1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

"በኢትዮጵያ ኅልውና ላይ አንደራደርም" የፀሐይ አሳታሚ መሥራች አቶ ኤልያስ ወንድሙ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 8 2010

መቀመጫውን በአሜሪካን ያደረገው ፀሐይ አሳታሚ የተቋቋመበትን 20ኛ ዓመት እያከበረ ነው። ለ20 ዓመታት በዘለቀ ሥራው 150 ገደማ መፃሕፍትን አሳትሞ ለገበያ አቅርቧል። ኢትዮጵያን የተመለከቱ "የማመሳከሪያ መፃሕፍት ማጣት" የወለደው ፀሐይ አሳታሚ በተመሰረተበት አገር የአፍሪቃ አሜሪካውያንን ጉዳይ የተመለከቱትን ጭምር ለአንባብያን ያደርሳል።

https://p.dw.com/p/2m7Dr
Temsalet Phenomenal Ethiopian women a book published by TSEHAI Publishers
ምስል TSEHAI Publishers

"በኢትዮጵያ ኅልውና ላይ አንደራደርም" አቶ ኤልያስ ወንድሙ

ስለ ኢትዮጵያ ያጠኑት የዶናልድ ሌቪን፣ክላውድ ሰመር (ዶ/ር)፣ አምባሳደር ዴቪድ ሺን ሥራዎችን ለንባብ ያበቃው ፀሐይ አሳታሚ ከተቋቋመ 20 አመታት ሞላው።የጸሐፌ-ተውኔት እና ገጣሚ ጸጋዬ ገብረመድህን የግል ማስታወሻ፣ የደበበ እሸቱ የትርጉም ሥራ፣ የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ እና የፎቶግራፍ ባለሙያዋ አይዳ ሙሉነሕ ሥራዎች ለኅትመት የበቁት በዚሁ ተቋም በኩል ነው።

የነገሥታቱን ታሪኮች፤ የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ፤አብዮት እና ኋላም በፖለቲካው መስክ በተለያየ ፅንፍ ቆመው የነበሩትን ኃይሎችን የተመለከቱ ሥራዎችም ባለፉት 20 ዓመታት በፀሐይ አሳታሚ በኩል ለአንባብያን ደርሰዋል። ቁጥራቸው ወደ 150 ገደማ ደርሷል።

Books published by TSEHAI Publishers
ምስል TSEHAI Publishers

በሎስ አንጀለስ ከተማ የሎዮላ ሜሪማውንት ዩኒቨርሲቲ የሚኘውን ፀሐይ አሳታሚ ያቋቋሙት አቶ ኤልያስ ወንድሙ ይባላሉ። በሙያቸው ጋዜጠኛ ነበሩ። "ለመቅረት አስቤ አልነበረም ካገሬ የወጣሁት። ድንገት እንደ ወጣሁ ነው የቀረሁት። በዛ ወቅት ስለ አገሬ ማወቅ የምፈልገውን ነገር፤ ማንበብ የምፈልገውን ራሴ አላገኘሁም። ለአዲሶቹ ጓደኞቼ እና ጎረቤቶቼ ወይም የሥራ ባልደረቦቼ ላስረዳ ሞክሬ ያንን በቅጡ ሊያሳይልኝ የሚችል ማመሳከሬ መፃሕፍቶችን ማግኘት አቃተኝ።" የሚሉት አቶ ኤልያስ ማጣት አሳታሚ ድርጅታቸውን ለማቋቋም ከገፋፏቸው ምክንያቶች አንዱ ነው።

 

አቶ ኤልያስ እንደሚሉት "ቁጥር ሥፍር የሌለው የተሰደደው የተማረ ኃይል እና የኢትዮጵያ ታሪክን የሚያውቁ፤ለኢትዮጵያ የለፉ ሰዎች በስደት ላይ እያሉ ታሪካቸውን የሚያሳትምላቸው ወይም የሚረዳቸው ጠፍቶ ባክነው ቀርተው ነበረ። ያንን ለማስተካከል እኔን የገጠመኝ ችግር የሚቀጥለው ትውልድ እንዳይገጥመው" ማድረግ ለፀሐይ አሳታሚ መጠንሰስ ሁለተኛው ምክንያት ነው።

ክትፎ ቤት ወይስ መፃሕፍት አሳታሚ

አቶ ኤልያስ ለ20 ዓመታት በዘለቀው የአሳታሚነት ሥራቸው ከልሒቃን፣ የጥበብ ሰዎች፣የልቦለድ ጸኃፊያን፣ የቀድሞ ባለሥልጣናት፣ተቃዋሚ ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞች ጋር የመስራት እድል አግኝተዋል። ተቋማቸው ፀሐይ አሳታሚ ከሎዮላ ሜሪማውንት ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የአፍሪቃ አሜሪካውያንን የብዕር ሥራዎች ማሳተም ጀምረዋል። ስሙ ራሳቸውን ከባርነት ነፃው አውጥተው ለሌሎች በታገሉት ጥቁር እንስት ሐርየት ቱብማን የተሰየመ ነው።

አቶ ኤልያስ እንደሚሉት መፃሕፍት አሳትሞ ትርፍ የማግኘቱ ነገር እምብዛም አዋጪ አይደለም። ሎስ አንጀለስ ወደ ሚገኘው ቢሯቸው ብቅ ያለው ኤርትራዊው ጋዜጠኛ እና ጸሐፊ ተስፋዬ ገብረአብ በግል ጦማሩ "ከትርፍ አንጻር ኤልያስ ወንድሙ መጠጥ ቤት ወይም ቁርጥና ክትፎ ቤት ቢከፍት ያዋጣው ነበር" ሲል ከሐሳባቸው የሚገጥም አስተያየት አስፍሮ ነበር።

Elias Wondimu founder and head of TSEHAI Publishers
የፀሐይ አሳታሚ መሥራች አቶ ኤልያስ ወንድሙምስል TSEHAI Publishers

"አሜሪካን አገር ውስጥ ጥቁር አሳታሚዎች በቁጥር እንኳን ትንሽ ነን። አፍሪካዊ ደግሞ ቁጥራችን በጣም ያነሰ ነው። በማሳተም ሥራ ውስጥ እንደ ትግል አድርገኸው ወይም ደግሞ አስተዋፅዖ እያበረከትኩ ነው ብለህ ካላሰብከው በስተቀር መፅሐፍ ቸርችረህ ገንዘብ አታገኝም።ስለዚህ የቢዝነስ ስኬቱ ያን ያህል ፎቅ የሚያስገዛ አይደለም።" ይላሉ አቶ ኤልያስ። ቢሆንም  ከኢትዮጵያውያን ርዕሰ-ጉዳዮች ተሻግሮ ለአፍሪቃ አሜሪካውያኑ የተረፈው ፀሐይ አሳታሚ በገንዘብም ባይሆን ለኅብረተሰቡ በሚያበረክተው አስተዋፅዖ ሚትልቅ ስኬት ነው የሚል እምነት አላቸው።

ቀዳዳ የሚሸፍን መፅሐፍ ፍለጋ

የፀሐይ አሳታሚ መፃሕፍት በይዘት እና የኅትመት ጥራታቸው ተለይተው ይታወቃሉ። አቶ ኤልያስ አሁን በኢትዮጵያ የሚታየውን የታሪክ አረዳድ ልዩነት መፃሕፍት ይሞሉታል የሚል እምነት አላቸው።

"የኢትዮጵያ ታሪክ ብዙ ቀዳዳዎች አሉት። በታሪክ ስለማንግባባ ነው አሁን የምንጣላው። በታሪክ የማንግባባበት ምክንያት ደግሞ በዛ ሰዓት የተደረጉ ነገሮች በቅጡ ተመዝግበው ለሕዝቡ በቀላሉ ሊገኝ በሚችል ቦታ ላይ አይደለም ያሉት። ያንን ለመቀየር ነው ዋናው ዓላማችን።"

መፃሕፍት ለማሳተም ሲመርጡ የኢትዮጵያ ታሪክ አሉበት የሚሏቸውን ቀዳዳዎች መሙላት መቻላቸው አንድ መሥፈርት ነው።

የኢትዮጵያ ገበያ እና የፀሐይ አሳታሚ መፃህፍት

የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም፣የሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ እና የኮሎኔል ፍሥሐ ደሥታን መፃሕፍት በኢትዮጵያ ያሳተመው ይኸው ፀሐይ አሳታሚ ነበር። የሕውሓት መሥራቹ አቶ አረጋዊ በርኼ መፅሐፍ ታትሞ ወደ ገበያ የተሰራጨው በዚሁ ተቋም አማካኝነት ነው።

"አማርኛዎቹ የበለጠ ኢትዮጵያ ውስጥ ተነባቢነት አላቸው ስለሚባል ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ያሳተምናቸው። ሌሎቹንም ኢትዮጵያ ውስጥ የማሳተም ፍላጎት አለን። የኅትመቶቹ ጥራት ከአሳታሚ ድርጅቶቹ ጥሩ አድርገን እናሳትማለን ብለው ቃል የገቡልንን አይደለም ያደረጉት። ይኸ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ መፍትሔ የሚፈልግ ችግር ነው።"

"በኢትዮጵያ ኅልውና ላይ አንደራደርም"

Temsalet Phenomenal Ethiopian women a book published by TSEHAI Publishers
ምስል TSEHAI Publishers

የኢትዮጵያ የጽንፍ ፖለቲካ የፀሐይ አሳታሚን ሲገዳደር መታየቱ ግን አልቀረም። "ትግላችን" የሚል ርዕስ የተሰጠውን የጓድ መንግሥቱ ኃይለማርያም መፅሐፍ በኢንተርኔት በማሰራጨት በአሳታሚው ላይ ጉዳት ለማድረስ ተሞክሯል። ድርጊቱን የፈጸሙት ወገኖች ከፀሐይ አሳታሚ ፈቃድ አልነበራቸውም። ድርጊቱንም የተቃውሟቸው መገለጫ እንደሆነ ገልጠው ነበር። "ግራ ቀመስ ከሆንክ የቀኙ ያበሳጭሃል። እንደ ተቋም ግን ዛሬ የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ እኔ ላስተዳድረው እንጂ ስለ እኔ ፍላጎት አይደለም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ማወቅ ስላለበት ታሪክ ነው። አንዳንድ የማልደግፋቸውን ታሪኮች አሳትሜ አውቃለሁ" የሚሉት አቶ ኤልያስ "በኢትዮጵያ ኅልውና ላይ አንደራደርም" ሲሉ ያክላሉ።

በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ፀሐይ አሳታሚ ለገበያ ከሚያቀርባቸው መፃሕፍት መካከል በአፄ ምኒሊክ ላይ ያተኮረው በሁለት ቅፅ የተዘጋጀ ነው። ስደተኛውን ልዑል ልጅ ዓለማየሁን የተመለከተ ሌላ መጽሐፍም ዝግጅቱ መጠናቀቁን አቶ ኤልያስ ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም የታተሙትን መፃሕፍት ኪንድል በመሳሰሉ የዘመኑ የማንበቢያ ቁሶች ለማቅረብ ፀሐይ አሳታሚ ዝግጅት  አድርጓል።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ