1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፆታ የማይለየዉ የጡት ካንሰር

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 16 2008

በየዓመቱስለጡት ጥቅምት ወር ካንሰር ግንዛቤ የማስጨበጫ እንቅስቃሴዎች በተለያዩ ሃገራት ይካሄዳሉ። አመጋገብ ላይ ጥንቃቄ ከማድረግ አንስቶ የሰዉነት እንቅስቃሴ ማዘዉተር የትኛዉንም የአካል ክፍል ከሚያጠቃ ካንሰር ለመከላከል የሚረዳ ተቀዳሚ ርምጃ መሆኑን ሃኪሞች ይመክራሉ።

https://p.dw.com/p/1Gv3Y
Gesundheit Gesundheitswesen Medizin Früherkennung Brustkrebs
ምስል Fotolia/Forgiss

ፆታ የማይለየዉ የጡት ካንሰር

ኢትዮጵያ ዉስጥ በሚካሄደዉ የካንሰር ምርመራ የጡት ካንሰር ተጠቂዎች ቁጥር መጨመሩን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ከሌሎች ሃገራት አኳያ ሲታይም የጡት ካንሰር ኢትዮጵያ ዉስጥ በወንዶች ላይ ከፍ ማለቱንም መረጃ ይጠቅሳሉ። በሌላዉ ዓለም እድሜ ከገፋ በኋላ የሚታየዉ የጡት ካንሰር ኢትዮጵያ ዉስጥ አቀድሞ እየታየ ነዉ።

የካንሰር ህክምና በተስፋፋባቸዉ ሃገራት የተለያዩ የህክምና ዓይነቶች ቢኖሩም የህክምና ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆኑ የህክምና መድህን ወይም ኢንሹራንስ ኩባንያዎችም ሰዎች ቅድመ ምርመራ እና የመከላከል ጥንቃቄዎች ላይ እንዲያተኩሩ አዘዉትረዉ ይወተዉታሉ። በተለይ ካንሰርን ጨምሮ ምንም ዓይነት መድኃኒት አልተገኘላቸዉም ለሚባሉት በሽታዎች። የጡት ካንሰርን ስር ከመስደዱ አስቀድሞ ለማከምና ለማዳን እንዲቻልም ከቀላሉ ማለትም እያንዳንዱ ሰዉ ራሱን ከሚፈትሽበት የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራ ጀምሮ፤ ዘመናዊ የመመርመሪያ ቴክኒዎሎጂን ተጠቅሞ ያለበትን ደረጃ ማወቁ ሢሠራበት የኖረ ስልት ነዉ። በቅርቡ የወጡ ጥናቶች በሌላ በኩል ይህን የቴክኒዎሎጂ እገዛ ጥያቄ ላይ እየጣሉት ነዉ። ብሪታኒያ ዉስጥ በየዓመቱ ከሁለት ሚሊየን የሚበልጡ ሴቶች ማሞግራም በተሰኘዉ መሣሪያ የጡት ራጅ ይነሳሉ። በዘመናዊዉ መሣሪያ የሚካሄደዉ ምርመራ ዓላማዉ የሰዉ ሕይወት ለማትረፍ ቢሆንም በሚገኘዉ የሀሰት ዉጤት ምክንያት በርካቶች ለለናሙና ምርመራ ቆዶ ጥገና አካሂደዉ ከካንሰር ነፃ መሆናቸዉ ይረጋገጣል፤ አንዳንዶች ደግሞ በቀሪ የሕይወት ዘመናቸዉ ምንም ዓይነት የጤና እክል በማያስከትል በትንሽ እብጠት ምክንያት ለተመሳሳይ ቀዶ ጥገና መዳረጋቸዉ መነጋገሪያ ሆኗል። በዚህ ምክንያትም ለጡት ካንሰር ጥንቃቄ አስቀድመዉ ከሚከናወኑ ቅድመ ምርመራዎች መካከል በዋናነት የሚታወቀዉ ማሞግራም የተሰኘዉ የምርመራ ቴክኒክ ለረዥም ዓመታት እንዳልተወደሰ በያዝነዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት የሚወጡ ጥናቶችና ዘገባዎች ይተቹት ጀምረዋል። የተሳሳተ መረጃ አቀባዩ የምርመራ ቴክኒኩ ይሁን በማሞግራም የተነሳዉን የሚያነብቡ ባለሙያዎች ግድፈት ግልፅ ባይሆንም ብዙዎች በዚህ መሳሪያ በተደረገላቸዉ ምርመራ ዉጤት ምክንያት እስከቀዶ ጥገና መድረሳቸዉ ምርመራዉ ይደረግ፣ በየትኛዉ ዕድሜ ክልልስ የሚለዉም ማከራከር ይዟል። የአሜሪካን የካንሰር ማኅበረሰብ ለቅድመ ጥንቃቄ የሚካሄደዉ የማሞግራም ምርመራ ከ40 ዓመት ጀምሮ መደረግ አለበት ሲል ይመክር ነበር። በቅርቡ ግን ሁሉም ሴቶች ሳይሆኑ በተለያዩ ምክንያቶች የጡት ካንሰር በአማካኝ ሊይዛቸዉ ይችላል ተብለዉ የሚገመቱት ብቻ ዕድሜያቸዉ ወደ45 ዓመት ከፍ ሲል በየዓመቱ ይህን ምርመራ ቢያካሂዱ፤ ከዚያም ከ55ዓመት በላይ የሆኑትም እንዲሁ በዓመት አንዴ ቢታዩ እንደሚሻል በይፋ ገልጿል። ይህን ምርመራ መተቸት የጀመሩት ባለሙያዎች እንደዉም ምርመራዉ ጨረር ያለበት በመሆኑ መዘዙ ከፍተኛ ነዉ በሚል ቀድሞ እድሜዋ የደረሰ ሴት ሁሉ እንድታደርገዉ አጥብቀዉ ይመክሩ የነበረዉን ምርመራ ወደጎን እያገለሉት ነዉ። በአዲስ አበባዉ ጥቁር አንበሳ ሃኪም ቤት የጨረር ህክምና ክፍል ኃላፊ ዶክተር ወንድማገኝ ጥግነንህም ይህንኑ ያጠናክራሉ።

Krebs Krebszelle Illustration Symbolbild
የካንሰር ሴልን የሚገልጽምስል Colourbox
Symbolbild Brustkrebsvorsorge
ማሞግራፊምስል picture alliance/CHROMORANGE

ዶክተር ወንድማገኝ እንደገለፁልን በጎርጎሪዮሳዊዉ 1998ዓ,ም ነዉ የካንሰር ህክምና ኢትዮጵያ ዉስጥ በይፋ የተጀመረዉ። እናም ከዚያን ጊዜ አንስቶ የካንሠር ታማሚዎች ቁጥር እየጨመረ ሄዷል። የተለያዩ የሰዉነት ክፍሎችን ከሚያጠቃዉ የካንሰር ዓይነት ደግሞ የጡት ካንሰር ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።

ክብደትን ከመቆጣጠር አኳያ የሰዉነት እንቅስቃሴ ማዘዉተር አጥብቆ የሚመከር አንድ መንገድ ነዉ። እንደዶክተር ወንድማገኝ ገለፃም በቀን ዉስጥ ቢያንስ ለ45 ደቂቃዎች ያህል የእግር ጉዞ ማድረጉ ለጡት ካንሰር ብቻ ሳይሆን የሌሎችን ተያያዥ በሽታዎችንም ስጋት ለመቀነስ ያስችላል ተብሎ ይገመታል። አንድ ሰዉ የጡት ካንሰር እንዳለዉ በምርመራ ከተረጋገጠ በኋላ የተለያዩ የህክምና ርዳታዎችን ሊያገኝ ይችላል። ኢትዮጵያ ዉስጥ የትኞቹ የህክምና አማራጮች ይኖራሉ ለሚለዉ ዶክተር ወንድማገኝ ያስረዳሉ፤

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ