1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጥቃት በስደተኞች መጠለያ

ማክሰኞ፣ ጥር 10 2008

ሉቤክ በተባለችው የሰሜን ጀርመን ከተማ ሃፈንሽትራሰ በተባለ ስፍራ ይገኝ በነበረ አንድ የተገን ጠያቂዎች መጠለያ ላይ የዛሬ 20 አመት የተጣለው ጥቃት በዘመናዊ ጀርመን ታሪክ ከደረሱት መሰል ጥቃቶች በአደገኛነቱ ይጠቀሳል ። የጥቃቱ 20 ኛ አመት ከትንናት በስተያ ታስቧል ።

https://p.dw.com/p/1Hg8o
Deutschland Brand Flüchtlingsunterkunft Hafenstraße in Lübeck
ምስል picture alliance/dpa/R. Rick

ጥቃት በስደተኞች መጠለያ

በዚሁ ስፍራ በጎርጎሮሳዊው 1996፣ ጥር 17 ለጥር 18 አጥቢያ ከለሊቱ 9:00 ሰአት ተኩል ግድም ስደተኞች የተጠለሉበት ህንጻ በእሳት ተለኩሶ የ10 ሰዎች ህይወት ሲጠፋ ሌሎች 38 ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል ። ከመካከላቸው አንዳንዶቹ ክፉኛ ነበር የቆሰሉት ። እሳት የተለኮሰበት ይህ ህንጻ የ48 ተገን ጠያቂዎች መኖሪያ ነበር ።የሉቤክ ማዘጋጃ ቤት የጥቃቱን 20ኛ አመት ምክንያት በማድረግ ባወጣው መግለጫ አደጋው የደረሰበትን ዕለት በከተማይቱ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ከሚታወቁት አሳዛኝ ቀናት አንዱ ብሎታል ።የዛሬ 20 አመት ጥቃት በደረሰበት በዚህ አካባቢ ለሞቱት መታሰቢያ የሚሆን ድንጋይ ተቀምጧል ።የዶቼቬለው ማትያስ ፎን ሃይን እንደዘገበው እስካሁን በዚህ የእሳት ቃጠሎ ተወንጅሎ ለፍርድ የቀረበ ሰው የለም ። ሚሻኤል ቡታይለር አደጋው በደረሰበት ወቅት የከተማይቱ ከንቲባ ነበሩ ። ለ12 አመት የሉቤክ ከተማ ከንቲባ የነበሩት ቡታይለር ከትናንት ወዲያ ምሽት የሞቱትን ለማሰብ በተካሄደ ስነ ስርዓት ላይ ተገኝተው ነበር ። የቀድሞው ከንቲባ ያኔ የሆነውን ለጋዜጠኞች ሲናገሩ እንባ ይቀድማቸዋል። ቡታይለር እንደሚሉት በከተማይቱ በ1990 ዎቹ በእሳት የተቃጠለው የተገን ጠያቂዎች መኖሪያ ብቻ አልነበረም ።
«መታወቅ ያለበት በጎርጎሮሳዊው 1996 የደረሰው የእሳት አደጋ ሉቤክ ውስጥ ከተጣሉት 4 የእሳት ጥቃቶች አንዱ ነበር ። ከዚያ ቀደም ሲል በጎርጎሮሳዊው 1994 እዚህ ሉቤክ ይገኝ የነበረ ሙክራብ ተቃጥሏል ።ይህ አንዱ ትልቅ ክስተት ነበር ። በ1995ም ይኽው ሙክራብ ሌላ ሁለተኛ ቃጠሎ ደርሶበታል ። በ1996 ደግሞ የሀፈንሽትራሰው የተገን ጠያቂዎች መኖሪያ ተቃጥሎ 10 ሰዎች ሞቱ ።በ1997 ደግሞ የቅዱስ ቪሲሊን የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ተቃጥሏል ።ቤተ ክርስቲያኗ ለአንድ አልጀሪያዊ ካህን ቤተሰብ ከለላ ሰጥታ ነበር ። »
በከተማይቱ የደረሱት እነዚህ ተከታታይ ጥቃቶች በወቅቱ ከተማዋንና ህዝቡን እንዳሸበሩ የቀድሞው ከንቲባ ቡታይለር ያስታውሳሉ ።ቡታይለር ከዚህ ሌላ በምርመራዎቹ አካሄድም ቅሬታ እንደነበራቸው ሳይገልፁ አላለፉም ።
«የቃጠሎው መደራረብ ከተማዋን አናውጧት ነበር ። በነዋሪዋም ላይም ያኔ አለመረጋጋትን አስከትሏል ።ያኔ እደተሰማኝ ሁሉ ዛሬም ጉዳዩ በጣም ያሳዝነኛል ። በምርመራው ሂደት የጥቃቱ ሰለባዎች እንደ ወንጀለኞች ተቆጥረው ይመረመሩ ነበር ። ሆኖም ምንም ዓይነት መረጃ አልተገኘባቸውም ።ይህ በጣም ትልቅ ክስተት ነበር ። አንዳንዶቹ ጉዳዮች በትክክል አልነገሩም ነበር ።»
ቡታይለር በይፋ ያልተናገሩት በርሳቸው ላይ የተሰነዘረ ጥቃትም ነበር ። ያኔ ወደርሳቸው የተላከ በፖስታ የታሽጎ ቦምብ ፈንድቶ የሥራ ባልደረባቸውን ለከባድ ጉዳት ዳርጓል ።የቀድሞው ከንቲባ አሁን ከምንም በላይ የሚያበሳጫቸው የ10 ተገን ጠያቂዎች ህይወት የጠፋበት የሃፈንሽትራሰው ወንጀል እስካሁን እልባት አለማግኘቱ ነው ። በርሳቸው አስተያየት በወቅቱ ፖሊስ ያካሄደው ምርመራዊ አድሎአዊ ነበር።እርሳቸው እንደሚሉት ፖሊስ የመረመረው አደጋው በደረሰበት ህንጻ ውስጥ የሚኖሩትን ሰዎች ብቻ ነበር ።የቡታይለርን አስተያየት ጋዜጠኛ ዲተር ፎግልም ይጋራል ። የበርሊኑ ጋዜጠኛ ፎግል በሉቤኩ የእሳት ቃጠሎ ላይ ጥልቅ ምርመራ ካካሄደ በኋላ አንድ መፀሀፍ አውጥቷል ።የመፀሃፉን ንዑስ ርዕስ «ህጋዊ ቅሌት» ነው ያለው ። ፎግል ከዶቼቬለ ጋር ባካሄደው ቃለ ምልልስ እንደተናገረው ፖሊስ በቤቱ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ከወንጀሉ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጣራት ምርመራ አካሂዶ ነበር ።ሆኖም እሳቱ በተለኮሰበት ለሊት በአካባቢው የነበሩ ቀኝ ጽንፈኞች ላይ ግን ተገቢውን ምርመራ አላካሄደም ብሏል ።ፎግል እንዳለው የአደጋው አድራሾች ቀን ጽንፈኞች ሳይሆኑ እንደማይቀሩ የሚጠቁሙ በርካታ መረጃዎች ነበሩ ። የፖሊስ ምርመራ ይበልጥ ያተኮረው ግን በስደተኞች ላይ ነበር ።

«በጣም የሚገርመዉ መጀመርያ ቤት ዉስጥ ይኖሩ የነበሩ ሰዎችን እናንተ ናችሁ ቃጠሎዉን ያስነሳችሁ ተብሎ ምርምር መጀመሩ ነዉ። ሰዎቹ በሕገ ወጥ ሥራዎች ተሰማርተው እንደነበር ለማወቅ ምርመራ ተካሂዷል ። ከመካከላቸው አንድ ሊባኖሳዊ ወንጀለኛ ተብሎ ተያዘ ። በሌላ በኩል ግን ምሽት ላይ እዚያ አካባቢ ጥቃቱን መፈጸማቸውን የሚያመልክቱ አንዳንድ ጠቋሚ ምልክቶች የታዩባቸው ተጠርጣሪ ቀኝ አክራሪዎች ታይተዋል ። በእነዚህ ላይ ታድያ ምንም አልተደረገም።»
ብሪጅ
የሉቤኩን መሰል የእሳት ቃጠሎ አሁንም ጀርመን ውስጥ መድረሱ አልቆመም ። ከዚያ ወዲህ በተለይ በቅርብ ዓመታት በመቶዎች የሚቆጠሩ መሰል ጥቃቶች ጀርመን ውስጥ ደርሰዋል ።ይህን መሰሉ ጥቃት ተባብሶ መቀጠሉ በጣም አሳሳቢ መሆኑን ጋዜጠኛ ፎግል ሳይጠቅስ አላለፈም በቅርቡ እንኳን በምዕራብ ጀርመኑ በኖርድ ራይን ቬስትፋለን ፌደራዊ ክፍለ ሃገር ውስጥ ሙንስተርላንድ በተባለው አካባቢ በሚገኘው በቦርከን ከተማ የደረሰው ጥቃት በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነው ። 40 ሺህ ነዋሪ ባላት በዚህች ከተማ ፣ ከ9 ቀናት በፊት ማንነቱ ያልታወቀ አንድ ግለሰብ በከተማይቱ ለስደተኞች ማቆያ የተዘጋጀ ማዕከልን መስኮት ሰብሮ ህንፃውን በእሳት አጋይቷል ። ህንጻው ውስጥ ሰዎች ባለመኖራቸው የተጎዳ የለም ።አንድ የአይን ምስክር እንደተናገረው ጥቃቱን ያደረሰው ግለሰብ በብስኪሌት ሲያመልች አይቷል ።የጋዜጠኛ ፎግልን ስጋት ጀርመን ለሚገኙ ስደተኞች መብት የሚቆመው ፕሮ አዙል የተባለው ድርጅት ምክትል ሃላፊ ቤርንድ ሜሶቪክ ይጋራሉ ።ሜሶቪክ እንደሚሉት በጎርጎሮሳዊው 2015 ብቻ ጀርመን ውስጥ ለስደተኞች መጠለያ በተዘጋጁ ቤቶች ላይ 126 ሆነ ተብለው የተፈፀሙ የእሳት ቃጠሎዎች ደርሰዋል ። እንደ ሜሶቪክ በነዚህ ጥቃቶች የሰው ህይወት አለማለፉ ትልቅ ነገር ነው ። ሆኖም የጥቃቱ መጠን መጨመር ግን አሳሳቢ ነው ።
«አንድም ሰው በነዚህ አደጋዎች አለመሞቱ 2015 እድለኛ አመት እንደሆነ ሊሰማን ይችላል ።በርግጥም ይህ በርካቶች ከተገደሉባቸውና እጅግ ብዙዎችም ክፉኛ ከቆሰሉባቸው ከ1990ዎቹ ዓመታት ጋር ሲነፃጸር ትልቅ ልዩነት አለው ። ከ20 አመታት በፊት ጀምሮ የነበረው የቀኝ ጽንፈኞች እንቅስቃሴ በከፊል አስጊ በከፊል ደግሞ እንደ አዲስ እያንሰራራ ነው ። ከዚህ በተጨማሪ ማህበረሰቡ ዘንድም ገብቶ ለመግባት በተደጋጋሚ ሙከራዎች ያደርጋሉ »
ፕሮአዙል በጎርጎሮሳዊው 2015 ጀርመን ውስጥ ባሉ የስደተኞች መጠለያዎች ላይ 528 ጥቃቶች መድረሳቸውን መዝግቧል ።የፌደራል ጀርመን የወንጀል መርማሪ ፖሊስ ደግሞ በመላ ሃገሪቱ በዚሁ አመት በተገን ጠያቂዎች መኖሪያዎች ላይ 924 ጥቃቶች እንደተፈጸሙ አስታውቋል ። ይህም ከቀደመው 2014 አም ጋር ሲነፃጸር በአራት እጥፍ አድጓል ። የፌደራል ጀርመን የወንጀል መርማሪ ፖሊስ ባለፈው ህዳር አጋማሽ ባካሄደው አመታዊ ስብሰባ ላይ የመሥሪያ ቤቱ ሃላፊ እንዳሉት በሃገሪቱ የቀኝ ጽንፈኞች ጥቃት ጨምሯል ። ቀኝ ጽንፈኞች በአሁኑ ሰአት ህብረተሰቡ ጉዳዩን ጉዳዬ ብለው አለመያዙን በመጠቀም በተለይ መካከለኛ ገቢ ያለውን የህብረተሰብ ክፍል ከጎናቸው ለማሰለፍ እየጣሩ መሆኑን ሃላፊው ተናግረው ነበር ።እንደ ሃላፊው ይህ በመጠኑም ቢሆን እነዚህ ወገኖች የተሳካላቸው ይመስላል ። ባለፈው አመት በተገን ጠያቂዎች ማቆያ ማዕከላት በደረሱ ጥቃቶች ተጠርጥረው ከታሰሩት መካከል 70 በመቶው እስከ ዛሬ ድረስ ፖለቲካዊ አላማ ባለው ወንጀል ውስጥ የተሳተፉ አይደሉም ።የጀርመን የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ቶማስ ደሚዜርም በሃገሪቱ የጠበኞች ቁጥር እያደገ በመሄድ ላይ መሆኑ እንዳሰጋ ተናግረው ነበር ። እርሳቸውም በወቅቱ እንዳሉት በተገን ጠያቂዎች ላይ ጉዳት በማድረስ ተጠርጥረው ከተያዙት መካከል ሁለት ሶስተኛው ከዚህ ቀደም ምን አይነት ወንጀል ፈፅመው የማያውቁ የየአካባቢው ነዋሪዎች ናቸው ።እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች የአካል ጉዳትማድረስ ፣ በስደተኞች መኖሪያዎች ላይ እሳት መለኮስና መሰል ወንጀሎችን መፈፀማቸው ተቀባይነት እንደሌለው ሊረዱት እንደሚገባ ሚኒስትሩ በወቅቱ አበክረው ነበር ያሳሰቡት።ጀርመን ለጀርመናውያን ብቻ የሚል አስተሳሰብ የሚያራምዱ ቡድኖች ና ደጋፊዎቻቸው ሃገሪቱ ከ1ሚሊዮን በላይ ስደተኞች ወደ ሃገርዋ ባስገባችበት ባለፈው አመት ነው ጀርመን ውስጥ በተገን ጠያቂዎች መጠለያዎች ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት ያባባሱት ። ጥቃቱ እንዲቆም ወንጀለኞችም ለፍርድ እንዲቀርቡ ህብረተሰቡ ፖለቲከኞችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ወገኖች አበክረው ማሳሰባቸውን ቀጥለዋል ።

Ebeleben Asylbewerberunterkunft Drei Wohnblöcke Brandanschlag
ምስል picture-alliance/dpa/S. Kahnert
Deutschland Brand in künftiger Flüchtlingsunterkunft Ebeleben
ምስል picture-alliance/dpa/S. Kahnert
Deutschland Brand in einer Turnhalle in Nauen
ምስል picture-alliance/dpa/reportnet24.de

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ