1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፀረ ሽብር ህግ በኬንያ

ረቡዕ፣ ጳጉሜን 2 1997

በኬንያ የሚገኙ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ቡድኖች የአገሪቱ መንግስት ያረቀቀዉ ፀረ ሽብር ህግ አወዛጋቢና ሰብዓዊ መብቶችን ከግምት ያላስገባ ነዉ በሚል ስጋታቸዉን ገለፁ። በእነሱ እምነትም ኬንያ ይህን ህግ ለማፅደቅ የምትጥረዉ ሽብርን ለመዋጋት ያደረገችዉን እንቅስቃሴ አስመልክቶ ዩናይትድ ስቴትስና ብሪታንያ ያሰሙትን ቅሬታ ለማካካስ ይመስላል።

https://p.dw.com/p/E0jW

ሽብርን ለመርገጥ በሚል የረቀቀዉ ይህ ፀረ ሽብር ህግ ከሁለት ዓመት በፊት በኬንያ መንግስት ቀርቦ ተቃዉሞና ትችት ስላየለበት የተተወ ነበር።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ህጉ ለሽብርና ሽብርተኝነት በሰጠዉ አሻሚና ሰፊ ትንትናኔ፤ እንዲሁም በሽብር ድርጊት የተጠረጠረን ግለሰብ ለመፈለግና ለመያዝ ለሚመለከተዉ አካል በሰጠዉ ከፍተኛ ስልጣን እንደሚያሳስበዉ ገልጿል።
በዚህ ረቂቅ ፀረ ሽብር ህግ መሰረት ፖሊስ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰዎችን መያዝ፤ ማሰርና ምርመራ ማካሄድ ይችላል።
በተጨማሪም በምርመራና ጥያቄ ወቅት የህግ ዉክልና የማግኘት መብትን የሚነፍገዉን ይህን ህግ አግባብ አይደለም በማለት አዉግዟል አምነስቲ።
ዘገባዎች እንደጠቆሙት የኬንያ ባለስልጣናት ይህን ህግ እንደአዲስ ለማቅረብ የፈለጉት በቅርቡ የአገሪቱ ፍርድ ቤት ከሽብር ተግባር ጋር በተገናኘ ተይዘዉ የነበሩ ሰባት ሰዎች እንዲለቀቁ የወሰነዉን ተከትሎ ከዩናይትድ ስቴትስና እስራኤል ትችት ስለተሰነዘረበት ነዉ።
ሰባቱ ተከሳሾች በአዉሮፓዉያኑ 2002 ህዳር ወር የ16 ሰዎች ህይወት ከጠፋበት የኬንያ ሞምባሳ ከሚገኘዉ ንብረትነቱ የእስራኤላዊ ከሆነዉ ሆቴል ላይ ከደረሰዉ የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት ጋር በተገናኘ በቁጥጥር ስር የዋሉ ነበሩ።
በወቅቱም በተመሳሳይ ሁኔታ ከሞምባሳ አዉሮፕላን ማረፊያ የተነሳዉን የእስራኤል አዉሮፕላን በሚሳኤል ለመምታት ተሞክሮ እንደነበር አይዘነጋም።
ሌሎች ሶስት ሰዎችም ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተገናኘ ታስረዉ የነበረ ሲሆን ከመንግስት በኩል ጥፋተኛነታቸዉን የሚያረጋግጥ ማስረጃ መቅረብ ባለመቻሉ ባላፈዉ ጥር ወር ገደማ ተለቀዋል።
በኬንያ የሽብርተኞች ተግባር ሲፈጸም ይህ የመጀመሪያ አልነበረም። ከዚህ በፊት በ1990 ነሐሴ ወር ናይሮቢ በሚገኘዉ የአሜሪካ ኤምባሲ ቦምብ ፈንድቶ ከ250 ሰዎች በላይ አልቀዋል።
በተመሳሳይ ሁኔታም በታንዛንያ ዳሬሰላም የአሜሪካ ኤምባሲ ተመሳሳይ ጥቃት ደርሶበታል። በአሜሪካ ኤምባሲዎችም ሆነ በሞምባሳ የደረሰዉ ጥቃት ከአልቃይዳ ጋር የተገናኘ መሆኑ ነዉ የተዘገበዉ።
የብሪታንያ ባለስልጣናት ደግሞ የወጣዉ ህግ እንደዉም በቂ እንዳልሆነ ኬንያ ተረድታለች ባይናቸዉ። በኬንያ የብሪታንያ ምክትል አምባሳደር እንደገለፁት ሽብርን ለመዋጋት ኬንያ የምትወስደዉን እርምጃ በማጠናከር ለመርዳት አገራቸዉ ዝግጁ ናት።
ይህን አስመልክተዉም ያሁኑ የኬንያ መንግስት ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ እየተወያዩበት እንደሆነ በይፋ ተናግረዋል።
ብሪታንያም በቅርቡ የ50 ሰዎችን ህይወት ያጠፋ የሽብር ጥቃትና በሁለት ሳምንቱ ደግሞ ለመክሸፍ የበቃ የሽብር ሙከራ ተፈፅሞባታል።
በተለይ ደግሞ ከሁለተኛዉና ከከሸፈዉ የሽብር ጥቃት ሙከራ ጋር በተያያዘ በፖሊስ የተያዙት ሁለት ተጠርጣሪዎች አንደኛዉ ከሶማሊያ ሌላኛዉ ከኤርትራ በጥቅሉ ከምስራቅ አፍሪካ የመጡ መሆናቸዉ ጫናዉን ኬንያ ላይ ያሳደረ ይመስላል።
የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾቹን ያሰጋቸዉም የትችት ዉርጅብኝ የኬንያ መንግስትን በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚያስከትለዉን ችግር ሳያስተዉል ህጉን ባፋጣኝ እንዲያፀድቅ ሳያጣድፈዉ አልቀረም የሚል ነዉ።
ናይሮቢ የሚገኘዉ ሰዎችን ማሰቃየት የሚቃወም መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ተጠሪ ሙቡጉዋ ካባ እንደሚሉት ሊታረም የሚገባ ያሉትን ሃሳብ ለመንግስት አቅርበዉ ምላሽ እየጠበቁ ነዉ።
በእርምቱ መሰረት መንግስት አሻሽሎ የሚያወጣዉን ረቂቅ ህግ አንድ አንድ ተመልክተንም አጥጋቢ ካልሆነ ጩኸታችንን እንቀጥላለን ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ኬንያ፤ ታንዛኒያና ዑጋንዳ በጋራ በመሆን ናይሮቢ ላይ ሽብርን ለማስቆም መንቀሳቀስ ጀምረዋል።
ይህ መልሶ ሽብርን የማጥቃት የጋራ ዘመቻም ከተለያዩ መንግስታዊ መስሪያ ቤቶች የሚመረጡ በስለላ ተግባር የሚሰማሩ ከ150 ሰዎች በላይ የሚሳተፉበት ይሆናል።