ጥሩ ህይወት ፍለጋ
ዓርብ፣ ኅዳር 7 2005ለፍርድ በቀረበችበትም ወቅት ሰራተኛዋን መደብደቧን አምና ግን ለመግደል ፈልጋ እንዳልነበር ገልፃለች። ሰራተኛዋ ከመሞቷ 10 ቀናት በፊት ሟቿን በኮረንቲ ገመድ ገርፋ እስራት ነበር። ይህም አልበቃ ብሎ የፈላ ውሀ ደፍታባት አይኗ ውስጥ ደግሞ ቁንዶ በርበሬ ጨምራለች። ይህ ሁሉ የሆነው እሷ እንደምትለው፤ ሰራተኛዋ «ሰነፍ»ስለሆነች ነው።
ይህንን ስቃይ ማየት ያልቻለው የቀጣሪ ልጅ ታድያ ፖሊስ ጠርቶ እናቱን በፖሊስ ቁጥጥር ስር አውሏል። ስቃዮን መቋቋም ያልቻለችው ኢትዮጵያዊት ወጣት ግን በድብደባው በመጎዳቷ ህይወቷን አጥታለች።
እንደ ሂውማን ራይትስ ዎች ያሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በተደጋጋሚ ለአመታት ከውጭ ሀገር የሚመጡ የቤት ሰራተኞች ላይ ስለሚፈፀሙ ጥቃቶች ሲመዘግቡ ቆይተዋል። የድርጅቱ የመካከለኛው ምስራቅ እና ሰሜን አፍሪቃ ምክትል ኃላፊ ናዲም ሀውሪ ፤ «በብዛት የሚታዩት ጉዳቶች፤ ደሞዝ ያለመክፈል፣ በቀጣሪዎች የሚደረጉ የኃይል ርምጃዎች፣ ሰራተኞቹ በሳምንት አንዴ ወይንም ጭራሽ ቤቱን ለቀው እንዳይሄዱ የማድረጉ ሁኔታ ፣ አገር ቤት ካሉ ቤተሰቦቻቸው ጋ እንዲገናኙ ያለመፍቀድ፤ በተጨማሪ በቃል እና በድርጊት የሚደረጉ ጉዳቶች፣ ከዛም አልፎ እስከ ወሲብ ጥቃት ይደርሳሉ ።» ይላሉ ሀውሪ
በቀጣሪ እና በተቀጣሪ መካከል ችላ ሊባል የማይገባው እና እስከ ጥል ድረስ የሚያደርሰው ዋና ምክንያት የቋንቋ ችግር ነው። በርካታ ከኢትዮጵያ የገጠሩ ክፍል ወደ አረብ ሀገር የሚሄዱ ወጣቶች፤ የአረብኛም ይሁን የእንግሊዘኛ ቋንቋ ችሎታ የላቸውም። ከዚህም ረገድ በኤጀንሲም ይሁን በግል ቅድመ ዝግጅት ሲደረግ አይታይም። ለብዙዎች ዘመናዊው ሀገር መደናገር ገና ከሀገር ሳይወጡ አዲስ አበባ ይጀምራል። ሆኖም በየቀኑ ወደ አረብ አገር የሚሄደው ሰው ቁጥር ብዙ ነው።
አራት ሚሊዮን ነዋሪ ያላት ሊባኖስ 200 000 የሚሆኑ የውጭ ሀገር ሰራተኞች ይኖሩባታል። ለሰራተኞች መብት የሚታገሉት ሀገራት ግን ጥቂት ናቸው።
« በአንዳንድ አገሮች አንዳንድ መሻሻል አለ።ለምሳሌ ዮርዳኖስ ለቤት ሰራተኞች አዲስ ህግ አውጥታለች። ሊባኖስ የቤት ሰራተኞች መብት የሚከበርበትን ውል አፅድቃለች። ነገር ግን እነዚህ ህጋዊ መሳሪያዎች በተግባር ላይ አልዋሉም። »
አንዳንድ ጥቃት የደረሰባቸው ወጣት ሴቶች እንደሚገልፁት ወደ ኢትዮጵያ ኤምባሲ ሄደው ምንም አይነት ድጋፍ እንዳላገኙ ነው። ለመሆኑ ማነው ለዚህ ሁሉ ኃላፊነት መውሰድ ያለበት? ሀውሪ፤
« እንደሚመስለኝ ቀዳሚው ኃላፊነት ያለው እንግዳ ተቀባይ ሀገራት ጋ ነው። አንድ ጥቃት ከደረሰ ይህ የእንግዳ ተቀባይዋ ሀገር የፍትህ ሚንስቴር እና ፖሊስ ስራ ነው ። በመቀጠል የሚልኩት ሀገራት ኃላፊነት አለባቸው በአንዳንድ ሀገራት ለምሳሌ ፊሊፒንስ ኤምባሲ፤ መንገዶችን ሲያመቻች ተስተውሏል። ሌሎች ሀገሮች ኢትዮጵያን ጨምሮ ደካማ አቅራቦት ነው ያላቸው። አዳዲስ ሰራተኞችን በመላክ ላይ የሚገኙ እንደ ኔፓል እና ማዳጋስካር ያሉ ሀገራት ደግሞ ጭራሽ ኤምባሲም የላቸውም። »
ሳውዲ አረቢያ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኤምባሲ የቤት ሰራተኞችን ጉዳይ አስመልክቶ ለመጠየቅ በስልክም ይሁን በፁሁፍ ያቀረብንላቸው ጥያቄ እስካሁን መልስ አጥቷል።
የሂውማን ራይትስ ዎች የመካከለኛው ምስራቅ እና ሰሜን አፍሪቃ ምክትል ኃላፊ ናዲም ሀውሪ እንደሚሉት ከግንዛቤ ማስጨበጥ ያለፈ ስኬት ብዙም አይታይም።
« እንደሚመስለኝ በአካባቢው ስላለው ችግር ግንዛቤ እንዲገኝ ሆኗል። በርካታ የአካባቢው እና ወጣት ሰራተኞች ስላለው ግንዛቤ እንዲገኝ መንገድ ፈጥረዋል። ይህ አንድ ምልዕክት ይመስለኛል። ይሁንና በሀገራት ደረጃ መሻሻል አልተመለከትንም። እንደሚመስለኝ ችግሩ እንደ ችግር አልተቆጠረም። ምንም አይነት መፍትሄ የሚሆኑ ርምጃዎችም አልተወሰዱም።» የዶይቸ ቬለ ዘጋቢ ነብዩ ሲራክ በሳውዲ አረቢያ ሲኖር በርካታ በቤት ሰራተኝነት ሊሰሩ የመጡ ሴት ኢትዮጵያንን አግኝቷል። በአጠቃላይ ያሉበትን ሁኔታ ነግሮናል።
ልደት አበበ
ነጋሽ መሐመድ