1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ

ዓርብ፣ ጥቅምት 11 2009

የኢትዮጵያ ፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የሕዝብ ግንኙነት እና የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፈንታው አምባው የጦር መሣሪያ አያያዝ በሕግ አግባብ ቁጥጥር ሊደረግበት እንደሚገባ አሳስበዋል። ሆኖም የአዋጁ አፈፃጸም መመሪያ ትጥቅ ማስፈታት አንዳልሆነ ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/2RXWu
Infografik Karte Proteste und Ausschreitungen in Äthiopien 2016

Int. Mit äthiopiesche Justizminister PR. die Ausrufen des Ausnahmezustands - MP3-Stereo

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መመሪያ ውስጥ የጦር መሣሪያን የተመለከቱ ሁለት አንቀጾች አሉ። አነዚህ አንቀጾች ውስጥ የተጠቀሱት ክልከላዎች እና በቁጥጥር ስር ስለዋሉ ሰዎች በመመሪያው የተካተቱት ሃሳቦች ጥያቄዎች እያስነሱ ነው ። መመሪያው ትጥቅ የማስፈታት ዓላማ ያለው ነው የሚሉ አስተያየቶችም ይሰማሉ ። የኢትዮጵያ ፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት ግን ይህን ያስተባብላል ። የመስሪያ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት እና የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፈንታው አምባው በአንዳንድ የሀገሪቱ ቦታዎች ኅብረተሰቡን ጦር መሣሪያ ለማስፈታት እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ስለመባሉ ለዶቼቤለ በሰጡት መልስ «የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ትጥቅ የማስፈታት መንፈስ የለውም» ብለዋል። 

«እነዚህ የጦር መሣሪያዎች በተለያየ መንገድ ኹከቱን እና ብጥብጡን የሚያባብሱ እና አሁን ያለውን አጠቃላይ ኹከት እና ብጥብጥ ራዲየሱን እያሰፋ የሚሄድ ሆኖ በመገኘቱ፤ ላልተገባ ጥቅም እየዋለ በመሆኑ፤    የማኅበረሰቡን ሠላም፣ መረጋጋት እና አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴውን ወይም በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው ላይ በሀገሪቱ አጠቃላይ ኢንቨስትመንት ላይ ጉዳት እየደረሰ በመሆኑ ይኼንን ጉዳት በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመቆጣጠር እንዲቻል ነው፤ የጦር መሣሪያ አያያዝ በሕግ አግባብ ቁጥጥር ሊደረግበት ስለሚገባ ነው፤ እንጂ የኅብረተሰቡን መሣሪያ ወይንም ትጥቅ የማስፈታት መንፈስ የለውም።»

በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል አንዳንድ ቦታዎች ትጥቅ የማስፈታት እንቅስቃሴ እንደሚደረግ ይሰማል።  አቶ ፋንታው ግን «ሙሉ በሙሉ ከዕውነት የራቀ ወሬ ነው» ሲሉ ነው የመለሱት ። በአዋጁ «ማንኛውም ሰው በሕግ የተፈቀደለትን ጦር መሣሪያ በራሱ የግል ይዞታው አካባቢ ይዞ እንዳይንቀሳቀስ የሚል ነገር አልወጣም» ሲሉም አክለዋል። ከዚህ ሌላ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎችም እንደጥፋታቸው መጠን ታይቶ ቀለል ያለ ወንጀል የፈጸሙት «የተሐድሶ» ያሉትን ስልጠና እንደሚሰጧቸው አቶ ፈንታው ተናግረዋል። 

«በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በወንጀል ድርጊት ውስጥ የተሳተፈ ማንኛውም አካል ከተጠያቂነት የሚድንበት አግባብ የለም። ዞሮ ዞሮ አለማወቅ ከተጠያቂነት ስለማያድን ማለት ነው። ነገር ግን እጅግ በጣም ቀላል እና በተሐድሶ ብቻ የተሻለ የባሕሪ ለውጥ አምጥተው በጉዳዩ ላይ ግንዛቤ እንዲጨብጡ በማድረግ፣ በማስተማር ጠቃሚ የማኅበረሰቡ አባል ሆነው እንዲቀጥሉ እና ከእንደዚህ አይነት ተመሳሳይ የጥፋት ድርጊቶች እንዲቆጠቡ የማድረግ፣የማስተማር ሥራም የዚህ የአዋጁ አንዱ ዓላማ ነው።»

Äthiopien Tote bei Anti-Regierungs-Protesten in Bishoftu
ምስል DW/Y. Gegziabher

ይሰጣል የተባለው «የተሐድሶ» ስልጠና የት እንደሚከናወን እንዲያብራሩ ለቀረባለቸው ጥያቄ አቶ ፈንታው ሲመልሱ  «እሱ መንግሥት በመረጠው ቦታ ላይ የሚሰጥ ነው የሚሆነው። በዚህ ደረጃ የሚጠየቅ ጥያቄ አይመስለኝም።»ብለዋል። 


የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ  ኮማንድ ፖስት ማለትም የእዝ ጣቢያ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ 1645 ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የኢትዮጵያ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ ሮይትርስ የዜና ወኪል አስታውቋል። እስሩ እንደቀጠለ የመንግሥት እና ለመንግሥት ቅርበት ያላቸው መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።   

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ