1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጥቃት፣ እገታና ስጋት በናይጀሪያ

ሐሙስ፣ ሰኔ 19 2006

በናይጀሪያ ሰዓት አቆጣጠር ትናንት አመሻሹ ላይ በዋና ከተማ አቡጃ ህዝብ በሚያዘወትረዉ የገበያ ማዕከል የደረሰ ፍንዳታ ለ21 ሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት ሆኗል። ከ50 በላይ ሰዎችም መጎዳታቸዉ ተነግሯል።

https://p.dw.com/p/1CQl3
Nigeria Terror Anschlag Abuja
ምስል Reuters

ባለስልጣናት ፍንዳታዉ የደረሰዉ በቦምብ ጥቃት መሆኑን ገልጸዋል። ለጥቃቱ ኃላፊነት የወሰደ አካል እስካሁን ባይኖርም ፖሊስ ተጠርጣሪ መያዙን ገልጿል። በናይጀሪያ በተለይ በዚህ ዓመት በተደጋጋሚ በዋና ከተማ የደረሰዉ የቦምብ ጥቃት የሀገሪቱን ዜጎች ከማነጋገር አልፎ አስቆጥቷል። መንግስት የዚህን ሁሉ መንስኤ ያዉቃል የሚሉት ዜጎች ተገቢዉን አላደረገም በሚል እየወቀሱ ነዉ። ከትናንቱ የቦምብ ፍንዳታ በኋላ በናይጀሪያዋ ዋና ከተማ ንዴትና ሃዘን አንግሷል። ብዙዎች በሚያዘወትሩት የገበያ ማዕከል የደረሰዉ ፍንዳታ ቢያንስ የ21 ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል። ፖሊስ እንደሚለዉ በትናንቱ ፍንዳታ ከሞቱት ሌላ ጉዳት የደረሰባቸዉ 17 ሰዎች በአምስት ሃኪም ቤቶች በመታከም ላይ ናቸዉ።

Nigeria Abuja Bombenanschlag im Stadtteil Wuse
ምስል DW/K. Gänsler

የአካባቢዉ እማኞች ደግሞ 50 ያደርሷቸዋል። ፍንዳታዉ የደረሰበት ኢምባ ፕላዛ የተሰኘዉን የገበያ ማዕከል በበርካታ ወታደሮችና ፖሊሶች ዛሬ እየተጠበቀ ነዉ። ወደስፍራዉ የሚያደርሰዉ መንገድ በመዘጋቱም በገበያ ማዕከሉ ሱቆች ያሏቸዉ ነጋዴዎች ማለፍ አልቻሉ። ፍንዳታ በደረሰበት ስፍራ በድንጋጤ እንደተዋጡ ከተሰባሰቡ በርካቶች መካከል አንዱ ጋዜጠኛ ሲመለከት ንዴቱን መቆጣጠር የቻለ አይመስልም።

«አዎ የቦምብ ፍንዳታ ነዉ። እናዉቀዋለን። እዚያ ያለዉ ሁሉ በጣም ተቆጥቷል። ከአንቺ ማንም ምንም መንስማት አይፈልግም። ብትሄጂ ይሻላል። ነገ ተመለሺ፤ አሁን ማንም ሊያነጋግርሽ ፈቃደኛ አይደለም።»

እሱ ይህን ሲል በስፍራዉ የነበሩት መሰሎቹ በአዎንታ አንገታቸዉን አነቃነቁ። በስፍራዉ የደረሰዉ ከባድ ፍንዳታ ሰዎችን ከመጉዳቱ ሌላ ከፍተኛ መልዕክት እንዳስተላለፈ ነዉ በዓለም ዓቀፉ የግጭት መንስኤና መፍትሄ አጥኚ ተቋም የናይጀሪያ ጉዳይ ተመራማሪ ናምዲ ኦባሲ ያመለከቱት። መልዕክቱ እንደእሳቸዉ ከሆነ የሚለዉ« በከተማዋ በየትኛዉም ቦታ ቢሆን አስተማማን አይደለም» የሚል ነዉ። በገበያ ማዕከሉ በርካታ ሱቆች ይገኛሉ። አደጋዉ ከደረሰ ከሰዓታት በኋላ ልዩ የፀጥታ ኃይሎች አካባቢዉን መክበባቸዉን እማኞች ይናገራሉ። በቀለም ባሸበረቀዉ ትልቁ የገበያ ማዕከል ህንፃ አቅራቢያ ያሉትን የከሰሉ ተሽከርካሪዎች ለተመለከተ የፍንዳታዉን ከፍተኛነት መገመት ያስችላል። ከዚያዉ የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተዉ 17 የሚሆኑትን ተሽከርካሪዎች ያጋየዉ ፖሊስ ነዉ። ፍንዳታዉ ተሽከርካሪ ላይ በተጠመደ ፈንጂ ሳይሆን እንዳለቀረ ነዉ ብዙዎቹ የሚገምቱት። በያዝነዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት በዋና ከተማ አቡጃ ይህን መሰል የፍንዳታ ጥቃት ደርሶ በርካቶችን ሲጎዳ ይህ ለሶስተኛ ጊዜ መሆኑ ነዉ። ባለፈዉ ረቡዕ አዳማ በተባለዉ ግዛት በገበያ ስፍራ የደረሰ ተመሳሳይ ጥቃት ቢደርስም እንደሀገር ዉስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘገባ ከሆነ ሰዉ አልሞተም። የጥቃቶቹ አቀነባባሪም ቦኮ ሃራም መሆኑን አብዛኛዉ ናይጀሪያዊ ይገምታል። ለዚህም ነዉ በፍፁም ቁጣ ከሀገራችን የት እንሄዳለን ሲል ይህ ሰዉ የሚናገረዉ፤

Nigeria Abuja Bombenanschlag im Stadtteil Wuse
ምስል DW/K. Gänsler

«መሸሽ አልችልም፤ ይህ ሀገሬ ነዉ። የእኔ መገኛ ይህ ነዉ። ወደገበያ ማዕከሉ ሄጄ መግዛት የሚኖርብኝ ከሆነ እሄዳለሁ። መሸሽ አልፈልግም። ይህ ሀገሬ ነዉ ይህ ቤቴ ነዉ።»

ቦኮ ሃራም በተለያዩ አካባቢዎች የሚያደርሳቸዉ ጥቃቶች ያልጠበቁ መሆናቸዉን በተደጋጋሚ የታየ ይመስላል። ባለፉት ቅርብ ቀናትም የተለያዩ መንደሮች ላይ ጥቃት አድርሷል። ቡድኑ በስፋት የሚንቀሳቀስበት አካባቢ የደህነት ይዞታዉ ጥሩ እንዳልሆነ ነዉ የሚነገረዉ። በተደጋጋሚም የፖሊስና ወታደራዊ ኃይል በስፍራዉ ቢኖርም በቂ አይደለም በሚል ተተችቷል። ሁኔታዉ የከፋ መሆኑን የሚያሳየዉም በዚህ ሳምንትም በድጋሚ ቡድኑ በርካቶችን ጠልፎ መዉሰዱ ነዉ። የቦኮ ሃራም አባላት መሆናቸዉ የተገመተ ታጣቂዎች የሶስት ዓመት ህፃናትን ጨምረዉ 60 ሴቶችን ወስደዋል። ቦርኖ ግዛት ቺቦክ ቀበሌ ሚያዝያ ዉስጥ ከትምህርት ቤታቸዉ ታግተዉ የተወሰዱት ከሁለት መቶ የሚበልጡ ታዳጊ ሴቶች ጉዳይ እንዳነጋገረ ካለ መፍትሄ ዛሬ ላይ ደርሷል። ባለፉት ሳምንታት ሰላም የሰፈነባት መስላ የከረመችዉ አቡጃም ዳግም ለጥቃት ተጋልጣለች። ይህም በርካቶችን እጅግ አስጥቷል። ከከተማዋ ነጋዴዎች አንዱ አብዱ ካዚ መሪዎቻችን በሀገሪቱ ምን እየተካሄደ እንደሆነ አናዉቅም ሊሉን አይችሉም ይላሉ፤

«እንዲህ ባለ ሁኔታ አንድ መሪ ምን እየተካሄደ እንደሆነ አላዉቅም ሊለን አይችልም። ምን እየተካሄደ እንደሆነ በሚገባ ያዉቃሉ። ችግሩ ምን እንደሆነ ያዉቃሉ። ስለዚህ ለችግሩ መፍትሄ ይፈልጉ። እኛ ናይጀሪያዉያን ነን። አፍሪቃዉያን ነን። እንተባበራለን አንድ ሆነን እንዘልቃለን። ሊያታልሉን አይችሉም። በእነሱ ምክንያት ወዴትም ልንሸሽ አንችልም። ሀገራችን ይኸዉ ነዉ። ቤታችን ይኸዉ ነዉ። ግዛታችን ይኸዉ ነዉ።»

ካትሪን ጌንዝለር /ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ