1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፎን ቫይሴከር 6 ተኛው የጀርመን ፕሬዝዳንት

ማክሰኞ፣ ጥር 26 2007

የቀድሞው የጀርመን ፕሬዝዳንት ሪቻርድ ፎን ቫይሴከር ባለፈው ቅዳሜ አርፈዋል ። ለ10 ዓመታት የጀርመን ፕሬዝዳንት የነበሩት የፎን ቫይሴከር ማንነት የዛሬው አውሮፓና ጀርመን ዝግጅታችን ትኩረት ነው ።

https://p.dw.com/p/1EV7Y
Bildergalerie Richard von Weizsäcker
ምስል imago stock&people

በጀርመን ለከፍተኛ የስልጣን እርከን የበቁና የህዝብን ፍቅር ያተረፉ መሪ ነበሩ ። ከዚያም አልፈው በዓለም ዙሪያ ለጀርመን በጎ ስም ያተረፉ ባለ ግርማ ሞገስ ርዕሰ ብሔርም ጭምር ፣ 6 ተኛው የጀርመን ፕሬዝዳንት ሪቻርድ ፎን ቫይሴከር ። ከሁሉ በላይ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ያበቃበት 40 ኛ ዓመት መታሰቢያ ላይ ያደረጉት ንግግር ምን ጊዜም በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ ክብርና ዝናን አጎናፅአቸው አልፏል ።ምናልባትም ይህ ንግግራቸው የዚያን ጊዜው የጀርመን ፕሬዝዳንት ፎን ቫይሴከር በስልጣን ዘመናቸው ካደረጉዋቸው ንግግሮች ደርዝ ያለው የተባለ ንግግር በመሆኑ ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል ። በናዚ ጀርመን ሽንፈት ላይ ጠንካራ ትችት የሰነዘረውን ይህን ንግግር ብዙዎች ማንበብ ብቻ በቂ አይደለም ፣መሰማትም ያለበት ነው ይላሉ ። በዓይነቱ የመጀመሪያ የተባለውን ፎን ቫይሴከር እጎአ ግንቦት 8 ፣1985 ያሰሙትን የጦርነቱን ማብቂያ 40 ኛ ዓመት መታሰቢያ ንግግር ለታሪክ ለማስቀመጥ ብዙዎች ከሩቅም ከቅርብም በየመፃህፍት ቤቱና በድምፅ መሸጫ ስፍራዎች ይጎርፉ ነበር ። ዝናው በሃገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ድንበርም በተሻገረው በዚህ ንግግራቸው ቫይትሴከር የሚሸፋፈነውን እውነታ በገልፅ አውጥተዋል ።
«ግንቦት 8 ለኛ ለጀርመናውያን የበዓል ቀን አይደለም ።በወቅቱ የነበሩት ሰዎች ትዝታዎች በጣም ግላዊ ሲሆን ተሞክሮአቸውም እጅግ የተለያዩ ናቸው ። አንዳንዶቹ ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል ።

Weizsäcker Wohnhaus Meisenstrasse 6 in Berlin Dahlem
ፎን ቫይትሴከር እጎአ በ1994 በበርሊን መኖሪያ ቤታቸውምስል ullstein bild - Weychardt

ሌሎቹ ደግሞ ቤት አልባ ነው የሆኑት ። አንዱ ነፃነት ሲጎናፀፍ ሌላው ደግሞ የእስር ጊዜውን ጀምራል ። ብዙዎች ለሊት የሚካሄዱ የቦምብ ድብደባዎች በመቆማቸው በህይወትም በመትረፋቸው ተደስተዋል ።ሌሎች ደግሞ አባት ሃገራቸው በገጠመው ከባድ ሽንፈት ቆሽታቸው አሯል ። የአንዳንድ ጀርመናውያን ምኞት ውሃ በልቶት ሲቀር ብዙዎች ደግሞ አዲስ ህይወት መጀመር ባስቻላቸው አጋጣሚ ረክተዋል ።»
የፎን ቫይትሴከር መፃኤ እድል የተደላደለው ገና ከልጅነት እድሜያቸው አንስቶ ነበር ። ፎን ቫይሴከር እጎአ ሚያዚያ 15 ፣ 1920 ነበር ከዲፕሎማት ቤተሰብ በደቡብ ጀርመንዋ በሽቱትጋርት ከተማ የተወለዱት። አባታቸው እርንስት ፎን ቫይሴከር በሂተለር ዘመነ መንግሥት እጎአ ከ1938 እስከ 1943 የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ነበሩ ። እስከ ሁለተኛው ዓለም ጦርነት ማብቂያ ድረስ ደግሞ በቫቲካን ዲፕሎማት ሆነው አገልግለዋል ። የዲፕሎማቱ ልጅ ወጣቱ ሪቻርድ እጅግ ከፍ ያለ ግምት የሚሰጠው የትምሕርት እድል አግኝቶ ነበር ያደገው ። ከልጅነት ህይወቱ አብዛኛውን ያሳለፈው በስዊትዘርላንድ ና በሌሎች የስካንድኔቭያን ሃገራት ነው ። በስዊዘርልንድዋ የባዝል ከተማ 4 ዓመት፣ በዴንማርክዋ ዋና ከተማ ኮፕንሃገን ሶስት ዓመት በኖርዌይዋ ኦስሎ 3 ዓመት እንዲሁም በስዊስዋ ቤርን 3 ዓመት ኖረዋል ። ወጣቱ ፎን ቫይሴከር በ17 ዓመቱ ወደ ብሪታኒያ በመሄድ በኦክስፎርዱ ቦልዮል ኮሌጅ ፍልስፍናና ታሪክ አጠና ።

Flash-Galerie Richard von Weizsäcker wird 90 mit Ernst von Weizsäcker
ፎን ቫይትሴከር ለአባታቸው ጥብቅና በቆሙበት ወቅትምስል cc

ይህንኑ ትምህርቱን በፈረንሳይም ቀጥሎ ነበር ። የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲጀመር ለጀርመን ጦር ተሰልፎ በአውሮፓ እየተዘዋወረ በወታደርነት ያገለገለው ፎን ቫይትሴከር በጀርመን ናዚ ጦር ውስጥ እስከ ሻምበል ማዕረግ ደርሷል ። ከሁለት ወንድሞች አንዱ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተሰልፈው ሲዋጉ ተገድለዋል ።ፎን ቫይትሴከር በ1945 እንደቆሰሉ ወደ ትውልድ ከተማቸው ሽቱትጋርት ተመለሱ ።ከጦርነቱ በኋላ የታሪክ ትምሕርታቸውን በጎቲንገን ቀጥለው ህግም አጠኑ። በህግ የዶክትሬት ዲግሪ አቸውን እ.ጎ.አ በ1950ያገኙት ቫይሴከር አባታቸው ተከሰው በቀረቡበት በኑርምበርጉ የናዚ ጀርመን የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ችሎት የአባታቸው ጠበቃ ረዳት ሆነው ሰርተዋል ።ችሎቱ በአባታቸውን ላይ የ7 ዓመት እሥራት ቢበይንም ከጊዜ በኋላ ወደ አምስት ዓመት ዝቅ ተደርጎላቸዋል ።እ.ጎ.አ በ1954 የጀርመን ክርስቲያን ዴሞክራቶች ህብረት ፓርቲ አባል የሆኑት ቫይትሴከር ከ1969 እስከ 1981 በጀርመን ፓርላማ የህዝብ እንደራሴ ነበሩ ። በ1974 ፓርቲያቸው ለፕሬዝዳንትነት ቢያጫቸውም በነፃ ዲሞክራቱ ፓርቲ በዋልተር ሼል ተሸነፉ ። ከ1979 እስከ 1981 ደግሞ የጀርመን ፓርላማ ምክትል ፕሬዝዳንት ነበሩ ።በኋላም ከ1981 እስከ 1984 የበርሊን ከተማ ከንቲባ ሆነው አገልግለዋል ። ፎን ቫይትሴከር በ1984 የፓርቲያቸውንና የያኔውን ተቃዋሚ ሶሻል ዲሞክራቶችን ይልተለመደ ድጋፍ አግኝተው ካርል ካርስተንን ተክተው በጀርመን ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ ።
«የተከበሩ ፕሬዝዳንት ምርጫውን ተቀብየዋለሁ ።»


ቫይትሴከር በፕሬዝዳንትነት ዘመናቸው በናዚ ጀርመን ወረራ ግፍ የተፈፀመባትን ፖላንድን ለመጀመሪያ ጊዜ የጎበኙ የምዕራብ ጀርመን መሪ ናቸው ። በዚሁ እጎአ በ1990 ባደረጉት የፖላንድ ጉብኝታቸው ወቅት የተዋሃደችው ጀርመን የምዕራብና የምስራቅ ድንበሮቻቸውን እንደምታከብር አረጋግጠዋል ። ግፈኛው የናዚ አገዛዝና አፋጣኝ ውድቀቱ በሪቻርድ ፎን ባይሴከር ላይ አሻራ ትቶ አልፏል ። ሪቻርድ ፎን ቫይሴከር ከዛሬ 29 ዓመት በፊት ያሰሙት ታዋቂ ንግግር በጀርመን ታሪክ አስከፊ የሚባለውንና ርሳቸውም የተሳተፉበትን የጦርነት ዘመን የሚያንፀባርቅ ነበር ።
«ግንቦት 8 የነፃነት ቀን ነው ። ሁላችንንም ኢሰብዓዊ ከሆነውከናዚ ጀርመን አገዛዝ ነፃ አውጥቶናል ። ከነፃነቱ ጋር ግንቦት 8 የጀመረውንና ከዚያም በኋላ ለብዙዎች የቀጠለውን ከባድ ስቃይ ማንም አይረሳውም ። ሆኖም የጦርነቱን ማብቃት ፣የስደት የመፈናቀል እና ነፃነት የማጣት ዋነኛ ምክንያት አድርገን መመልከት አይገባንም ። ከዚያ ይልቅ ምክንያቶቹ በአጀማመሩ እና ወደ ጦርነቱ ባመራው የአገዛዙ አነሳስ ላይ ነው ያሉት ። ስለዚህ እጎአ ግንቦት 8፣1945 እና ጥር 30 1933 ን መነጣጠል አንችልም ።»
ናዚ ጀርመኖች እጅ የሰጡበትንና ወደ ሥልጣን የወጡበትን ቀናት ነው ቫይሴከር በዚህ ንግግራቸው በአንድ መታየት ያለባቸው ናቸው ያሉት ። እጎአ ከ1984 እስከ 1994 ጀርመንን በፕሬዝዳንትነት የመሩት ቫይትሴከር በ10 ዓመት የፕሬዝዳንትነት ዘመናቸው ዋነኛ ትኩረታቸው ከምሥራቅ አውሮፓና ከእሥራኤል ጋር እርቀ ሰላም ማውረድ ላይ ነበር ። ያለፈውን ታሪክ ወደ ኋላ በማስቀረት ከነዚህ ህዝቦች ጋር አዲስ ግንኙነት መፍጠር እንደማይቻል ይልቁንም ያለፈውን ማስታወስና ማሰቡ ጠቃሚ መሆኑን ከጊዜ በኋላ ቫይትሴከር አምነዋል ።

Bundespräsident Richard von Weizsäcker mit Sohn
ፎን ቫይትሴከር ከልጃቸው ከፍሪትስ ፎን ቫይትሴከር ጋርምስል picture-alliance/Wolfgang Eilmes


«ያለፈውን የማስቀረት ጉዳይ አይደለም ።ያን ማንም ማድረግ አይቻለውም ።መቀየርም ሆነ እንዳልነበረ ማድረግ አይቻልም ።ሆኖም ባለፈው ታሪክ ላይ የዓይኑን የሚጨፍን የአሁኑን ወቅት የሚሳነው ነው የሚሆነው ። ያለፈን ኢሰብዓዊ ድርጊቶችን ማስታወስ የማይፈልግ እንደገና በአዲስ መልኩ ተመሳሳይ ድርጊት ከመፈፀም አይመለስም »
በርሳቸው ዘመን የበርሊኑ ግንብ ፈርሷል ። ለረዥም ጊዜ ተለያይተው የቆዩት ሁለቱ ጀርመኖች ተዋህደዋል ።የዲሞክራሲና የነፃነት ጠበቃ የሚባሉት ቫይትሴከር እጎአ በ1994 ከሥልጣን ከወረዱ በኋላም በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ ጉዳዮች በአማካሪነት የሚፈለጉ ሰው ነበሩ ። በስብዕናቸው እና ባለፈ ታሪካቸው ከምንም በላይ ደግሞ በዲፕሎማት ባህርያቸው የህዝብ ፍቅር የቸራቸው 6 ተኛው የጀርመን ፕሬዝዳንት ሪቻርድ ፎን ቫይሴከር ቁም ነገረኛ ና በደንብ የተማሩ ህዝብን በትክክል የሚወክሉ መሪ እንደነበሩ ብዙዎች ይመሰክሩላቸዋል ። ፎን ቫይትሴከር ባለፈው ቅዳሜ ማለፋቸው እንደተሰማ የአሁኑ የጀርመን ፕሬዝዳንት ዮአሂም ጋውክ ታላቅ ሰው አጣን ነበር ያሉትት ።
«ጀርመን በሃዘን ላይ ናት ።ሃገራችን አንድ ታላቅ ሰውና ከፍተኛ ተስጥኦ የነበራቸውን ርዕሰ ብሔር አጥታለች ። ሪቻርድ ፎን ቫይትሴከር ለፕሬዝዳንቱ ቢሮ ቋሚ ቅርጽ ሰጥተውታል ።በተፈጥሮአዊ ስጦታቸውና በተዓማኒነታቸው ፌደራል ጀርመን ሪፐብሊክን በውጭው ዓለም ወክለዋል ።በዓለም ዙሪያ ጀርመን ከዓለም ዴሞክራሲያዊ ሃገሮች ቤተሰብ መካከል እንድትገኝ ያበቁ ናቸው ።»
ፎን ቫይትሴከር እጎአ በ1953 ከመሰረቱት ትዳር ያፈሯቸው የ4 ልጆች አባት ነበሩ ።ከልጆቻቸው ሶስቱ የዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰሮች ሲሆኑ አንደኛው ጠበቃ ና ጋዜጠኛ ናቸው ። ባለፈው ቅዳሜ ያረፉት የ94 ዓመቱ ፎን ቫይትሴከር
የቀብር ስነ ስርዓት በሚቀጥለው ሳምንት ረቡዕ ይፈጸማል ።

Joachim Gauck Kondolenzbuch Richard von Weizsäcker 31.1.2015
ጋውክ የሃዘን መግለጫ ሲፅፉምስል picture-alliance/dpa/H. Hanschke

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ