1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጥንታዊ የዓረብኛ ሥነ-ፅሁፎች በኢትዮጵያ

ሐሙስ፣ መጋቢት 18 2006

ባለፈዉ ሰምወን በኢትዮጵያንና በአካባቢዋ የሚገኙ ሃገራትን የእሥልምና ሥነ-ፅሁፍ ይዘትንና ታሪካዊ ፋይዳዉን የሚቃኝ አንድ ዓለም አቀፍ ጥናታዊ ጉባኤ አዲስ አበባ ዉስጥ መካሔዱ ይታወሳል። በዚህ ጉባኤ የእሥልምና ሥነ-ፅሁፍ በምሥራቅ አፍሪቃ ዉስጥ በሚነገሩ በተለያዩ ቋንቋዎች ለረጅም ጊዜ የተለያዩ አገልግሎቶች ሲስጥ እንደነበር፤

https://p.dw.com/p/1BWZt
Islamische Handschriften am Horn von Afrika
ምስል Dr. Andreas Wetter

ጥናቱን የሚያካሂዱት ምሁራን በአቀረቡት የጥናት ፅሁፋቸዉ አሳይተዋል። በዚህ ዝግጅታችን አዲስ አበባ ላይ ለሁለት ቀናት ስለተካሄደዉ የምስራቅ አፍሪቃ ጥንታዊ የእስልምና የእጅ ሥነ-ፅሁፎች ዓለማቀፍ ጉባኤ በተለይም በኢትዮጵያ ስለሚገኙት ጥንታዊ የአረብኛ ፅሁፎችና ታሪካዊ ፋይዳዎችን በተመለከተ ምሁራንን አነጋግረን ቅንብር ይዘናል።
ባለፈዉ ሰምወን የፈረንሳይ የኢትዮጵያ ጉዳይ ጥናት ተቋም ከኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ጋር በጋራ ባዘጋጁት ጉባኤ ላይ በምሥራቅ አፍሪቃ ሙሥሊሞችና በእሥልምና ሥነ-ፅሁፍ ላይ ጥናት ያደረጉ የተለያዩ ሐገራት ምሁራን ጥናታዊ ፅሁፋቸዉን አቅርበዋል። የጥናት ፅሁፋቸዉን ካቀረቡት ምዕራባዉያን መካከል በኢትዮPጵያ ቋንቋዎች ላይ ጥናት የሚደ,ርጉ ጀርመናዉያን እና ፈረንሳዉያን የተገኙ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ በአፍሪቃዉ ቀንድ እና በምዕራብ አፍሪቃ የተገኙ ጥንታዊ እስላም ሥነ-ፅሁፎች በሃገራቱ ዉስጥ ተመሳሳይ ታሪካዊ መረጃን እንዳሚያሳዩ ተነግሮአል። በኣዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ዉስጥ በምርምር ላይ የሚገኙት ዶክተር ከማል አብዱልዋሃብ፤ በኢትዮጵያ የመጀመርያዉ እስልምና እና የሙስሊሞች ጥናት በ1930ዎቹ መጀመሩን ገልፀዋል።
ቀደም ባሉት ዓመታት ስለሙስሊም የሚወጡ የጥናት ፅሁፎች የታሪክና የባህል አንድ ምሶሶ መሆናቸዉን ታሳቢ ያደረጉ አልነበሩም የሚሉት ዶክተር ከማል በአሁኑ ግዜ፤ በኢትዮጵያ የእሥልምና ሥነ-ፅሁፍን እና ታሪካዊ ይዘቱን የሚያጠና ተቋም መከፈቱን ያስረዳሉ።
በኢትዮጵያዉስጥ የተገኙት ጥንታዊ የዓረበኛ ፅሁፎች ሃይማኖታዊ ይዘት ቢኖራቸዉም፤ የተለያዩ ማህበራዊ እና ታሪካዊ ጉዳዮችንም ያዘሉ እንደሆኑ የሚገልጹት እና በአዲስ አበባ ለሁለት ቀናት በተካሄደዉ ጉባኤ ላይ የጥናት ፅሁፋቸዉን ያቀረቡት በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ቋሚ ባልደረባ አቶ አህመድ ዘካርያ፤ በጥንታዊ የፅሁፍ መረጃ ቅርስ ኢትዮጵያ ከአፍሪቃ ቀደምቱን ቦታ ይዛ እንደምትገኝ ተናግረዋል።
እስልምናን እና የዓረብኛ ሥነ -ፅሁፎችን አስመልክቶ በቋንቋ ጥናት ተቋም ስር የፊሎሎጂ ትምህርት ክፍል በግእዝና በዓረብኛ ቋንቋ የተፃፉ ሃገራዊ ጽሁፎች ላይ ጥናት እንደሚካሄድ የሚናገሩት፤ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ፤ በምርምር ስራ ላይ የሚገኙት ዶክተር ከማል አብዱልዋሃብ፤ የትምህርት ክፍሉ በተለይ ከ 2004 ዓ,ም ጀምሮ በኢትዮጵያ የተገኙ ጥንታዊ የዓረብኛ ጽሁፎች ላይ በከፍተኛ ደረጃ ጥናት መካሄዱን ገልፀዋል።
ዓረበኛ ቋንቋን ከእስልምና ሐይማኖት ጋር ብቻ ማያያዝ የለብንም የሚሉት ዶክተር ከማል፤ ዓረብኛ በማህበረሰባዊ ጉዳዮችና በኦርቶዶክስ እምነትም ብዙ አስተዋፅኦን ያደረገ እንደሆን ተዓምረ ማርያምን ምሳሌ በመጥቀስ ተናግረዋል። በተለይ ሐረር ከተማ የተገኙ መዛግብትና መፃሐፍት የምሥራቅ አፍሪቃዉ ጥንታዊዉ የሙስሊሞች ሥልጣኔ ከዝነኛዋ በምዕራብ አፍሪቃዊትዋ ከማሊ ከተማ ከቲምቡክቱ ሥልጣኔ ጋር ታሪካዊ ትስስር እንዳለዉ በአዲስ አበባዉ ጉባኤ ላይ መገለፁን የሚናገሩት በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ቋሚ ባልደረባ አቶ አህመድ ዘካርያ፤ እስከዛሪ አፍሪቃ በሥነ- ፅሁፍ ደሃናት የሚለዉን አመለካከት ቲምቡክቱ ላይ የሚገኘዉ እጅግ ጥንታዊዉ የዓረበኛ ፅሁፍ ዉድቅ ያደርገዋል። «አጀሚ» የሚል መጠርያ ስላለዉ የተለያዩ ቋንቋዎችን በአረብኛ ፊደል አፃፃፍ ዘዴ፤ እንዲሁም በኢትዮጵያ ስለ አረብኛ ፅሁፍ ጥንታዊ ቅርስ ሃብትና አያያዛቸዉን በተመለከተ ሰፊ ማብራርያ የሰጡንን ይዘን በሁለተኛ ክፍል ዝግጅት እንቀርባለን። ሙሉዉን ዝግጅት የድምፅ ማድመጫዉን በመጫን ይከታተሉ!
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሃመድ

Islamische Handschriften am Horn von Afrika
ምስል Dr. Andreas Wetter
Islamische Handschriften am Horn von Afrika
ምስል Dr. Andreas Wetter