበለጠች አክራሪና አደገኛ ወደምትሆን ሐገር።»

እንዲሕ አይነቱ አስተያየት-ሰዉዬዉን አበሳጭቷቸዋል።ረቂቁ-ከሸሪዓ ሕግ-ጋር ምንድ ነዉ ግንኙነቱ።እኛ መናፍቃን ነበርን እንዴ? ጠየቁ-ቆጣ፥ ጮክ ብለዉ።

«ከሸሪዓ ጋር ምንድ ነዉ ግንኙነቱ? እስካሁን መናፍቃን ነበርን እንዴ?ምን ማለት ነዉ-ይኸ? እኛ ሁላችንም ሙስሊሞች ነን።»

ለሰዉዬዉ ጥያቄ ገለልተኛ መልስ ሰጪ ከተገኘ-መልሱ ትናንት መሰጠት እንደተጀመረዉ ሕዝበ-ዉሳኔ አይ-ወይም አዎ ነዉ-ሳይሁን ሁለቱንም መሆን ያለበት።የሕገ-መንግሥቱ አንዳድ አንቀፆች በተለይም አንቀፅ ሰወስት ሕጎች ከእስልምና ሕግጋት ይመነጫሉ ማለቱ፥ አዎ ከሸሪዓ-ጋር ይገናኛል ያሰኛል።የሴቶችን እኩልነት፥ የእስረኞችን መብት፥ የመገናኛ ዘዴዎችን፥ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ነፃነት፥ በነፃ የመደራጀትና ሐሳብን በነፃ የመግለፅ መብቶችን የሚደነግጉት አንቀፆች ደግሞ አይ-ያሰኛል።ዲሞክራሲያዊ ነዉ።

ብቻ ግብፆች እንዲሕ ተከፋፍለዉ ግሚስ ግብፅ ቅዳሜ ድምፅ ሰጠ።የተቀረዉ በያዝነዉ ሳምንት ማብቂያ ይቀጥላል።ግብፅ-እንደ ሥርዓት፥ እርምጃ ደጋፊ ተቃዋሚ፥ ገለልተኛ እሁለት፥ እሰወስት ሲከፈል ግን ያሁኑ የመጀመሪያዉ አይደለም።

የሆስኒ ሙባራክ ደጋፊና ተቃዋሚዎች ተሕሪር አደባባይ መሠለፍ፥ መጋጨት፥ ተቃዋሚዎች በፀጥታ ሐይሎች መገደል፥ መታፈን፥ መደብደብ፥ መታሰራቸዉ ያበቃዉ በሙባረክ መወገድ ነበር።የግብፅ ሕዝብ የሙባረክ ዘመኑን ሕገ-መንግሥት ለማሻሻል ድምፅ የሰጠዉ የሙባረክን ሥልጣን የተረከበዉ የጦር ጄኔራሎች ምክር ቤት፥ በሥልጣን ለመቆየት ማሴሩን በመቃወም አደባባይ የወጣዉ ሕዝብ፥ ከፀጥታ አስከባሪዎች ጋር በሚጋጭ፥በሚደበደብ፥ በሚገደል፥ በሚታሰርበት መሐል ነበር።

መጋቢት 19/ 2011 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ።)

በተሻሻለዉ ሕገ-መንግሥት መሠረት የግብፅ ሕዝብ በረጅም ጊዜ የሐገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሕግ-መወሰኛና መምሪያ ምክር ቤቶች እንደራሴዎቹን በነፃ መርጧል።ሕዝቡ ከሕዳር-ሁለት ሺሕ አስራ-አንድ፥ እስከ ጥር ሁለት ሺሕ አስራ-ሁለት ሁለቴ ድምፁን የተሰጠዉ ጦር ሐይሉ አዲስ የደነገገዉን ያስቸኳይ ጊዜ-አዋጅ በአደባባይ ሰልፍ በሚቃወም፥ በተቀናቃኝ ፖለቲከኞች አቋም እብዙ ሥፍራ ተገምሶ በሚሟገት-በሚከራከርበት መሐል ነበር።

የመጀመሪያዉ ዙር ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ባለፈዉ ግንቦት ሲደረግም ተሕሪር አደባባይ ተሰላፊ አላጣም ነበር።በግብፅ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሕዝብ ነፃ ፍላጎትና ቀጥተኛ ተሳትፎ የተመረጠዉ ምክር ቤት በተሰየመ ማግስት ካፀደቃቸዉ አዋጆች፥ በሙባረክ ዘመን ከፍተኛ ሥልጣን ላይ የነበሩ ፖለቲከኞች በወደፊቷ ግብፅ ከፍተኛ ሥልጣን እንዳይዙ የሚያግደዉ አንዱ ነበር።

ሰኔ አጋማሽ።የግብፅ ሕዝብ ለመጨረሻዉ ዙር ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ካለፉት እጩዎች አንዱን ለመምረጥ ሁለት ቀን ሲቀረዉ፥-በሙባረክ የተሾሙ፥ የተሸለሙት የሐገሪቱ ሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ዳኞች በሞተ-ሥርዓታቸዉ ላይ እስትንፋስ ለመዝራት ሐያል-ጠንካራ ጥይታቸዉን ተኮሱ።

ምክር ቤቱን አግዱ።ዉሳኔዉን ሻሩ፥ ሥልጣን ላይ ያሉት የጦር ጄኔራሎች ጓደኛ፥ የሙባረክ የመጨረሻ ጠቅላይ ሚንስትር የነበሩትን እና ለፕሬዝዳትነት የሚወዳደሩትን የማርሻል አሕመድ ሻፊቅን እጩነት አፀደቁ።

ከአየር ሐይል ማርሻል አሕመድ ሻፊቅ ጋር የሚወዳደሩት የቀድሞዉ የሙስሊም ወንድማማቾች ፖለቲከኛ ዶክተር መሐመድ መሐመድ ሙርሲይ የፍርድ «ቤቱ ዉሳኔ መከበር አለበት» ነበር-ያሉት ያኔ።ሕዝቡን ግን ዉሳኔዉ ለሌላ ተቃዉሞ፥ ለሌላ ሰልፍ አሳደመዉ፥ ሌላ ክክፍል፥ እና አምስተኛዉ ድምፅ።ወይም ምርጫ።

በሰልፍ፥ ግጭት፥ ክፍፍሉ የተሰላቹት ምናልባትም የተጎዱት ጡረኛ በቃን አሉ፥-ስድስተኛዉ ድምፅ በሚሰጥበት ዕለት ዋዜማ-በቀደም።

«ከእንግዲሕ አለመረጋጋት አንሻም።መኖር ነዉ-የምንፈልገዉ።ደሞዝ ይከፈላል-ማለት አይቻልም። የጡረታ አበላችን ትንሽ ነዉ።የምግብ ዋጋ ዉድ ነዉ።»

ሕዝባዊዉ አብዮት አምባገናዊ ሥርዓትን ለማስወገድ፥ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት፥ የሕዝብ መብት ነፃነትን፥ ለማስከበር መጥቀሙ አላነጋገረም።የተቃዉሞ፥ ድጋፉ ሠልፍ፥ መንዛዛት ግን የግብፅን ምጣኔ ሐብት ክፉኛ ጎድቶታል።

ካለፈዉ ሕዳር ጀምሮ ፕሬዝዳት ሙርሲ የሕገ-መንግሥታዊዉን ፍርድ ቤት ሥልጣን ለመቀነስ ያወጁትን ደንብ በመቃወምና በደገፍ፥ አዋጁን ከሻሩ በሕዋላ ደግሞ በረቂቅ ሕገ-መንግሥቱ ሰበብ ሙርሲንና ሙስሊም ወንድማማቾችን በመቃወምና በደገፍ የተደረገዉ ሠልፍና ግጭት እንኳ ግብፅ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ለመደበደር የጠየቀችዉን የ4.8 ቢሊዮን ዶላር ብድር የሚሰጥበት ጊዜ እንዲዘገይ አስገድዷታል።

ክፍፍል፥ ዉዝግቡ ግን ከረቂቅ ሕገ-መንግሥቱ መፅደቅ ወይም መዉደቅ በሕዋላም የሚረግብ አይመስልም።እንዲያዉም አንዳዶች፥- የሙስሊም ወንድማማቾና አክራሪ ሙስሊሞችን ባንድ ወገን፥የሙባረክ ሥርዓት ቅሪቶችን፥ ለሐይማኖት ያልወገኑና ግራ-ክንፍ ፖለቲከኞችን በተቃራኒዉ ያሠለፈዉ ልዩነት ወደ ከፋ ግጭት እንዳያመራ ያሠጋል ባዮች ናቸዉ።

ተቃዋሚዉ ፖለቲከኛ መሐመድ ሐሺም ግን ሥጋቱን ያጣትሉታል።

«እንዲያዉም በተቃራኒዉ እኔ ተስፈኛ ነኝ።በሙባረክ ዘመን በፀጥታ አስከባሪዎች አማካይነት የሚፈፀም የጨቋኞች ግንብ ነበር።ሥርዓቱ በስብሶ ግንቡ ፈርሷል።ሙባረክ ከተወገዱበት (11.02.11) ሙርሲ ለፕሬዝዳትነት እስከተመረጡበት የነበረዉ ጊዜ ብዙዎች የተገደሉበት፥ ብዙ ደም የፈሰሰበት፥ መጥፎ ጊዜ ነበር።ጦር ሐይሉ ሥልጣን የያዘበት ወቅት ነበር።ጦሩ ሥልጣን ሲለቅ ሁለተኛዉ ግንብ ተንዷል።አሁን የቀረዉ ሰወስተኛዉ ግንብ ነዉ።የሙስሊም ወንድማማቾችና እስላማዊ ሕገ-መንግሥታቸዉ።»

በሐሺም ቋንቋ ሰወስተኛዉን ግንብ ለመናድ፥-የሳቸዉ ብጤ ፖለቲከኞች ቆርጠዋል።ዶክተር መሐመድ ኤል-በረዳይ፥ ዶክተር አምር ሙሳ፥ ማርሻል አሕመድ ሻፊቅም ከጎናቸዉ አሉ።ኤል በረዳይ፥በሆስኒ ሙባረክ ዘመን ከዲፕሎማትነት፥ እስከ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአቶሚክ ተቆታጣሪ ባለሥልጣን ሐላፊት የደረሱ ናቸዉ።ሙባረክ ሊወድቁ ወራት ሲቀራቸዉ ሐገራቸዉ ተመለሱ፥ ሙባረክ ሊወገዱ ዕለታት ሲቀራቸዉ ደግሞ ተቃዋሚዉን ጎራ ተቀየጡ።

አምር ሙሳ የሙባረክ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር፥ለአረብ ሊግ ዋና ፀሐፊነት በሙባረክ የተሾሙ ፖለቲከኛ ነበሩ።ሕዝባዊዉ አመፅ ሲግም ወደ ተሕሪሪ አደባባይ ብቅ አሉ።አሕመድ ሻፊቅ ከፓይለትነት እስከ የአየር ሐይል አዛዝዥ ማርሻልነት፥ ከሚንስትርነት እስከ ጠቅላይ ሚንስትርነት ሙባረክን በታማኝነት አገልግለዋል።የጠቅላይ ሕገ-መንግሥታዊዉ ፍርድ ቤት ዳኞችም እንዲሁ።

አሁን ከነሐሺም ጋር ያበሩት ሁሉ በሚሾሙ፥ በሚሸለሙ፥ በሚሽሞነሞኑበት ዘመን፥እንደ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ወይም መምሕርር ከደብተር፥ እርሳስ፥ እስኪርቢቶ፥ ጠመኔ-ጋር ተጣብቀዉ የነበሩትን በሕዝብ ድምፅ የተመረጡትን ሙርሲን ለመቃወም ባንድ አብረዋል።የሐሺሙ ሰወስተኛ ግንብ ሙስሊም ወንድማማቾች ደግሞ ከንጉስ ፋሩቅ-እስከ ገማል አብድ ናስር፥ ከአንዋር አሳዳት እስከ ሆስኒ ሙባረክ በነበሩት ሥርዓቶች ሲደቆስ፥ ሲደፈለቅ፥ ሲጨፈለቅ ሥልቱን እየቀያየረ በሕቡዕ የኖረ ማሕበር ነዉ።የሐሺም ምኞት ዳር ይደርስ ይሆን? ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

Egyptian President Mohammed Morsi is seen during a photo opportunity in his office at the presidential palace in Cairo, Egypt, Saturday, Dec. 8, 2012. Egypt's military said Saturday that serious dialogue is the "best and only" way to overcome the nation's deepening conflict over a disputed draft constitution hurriedly adopted by Islamist allies of President Mohammed Morsi, and recent decrees granting himself near-absolute powers.(Foto:Maya Alleruzzo/AP/dapd)
ሙርሲምስል AP
epa03267748 Egyptian presidential candidate Ahmed Shafik (C) casts his vote at a polling station during the run-off presidential elections in Cairo, Egypt, 16 June 2012. Some 50 million people are eligible to vote in the two-day poll to pick a successor to former president Hosni Mubarak, who was deposed in a popular revolt last year. The two contenders; Muslim Brotherhood candidate, Mohammed Morsi, and Mubarak's last PM, Ahmed Shafiq, failed to secure an outright majority in the first round last month. EPA/KHALED ELFIQI +++(c) dpa - Bildfunk+++
ሻፊቅምስል picture-alliance/dpa
epa03483401 Mohammed El-Baradei (2-L) Nobel Peace Prize laureate and former head of the United Nations' nuclear watchdog walks next to former Presidential candidate Hamdeen Sabahi (3-L) during a rally over Morsi decrees, in Garden City, Cairo, Egypt, 23 November 2012. Opposition planned a mass rally to protest constitutional changes ordered by the Islamist President Morsi. Morsi on 22 November signed constitutional amendments making his decisions immune to judicial review. EPA/STR +++(c) dpa - Bildfunk+++
ኤል ባራዳይ ከሌሎች ተቃዋሚዎች ጋርምስል picture-alliance/dpa
Women formed discussion groups as they stood in the lines waiting to vote. 15.12.2012, Heliopolis Copyright: DW/A. Hamdy
ድመፅ ሠጪዉምስል DW/A. Hamdy
Egyptian referendum officials count votes at a polling station in Cairo, Egypt, late Saturday, Dec. 15, 2012. Egyptians took their quarrel over a draft constitution to polling stations Saturday after weeks of violent turmoil between the newly empowered Islamists and the mostly liberal opposition over the future identity of the nation. (Foto:Amr Nabil/AP/dapd).
ድምፅ መስጪያዉምስል AP

ነጋሽ መሐመድ
ተክሌ የኋላ

















ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ