1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዉጥረት በዲሞክራቲክ ኮንጎ።

ረቡዕ፣ መጋቢት 20 2009

የተመድ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ዉስጥ የተባባሰዉን የፖለቲካ ዉጥረትና የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲያጣሩ አሰማርቷቸዉ የተገደሉትን ባልደረቦቹን ጉዳይ ባስቸኳይ እንደሚያጣራ አስታወቀ። የሁለቱ የዉጭ ዜጎች አስከሬን ከሁለት ሳምንት ፍለጋ በኋላ ነዉ ትናንት መገኘቱ የተሰማዉ።

https://p.dw.com/p/2aGHQ
Kongo tödliche Proteste gegen Kabila
ምስል Reuters/T. Mukoya

Political instability in DRC - MP3-Stereo


በሀገሪቱ በተከሰተዉ ብጥብጥ ሳቢያ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ መምጣቱን የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እየገለጹ ናቸዉ። 
ማዕከላዊ አፍሪካዊቷ ሀገር ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ በጎርጎሮሳዊዉ ከታህሳስ 2015 ወዲህ  በጸረ መንግሥ ተቃዉሞ እየታመሰች ትገኛለች። ምክንያቱ ደግሞ አባታቸዉ ሎረን ካቢላ በመገደላቸዉ  በጎርጎሮሳዊዉ 2001 ወደ መንበረ መንግሥቱ የመጡት የአሁኑ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ካቢላ የሀገሪቱ ሕገ መንግስት ከሚፈቅደዉ ዉጭ ለፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር መፈለጋቸዉ ነዉ። ተቃዉሞዉ በአብዛኛወቹ የሀገሪቱ ክፍል የተካሄደ  ሲሆን ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ካቢላ ከስልጣን እንዲለቁ የሚጠይቅ ነዉ ።
በዚህም ምክንያት በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ብዙዎች ተገድለዋል በመቶች የሚቆጠሩም መታሠራቸዉ ይነገራል። በሀገሪቱ ይደርሳል የተባለዉን የሰብአዊ መብት ጥሰት ለማጣራት የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታዉ ምክር ቤት ልዑካኑን ወደ ሀገሪቱ ሲልክ ቆይቷል። አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ከኪንሻሳ እንደዘገበዉ ለዚሁ ተግባር የተላኩት ማይክል ሻርፕና ዛይዳ ካታላን ተገድለዉ  ተገኝተዋል። 
ሟቾቹ ከተያዘዉ ወር አጋማሽ ጀምሮ አብረዋቸዉ ከነበሩ 4 የኮንጎ ዜጎች ጋር የደረሱበት ጠፍቶ ነዉ የቆየዉ። በድርጅቱ የኮንጎ ተልኮ  ከጠፉበት ጊዜ አንስቶ ፍለጋ ሲያካሂድ ሰንብቶ ነዉ አስከሬናቸዉ የተገኘዉ። ቀሪወቹ የኮንጎ ዜጎች እስካሁን ደብዛቸዉ አልተገኘም። የሀገሪቱ  የመንግስት ቃል አቀባይ ላምበርት ሜንደ  እንደተናገሩት መርማሪወቹ  አስከሬናቸዉ የተገኘዉ ካሳይ አካባቢ በሚገኝ አንድ ወንዝ አጠገብ ነዉ። የመንግሥታቱ ድርጅትም በዚህ ስፍራ የተፈፀመዉን የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲያጣሩ ነበር የላካቸዉ። ማይክል ሻርፐር አሜሪካዊ ሲሆኑ ዛይዳ ካታላን ደግሞ የስዊድን ዜጋ ናቸዉ።   ለግድያዉ እስካሁን ኃለፊነት የወሰደ አካል አለመኖሩም ተመልክቷል።
በካቢላ መንግስት ላይ አምጸዉ የነበሩት ኪሚዋና ነሳፑ የተባሉ የጎሳና የሚሊሻ  መሪ በመንግሥት ኃይሎች  ከተገደሉ ካለፈዉ ከነሐሴ አጋማሽ  ወዲህ  በካሳይ ክፍለ ግዛትና በአጎራባች ከተሞች  ዉጥረቱ እየጨመረ መጥቶ ቢያንስ 400 ሰዎች መሞታቸዉን ከአካባቢዉ የሚወጡ የዜና ዘገባዎች ያመለክታሉ። የኮንጎ መንግሥት ብሔራዊ ፓሊስ ዓርብ ዕለት እንዳስታቀዉ ደግሞ  39 የፓሊስ  መኮንኖች በጎሳ መሪዉ ደጋፊ ናቸዉ በተባሉ አማጽያን  በካሳይ ክፍለ ግዛት  ተገድለዋል። 
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የአዉሮጳ ኅህብረት እና የአፍሪቃ ኅብረት በሀገሪቱ እየተፈጸመ ያለዉ ጥቃት አሳሳቢ በመሆኑ የሀገሪቱ የፓለቲካ መሪዎች በኅብረት አፋጣኝ እና ሰላማዊ መፍትሄ እንዲያፈላልጉ እያሳሰቡ ነዉ። ድርጅቶቹ ይህን ይበሉ እንጅ በጋቦን ዩኑቨርሲቲ የየሃገራት ስልታዊ ግንኙነትና ፖለቲካ ፕሮፌሰር የሆኑት ዮናታን ኖዶቶሚ ንጎሚ ግን የፓለቲካ መሪዎቹ የማይተባበሩበትን ምክንያት እንዳለ ነዉ የሚገልጹት።
«በዴሞክራቲክ ኮንጎ ሪፐብሊክ ፖለቲካ ላይ የተለያዩት ወገኖች በጋራ አብረው መስራት ላልቻሉበት ጉዳይ ሁለት ምክንያቶች ያሉ ይመስለኛል።  የመጀመሪያው የተቃዋሚው ቡድን መከፋፈል ነው፣ በተለይ መሪው ኤትየን ቺሴኬዲ ከሞቱ በኋላ፣ የተቃዋሚው ጥምረት ሁለት እና ሶስት ፕሬዚደንቶች ማቅረቡ ትልቅ እንቅፋት ደቅኗል። ሁለተኛው ፣ ከፕሬዚደንት ካቢላ በኩልም ስምምነቱ እንዲሳካ ፈቃደኝነቱ ተጓድሎ ይገኛል። እንደሚታወቀው፣ በሕገ መንግሥቱ መሰረት፣ ፕሬዚደንት ካቢላ፣ የስልጣን ዘመናቸው በማብቃቱ፣ በዚህ ስልጣን ላይ መገኘት አልነበረባቸውም።»
እንደ ፕሮፌሰር ንጎሚ በሀገሪቱ ለተከሰተዉ አሳሳቢ ችግር እና ለሚታየዉ አለመግባባት ከሀገሪቱ ፓለቲከኞች ባሻገር የጎረቤት ሃገራት ሚናም እንደቀላል የሚታይ አይደለም።
« ለኮንጎ ቀውስ ሌላው እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው ጉዳይ፣ የማይታዩት ተዋናዮች ናቸው። ማለትም፣ ባካባቢው ያሉ ርዋንዳን፣ ዩጋንዳን የመሳሰሉት ሀገራት በጠቅላላ፣ በተለይ ደግሞ፣ ምዕራባውያቱ ሀገራት ተጠያቂዎች ናቸው፣። እንደምታውቁት፣  ኮንጎ በተፈጥሮ ሀብት የታደለች እንደመሆኗ መጠን ሁሉም ይህው ሀብቷን መበዝበዝ ይፈለጋል። በዚሁ ስልታዊ ጥቅም የተነሳም የውጭ ኃይላት የኮንጎ ፖለቲካዊ ውዝግብ እንዳያበቃ የራሳቸውን ተፅዕኖ ያሳርፋሉ።» 
የተባበሩት መንግስታት በሀገሪቱ ከ19 ሺህ በላይ የሰላም አስከባሪ ሀይል አሰማርቶ የሚገኝ ሲሆን ለዚህም በየአመቱ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጭ ይደረጋል። የጸጥታዉ  ምክር ቤት በኮንጎ ያሰማራዉ በምህፃሩ MONUSCO የሰላም ማስከበር የተልዕኮ ጊዜዉን ለማራዘም በዛሬዉ ዕለት ድምጽ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል። 

Kongo Unruhen in Kinshasa
ምስል Reuters/N'Kengo

ፀሐይ ጫኔ

ሽዋዬ ለገሠ