1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፌስቡክ ያሸነፈው ክስ

ዓርብ፣ ግንቦት 25 2009

ልጃቸው የሞተችበትን ምክንያት ያላወቁ አንዲት እናት  ምክንያቱን ለማወቅ ይረዳ ይሆናል በሚል ፌስቡክ የልጃቸውን ገፅ እንዲከፍትላቸው ቢጠይቁም መሥሪያ ቤቱ ሳይተባበራቸው በመቅረቱ ይከሳሉ። ውሳኔው ግን ተስፋ እንዳደረጉት አልነበረም።

https://p.dw.com/p/2dzwY
Facebook unter der Lupe
ምስል picture-alliance/dpa/T. Hase

ፌስቡክ ያሸነፈው ክስ

እአአ በ 2012 ዓም ነበር አንዲት የ15 ዓመት ወጣት በርሊን ውስጥ በቀላል ባቡር ተገጭታ ህይወቷ ያለፈው። ልጅቷ ሆን ብላ ራሷን ታጥፋ ወይም ሳታስበው በአጋጣሚ ትገጭ እስካሁን ግልፅ አይደለም። ምናልባት ለዚህ ምላሽ ካገኘን በሚል ወላጆች የልጃቸውን የፌስቡክ ገፅ ከፍተው እንዲያዩ ፌስቡክን የሚስጥር ቁጥሯን (password) ቢጠይቁም ፌስቡክ ይከለልላቸዋል። ፌስቡክም የልጅቷን ገፅ ወደ « መታሰቢያ » ገፅነት ቀይሮ፤  ቤተሰብ እና ጓደኞች የተሰማቸውን ሀሳብ ገጿ ላይ መለዋወጥ ብቻ ፈቅዷል። ምንም እንኳን ሁኔታው አሳዛኝ ቢሆንም የሚስጥር ቁጥሩን ለማንም አሳልፎ እንደማይሰጥም ይገልፃል። በዚህ ያልተደሰቱት የልጅቱ ወላጆች ፌስቡክን  ይከሳሉ። ይሁንና ጉዳዩን የተመለከተው ችሎት ለፌስቡክ መብቱን ሰጥቷል። ለምን? ጉዳዩን የተመለከተው ፍርድ ቤት ቃል አቀባይ አኔተ ጋብርዬል፤ « ልጃቸው የሞተችበትን ምክንያት የማያውቁት ወላጆች በዚህ መንገድ ፍንጭ ማፈላለጋቸውን ፍርድ ቤቱ በሚገባ ይረዳል ነገር ግን በሌላ በኩል ፍርድ ቤቱ በህግ ይገደባል። እዚህ ጋር በርካታ ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ወሳኝ ነበሩ። ስለዚህ ውሳኔው ቀላል አልነበረም።»

Mark Zuckerberg
የፌስቡክ መስራች ማርክ ሱከርበርግምስል picture-alliance/dpa/P. Dasilva

ውሳኔውን የከበደው አንዱ ጉዳይ ወላጆች ልጃቸው ከሌሎች ሰዎች ጋር ምን እንደተፃፃፈች ማንበብ መቻላቸው ብቻ ሳይሆን፤ የሌሎችንም ማንነት ፌስቡክ አሳልፎ ስለሚሰጥ እና እነዚህ ከሟች ጋር በግል መልዕክት የተለዋወጡ ሰዎች መብታቸው የሚጥስ በመሆኑ ነው።  ስለሆነም ለሟች ወላጆች ለአምስት አመታት ያህል ያልተመለሰው ጥያቄ አሁንም ክፍት ሆኖ ይቆያል። ከሰው የተሸነፉት ወላጆች፤ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ እጅግ አዝነው ጉዳዩንም ለከፍተኛ ፍርድ ቤት የይግባኝ ማመልከቻ እንደሚያስገቡ ጠበቃቸው ገልፀዋል።

የሁለት ልጆች አባት የሆኑት አቶ ይበልጣል «የሆነው ነገር የሚያሳዝን እና እንደ ወላጅ የሟች ወላጆችን ምክንያት ፍለጋ የምረዳ ቢሆንም የፌስቡክ ውሳኔ ትክክል  ነው ይላሉ»።ምንም እንኳን እስካሁን ልጅ ባይኖረኝም ራሴን በሁለቱም ቦታ አድርጌ ስመለከተው ወላጆቹ የልጃቸውን የፌስቡክ ገጽ ማየቱ ቢቀርባቸው ይሻላል የሚሉት ደግሞ ባለትዳር የሆኑት ኃይለእየሱስ ናቸው። የሟች ወላጆች ሌላ ምን የተሻለ አማራጭ ነበራቸው? አሁንስ ምን ማድረግ ይችላሉ? ሳይንቲስት ዶክተር ታዬ በሚኖሩበት ኖርዌው ከዚህ ቀደም የተከሰተን አንድ ጉዳይ በምሳሌነት በማንሳት መፍትሄ ይሆናል የሚሉትን ገልጸውልናል።

Facebook Nutzer Symbolbild
ምስል picture-alliance/dpa/O. Berg

የ 15 ዓመቷ ጀርመናዊት በባቡር መገጨት እና መሞት የታየ እና የተረጋገጠ ነገር ቢሆንም፤ መስመሩን ጠብቆ በሚሄድ የከተማ ባቡር መገጨት በወላጆቿ በኩል ብቻ ሳይሆን ሰሚው  ዘንድም ጥያቄ ይፈጥራል። ይሁንና ለዚች ልጅ ወላጆች ብቻ ሳይሆን አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች በሞት ሲለዩዋቸው መሞታቸውን ማወቃቸው ብቻ ለህሊናቸው በቂ አይደለም። ይልቁንስ የበለጠ መረጃ ለማግኘት ይጥራሉ። ይህ ከምን የመነጨ ነው?። በአዲስ አበባ ዮኒቨርሲቲ የማህበራዊ ኑሮ ባለሙያ ( የሶሲዮሎጂ ተባባሪ ፕሮፌሰር)- የሆኑት ዶክተር የራስወርቅ አድማሴ ምክንያቱ እርማቸውን እንዲያወጡ እና ጥያቄያቸው እንዲመለስላቸው ስለሚረዳ ነው ይላሉ። በሟች እድሜ ክልል የሚገኙ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ወጣቶች ስለጉዳዩ ምን ያስባሉ?

የሁሉንም ሰፊ ምላሽ ከዚህ በታች በድምፅ ያገኛሉ።

ልደት አበበ

ሂሩት መለሰ