1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ጥበብ በአደባባይ» በጎተ ተቋም

ሐሙስ፣ ግንቦት 17 2009

«ዝግጅቱ ጥበብ በአደባባይ የሚል ነዉ። ብዙ ጊዜ ጥበብ በጓዳችን ብቻ ነዉ ያለዉ። ለምሳሌ አንድ ሰዉ የስዕል ተሰጥኦ ይኖረዉና ወደ አደባባይ ለመዉጣት እድሉ አይኖረዉም። የሙዚቃ ተሰጥኦ ይኖረዉና ይዞት ላይወጣ ይችላል። ይህ በጓዳ የሚቀርን የጥበብ ክህሎት ወደ አደባባይ ለማዉጣት ተሰጥኦ ያላቸዉን ሰዎች ለማነሳሳት የታሰበ ፕሮግራም ነዉ።»

https://p.dw.com/p/2dXVS
Logo Äthiopien Veranstaltung Goethe Institut "Tibeb be Adebabay – The Art Side of Addis Abeba"

«ጥበብ በአደባባይ» በጎተ ተቋም

አዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ፈጠራዎች እና አዳዲስ ሃሳቦች የሚፈልቁባት ዉብ ከተማ ናት። «ጥበብ በአደባባይ»  በከተማዋ ሕዝብ በብዛት በሚገኝባቸዉ መንገዶችና አደባባዮች የተለዩ ጥበባዊ ክንዉን በማካሄድ መድረክ ያላገኙ፤ ነገር ግን እምቅ ችሎታ ያላቸዉን የከተማዋን  ነዋሪዎችም ያሳትፋል ይላል ባለፈዉ ሳምንት መገባደጃ የጀርመኑ ጎተ ተቋም በተለያየ ዘርፍ ላይ ከተሰማሩ የኪነ-ጥበብ ባለሞያዎች ጋር የጀመረዉና ለሦስት ሳምንታት የሚዘልቀዉ ዝግጅት።

Äthiopien Veranstaltung Goethe Institut "Tibeb be Adebabay – The Art Side of Addis Abeba"
ምስል Goethe Institut/Maheder Haileselassie

በአዲስ አበባ የሚገኘዉ የጀርመኑ የጎተ ተቋም በ 10 የተለያዩ የጥበብ ዘርፎች ላይ የሚሰሩ  ባለሞያዎችን በመደገፍ ባህላዊ እንቅስቃሴ ጀምሮአል። «ጥበብ በአደባባይ» የተሰኘዉ በአዲስ አበባ ከተማ የጀመረዉ ባህላዊ ክንዉን ምንድን ነዉ? 

 

በአዲስ አበባ የሚገኘዉ የጀርመኑ የጎተ ተቋም አስር የተለያዩ የጥበብ ዘርፍ ባለሞያዎችን በማሰባሰብ እና በከተማዋ ሕዝብ በርከት ብሎ በሚገኝባቸዉ አደባባዮች ላይ ሞያቸዉን እንዲያሳዩ ብሎም መድረክ ያላገኙ የጥበብ ሰዎች እንዲሳተፉ «ጥበብ በአደባባይ» የተሰኘ ዝግጅትን በመክፈት የተለያዩ አዳዲስ ጥበባዊ ሃሳቦችን እያሰባሰበም ይገኛል። የሙዚቃ ባለሞያዉና በአዲስ አበባ የጃዝ አንባ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና መምህር ዩናስ ጌታቸዉ ጎተ ተቋም ባነሳሳዉ እና ባለፈዉ ሳምንት አርብ የጀመረዉ « የጥበብ በአደባባይ» ፕሮጀክት ላይ ተሳታፊ ነዉ።

Äthiopien Veranstaltung Goethe Institut "Tibeb be Adebabay – The Art Side of Addis Abeba"
ምስል Goethe Institut/Maheder Haileselassie

«ዝግጅቱ ጥበብ በአደባባይ የሚል ነዉ። ብዙ ጊዜ ጥበብ በጓዳችን ብቻ ነዉ ያለዉ። ለምሳሌ አንድ ሰዉ የስዕል ተሰጥኦ ይኖረዉና ይጦት አደባባይ አይወጣም፤ የሙዚቃ ተሰጥኦ ይኖረዉና ይዞት አይወጣም፤ እግዚአብሄር አድሎት የሆነ ትምህርት ቤት ከገባ ፤ የትምህርት ቤት ደጁን ያየዋል እንጂ ብዙ ጊዜ በጓዳ ነዉ የሚቀረዉ። ይህ በጓዳ የሚቀርን ነገር ወደ አደባባይ ለማዉጣት ተሰጥኦ ያላቸዉን ሰዎች ለማነሳሳት፤ የማይሞክሩትን ለማስሞከር የታሰበ ፕሮግራም ነዉ። ጎተ ተቋም ይህንን ፕሮግራም ሲያዘጋጅ ጃዝ አንባ የሙዚቃ ትምህርት ቤት የወሰደዉ ሃላፊነት ሙዚቃን ማስተማር ማሳየት ሙዚቃን ለሦስተኛ ሰዉ ማለት አድማጩ፤ አድማጭ ብቻ ከሚሆን ተሳታፊ እንዲሆን ለማድረግ ታስቦ የሚንቀሳቀስ ፕሮጀክት ነዉ። እስካሁን በነበረን ዝግጅት ያደረግነዉ ፤ የኛ ተማሪዎች መሳሪያቸዉን ይዘዉ ወጡ ፤ ሙዚቃ ተጫወትን ሙዚቃ ሲሰማ ሰዉ ተገልብጦ መጣ፤ ከዝያ ጥበብ በአደባባይ የሚለዉን ዝግጅት አላማ ነግረናቸዉ፤ ሙዚቃን የሚሞክሩ ልጆች እየጋበዝንና ከኛ ጋር ተቀላቅለዉ እንዲጫወቱ እያደረግን አንዳንድ ነገሮችን አስተማርን ፤ በጣም ብዙ ሰዉ ነበር ወደኛ ጋር የመጣዉ ወደ አራት ሰዓት ያህል አደባባዩን ጥለን መሄድ አልቻልንም ነበር። እና በዚህ ዝግጅት ላይ ከመቶ በላይ ሙዚቃን መማር የሚፈልጉ ሰዎችን አግኝቼ ስም ዝርዝር ፅፊ ነዉ የወጣሁት።

 

ጎተ ተቋም ትልቅ ድጋፍ እያደረገ እንደሆነ የገለፁት አቶ ዮናስ ጌታቸዉ «ጥበብ በአደባባይ» ፕሮጀክት ላይ ሸቀጥ ሳይሆን ጥበብን የምንሸጥባት የምትገርም ትንሽ ሱቅ አዘጋጅቶል ሲሉ ገልፀዋል። «ጎተ ተቋም በጣም የምትገርም ትንሽ ሱቅ አዘጋጅቶልናል፤ በሱቅዋ ላይ የጎተ ዓርማ ተለጥፎባታል። ብዙ ጊዜ ሱቅ ሲባል አንድ ቦታ ሆኖ እዝያዉ ቦታ ላይ ነዉ የሚሰራዉ። ከጎተ ተቋም ያገኘናት ሱቅ ግን የምትንቀሳቀስ ናት ተጣጥፋ ትነሳለች። አንዴ ፒያሳ ናት፤ አንዴ መርካቶ ናት፤ አንዴ መገናኛ ናት፤ አንዴ መስቀል አደባባይ ናት፤ ትንቀሳቀሳለች። ተንቀሳቅሳ ግን ሸቀጥን ሳይሆን የምትነግደዉ ጥበብን ነዉ። እዉቀቱ ኖርዋቸዉ ፍላጎቱ ኖርዋቸዉ ፤ ምንም መስራት ያልቻሉትን ሰዎች ወደ መቻል እንዲመጡ የሚያደርግ የሚያነሳሳ ነገር ለማድረግ ነዉ። ጎተ በመጀመርያ ፈቃድ በማዉጣት ብዙ ርምጃዎችን ከሄደ  በኋላ ነዉ እኛን የጋበዘን። እና ጎተ ተቋም በቀደደልን መስመር መሰረት ፕሮግራሙን ተከትለን ዝግጅታችን እያቀረብን ነዉ። እናም ዉጤታማ ነገር በመጀመርያዉ ቀን አይተናል።»        

Äthiopien Veranstaltung Goethe Institut "Tibeb be Adebabay – The Art Side of Addis Abeba"
ምስል Goethe Institut/Maheder Haileselassie

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘዉ የጀርመኑ ጎተ ተቋም ለአለፉት 55 ዓመታት በተለያዩ ጥበባዊና ባህል ነክ ጉዳዮች ላይ እየሰራ እንደሆን የተናገሩት የድርጅቱ  ፕሮግራም አስተባባሪ ወ/ሮ ተናኘ ታደሰ እንደሚሉት እስከ ዛሬ ተቋሙ የሚያዘጋጃቸዉን የተለያዩ ክንዉኖች ተመልካችም ሆነ ተሳታፊ ተቋሙ ዉስጥ በመምጣት ነበር የሚያከናዉነዉ ፤

Äthiopien Veranstaltung Goethe Institut "Tibeb be Adebabay – The Art Side of Addis Abeba"
ምስል Goethe Institut/Maheder Haileselassie

«ከተማዋ ዉስጥ ሊዳረሱ በሚችሉባቸዉ ቦታዎች ለምን የጥበብ መድረክ አናዘጋጅም በሚል ነዉ ሃሳቡ የመጣዉ። እና አርክቴክት ፋሲል ጊዮርጊስ በ 2005 ዓ,ም ፈረንሳይ ላይ ባዘጋጁት አንዲት ትንሽ ኤግዚቢሽን ላይ፤ አንዲት ከብረት የምትሰራ ኪዮስክ አዘጋጅተዉ ነበር። ይህችን አይነት ኪዮስ ተጠቅመን የጥበብ ባለሞያዎቹ ክህሎታቸዉን ለምን አያሳዩም፤ ሕዝቡም ጥበብ ምን እንደሆነ ለምን አያይም በሚል ነዉ። ሙዚቃም ፊልም ፎቶግራፍም ፤ ስዕልም ሥነ-ጽሑፍም ጥበብ ነዉ፤ ሕዝቡ ለምን ከባለሞያዎቹ ጋር አይሳተፍም በሚል ተነሳሽነት ነዉ ይህ ዝግጅት ተግባራዊ ለመሆን የበቃዉ።        

አርክቴክቸርና የከተማ ፕላን በሚለዉ ዘርፍ ስር  የማ አርቲክቴክቸርና ከቤት እስከ ከተማ የተሰኘዉ የራድዮ ፕሮግራም በጋራ የከተማ ሚዛን ልኬት እና መጠን በሚል ሱቅ አዘጋጅተናል ይህ ሱቅም ሦስት አገልግሎቶችን ይሰጣል ያለን በሸገር ኤፍ ኤም ከቤት እስከ ከተማ የተሰኘ ሳምንታዊ የራድዮ ፕሮግራም አዘጋጅና በግል አማካሪ ድርጅት ዉስጥ የሚሰራዉ አርክቴክት ማኅደር ገብረመድህን፤ « ጥበብ በአደባባይ » በተሰኘዉ ዝግጅት ላይ ያለዉ ሱቅ አንደኛዉ አገልግሎት ከተማዉ የእርሶ ነዉ ይገንቡት ይላል። ሰዎች ከከተማዋ ጋር ያላቸዉን ግንኙነት በአንድ አማራጭ ለማሳየት የሚረዳ ነዉ።… ሁለተኛዉ ቁመቶ ስንት ነዉ ነዉ የሚለዉ። ይህ የአገራችን እስኬል ለማወቅ ረዳል ተብሎ የታሰበ ነዉ። ....»

Äthiopien Veranstaltung Goethe Institut "Tibeb be Adebabay – The Art Side of Addis Abeba"
ምስል Goethe Institut/Maheder Haileselassie

ማኅደር በመቀጠል ሦስተኛዉ አገልግሎት ምናባዊ ጉዞ ይባላል ሰዎች በተምኔታዊ መንጽር የተለያየ ቦታዎችን እንዲያዩ ከስኬል ጋር ያለንን ግንኙነት ለመፈተሽ ነዉ ሲል ገልፆአል።   

ሠዓሊ ሙሉጌታ ገብረኪዳን የጀርመኑ ጎተ ተቋም በነደፈዉ «ጥበብ በአደባባይ»  በተሰኘዉ ፕሮጀክት ተሳታፊ ነዉ። አደባባይ ይዞት በወጣም ሱቅ የስዕል በቀለም ቅብ ዘርፍ በተለይ ወጣትና ሕጻናት ላይ የተኮረ እንደሆን ገልፆአል። 

Äthiopien Veranstaltung Goethe Institut "Tibeb be Adebabay – The Art Side of Addis Abeba"
ምስል Goethe Institut/Maheder Haileselassie

ነገ አንደኛ ሳምንቱን በሚይዘዉ «ጥበብ በአደባባይ» የፊልም ሥራ ባለሞያዎች ስለፊልም ስራ፤ ለፊልም ሥራ የሚያስፈልጉትን ነገሮች በዚሁ መድረክ እንደሚያስተምሩ ብሎም እንደሚያሳትፉ በጎተ ተቋም የፕሮግራም አስተባባሪ ወ/ሮ ተናኘ ታደሰ ተናግረዋል።    

አዲስ አበባ ከተማ በሚገኘዉ በጀርመኑ ጎተ ተቋም ድጋፍ ግንቦት 11 የጀመረዉ «ጥበብ በአደባባይ» ዝግጅት  እስከ ፊታችን ሰኔ ሁለት ድረስ ይቀጥላል።  በ 10 የተለያዩ የጥበብ ዘርፎች ለሦስት ሳምንታት በአደባባ የተካሄደዉ የጥበብ ዓዉደ ርዕይ በፎቶ በፊልም እንዲሁም በመጽሐፍ አልያም በመጽሔት መልክ በኢግዚቢሽን መልክ ከእሁድ ሰኔ ሦስት ጀምሮ በጎተ ተቋም ቅፅር ጊቢ በእግዚቢሽን መልክ ለተመልካች እንደሚቀርብ በጎተ ተቋም የፕሮግራም አስተባባሪ ወ/ሮ ተናኘ ታደሰ ገልፀዉልናል።  ቃለ-ምልልስ የሰጡን ባለሞያዎች በማመስገን ሙሉዉን ጥንቅር የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ሙሉዉን ቅንብሩን እንዲያደምጡ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ