1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጥምቀት፤ ከከተራ እስከ ቃና ዘገሊላ

ሐሙስ፣ ጥር 12 2008

«ጥምቀት በጣም የደመቀ በዓል ነዉ። እንደ ድሮ ጊዜ ህዝቡ ዝም ብሎ ገብቶ ከታቦቱ ጋር መጋፋት ከቀሳዉስት ዲያቆናት ጋር መጋፋት የለም፤ ሕዝቡ በስርዓት ሆ እያለ፤ እየጨፈረ ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ እንደሚለዉ ሴትዋም እንደው ነጭ የሃገር ባሕል ልብሷን ለብሳ ወንዱም ነጭ የሃገር ባህል ልብሱን ለብሶ፤

https://p.dw.com/p/1Hhxp
Äthiopien Hoher äthiopischer Timkat in Addis Abeba
ምስል DW/Y. Gebere Gziabeher

ጥምቀት፤ ከከተራ እስከ ቃና ዘገሊላ

ረጅም ሽመሉን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀብቶ ካህናቱ እየዘመሩ፤ እያመሰገኑ ሲሄዱ ሕዝቡ ደግሞ ሆ እያለ ደስታዉን እየገለፀ የሚያከብረዉ ትልቅ በዓል ነዉ» ጥምቀት!
እንኳን ለብርኃነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሳችሁ፤ አንጋፋዉን ጋዜጠኛ ንጉሴ አክሊሉን የተናገረዉ ነዉ። በዛሬዉ ዝግጅታችን በቅርስነት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት «UNESCO» እንዲመዘገብ ጥረት እየተደረገ ስላለዉና በኢትዮጵያዉያንን ዘንድ በድምቀት ስለተከበረዉ የጥምቀት በዓል ክብረ እንቃኛለን።

የጥምቀት በዓል ከጊዜ ወደ ጊዜ የዓለም አቀፉን ኅብረተሰብ ቀልብ እየሳበ የመጣ ታላቅ ኃይማኖታዊ ክብረ በዓል ነው። ኢትዮጵያ ጥምቀትን ከሚያከብሩ ጥቂት የዓለማችን ሃገሮች አንዷ እና ዋነኛዋ ናት። ይህ ታላቅ ኃይማኖታዊ በዓል ከሕዝቡ ባህል ጋር ጥብቅ ትስስር ያለው ስለሆነም ከኃይማኖታዊ በዓልነቱ ባሻገር ባሕላዊ ፋይዳውም አብሮ የሚሄድ ነው። ለዚህም ዳንሱ ጭፈራዉ ሎሚ ዉርወራዉና የፍቅር ጓደኛ መተዋወቁ ከጥምቀት በዓል ጋር ተያይዘዉ የሚታዩ በሥነ-ቃልም የሚገለፁ ክስተቶች ናቸው። የኢትዮጵያ የቅርስ አስተዳደር ሰነድ ዝግጅት ከፍተኛ ኤክስፐርት አቶ ኃይለመለኮት አግዘዉ እንደሚሉት ጥምቀት ለሦስት ቀናት ማለትም ከተራ እስከ ቃና ዘገሊላ በተከታታይ የሚከናወን የአደባባይ ክብረ በዓል ነዉ።

Äthiopien Hoher äthiopischer Timkat in Addis Abeba
ምስል DW/Y. Gebere Gziabeher


በዉጭ አገር ኢትዮጵያዉያን የጥምቀት በዓል እንዴት ያከብሩት ይሆን። በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ኃላፊ ሊቀ ካህናት ዶክተር መርዓዊ ተበጀ በዓላቱን ልክ እንደ ሃገራችን ማክበር አንችልም ሲሉ ገልፀዉልናል። ምክንያቱ ደግሞ የምዕመኑ የሥራ መግቢያ ጊዜ የተለያየና ጀርመናዉያን የጥምቀት በዓልን ስለማያከብሩ ነዉ።
እንዲያም ሆኖ ግን የባህል አልባሳትን የለበሱ ምዕመናን መዘመራን ክብረ በዓሉን በዝማሪና በሽብሸባ በቅዳሴ እንደሚያደምቁት ሊቀ ካህናት ዶክተር መርዓዊ ተበጀ ተናግረዋል።
በቅርቡ ወደ ዩኤስ አሜሪካ ኮለራዶ የተጓዘዉ ወጣት ሰለሞን መኮንን፤ በዉጭ የጥምቀት በዓል አከባበርን አይቶ «ወገኔ » ሲል የገጠማትን ልኮልናል፤ በአጭሩ እንዲህ ይላል
ወገኔ
የኔ አገር እንዲህ ነዉ
ወግና ባህሉ ደምቆ እሚታይበት
እንዲህ ነዉ የኔ አግር
ታቦታቱ ወጥተው ከተራ እሚያድሩበት
እንዲህ ነዉ የኔ ወንዝ
ጃልሜዳና ጎንደር እሚጥለቀለቁበት
እንዲህ ነዉ የኔ ህዝብ
ታቦታቱን ከቦ ሜዳ የሚያድርበት
እንዲህ ነዉ ወገኔ
ለፀሎት ምህላ ድንኳን ሚጥልበት
እንዲህ ነዉ ልማዱ
ጥምቀትን ሲያከብር ዉዳሴ ፀሎቱ
እንዲህ ነው ሀገሬ
የትዉልድ መንደሬ

Äthiopien Hoher äthiopischer Timkat in Addis Abeba
ምስል DW/Y. Gebere Gziabeher
Äthiopien Timkat Fest in Addis Abeba
ምስል DW/Azeb Tadesse Hahn


የጥምቀት በዓል በተመ የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት «UNESCO» እንዲመዘገብ በተደጋጋሚ ጥያቄ መቅረቡን የኢትዮጵያ የቅርስ አስተዳደር ሰነድ ዝግጅት ከፍተኛ ኤክስፐርት አቶ ኃይለመለኮት አግዘዉ ተናግረዋል። ቃለ- ምልልስ የሰጡንን በዶቼ ቬለ ስም እያመሰገንን ዓመት ዓመት ያድርሰን በማለት የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን እንዲያደምጡ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ


ሂሩት መለሰ