1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፓሪስ፥ አሸባሪ ወንድማማቾቹ ተገደሉ

ዓርብ፣ ጥር 1 2007

በፈረንሣይ መዲና ፓሪስ «ሻርሊ ኤብቶ» የተሰኘው የስላቅ ጋዜጣ ዋና ጽ/ቤትን ፓሪስ ውስጥ በመውረር ግድያ የፈፀሙት ኹለት ወንድማማቾች መገደላቸው ተዘገበ። በፓሪስ ስተምሥራቅ አንድ የአይሁድ ሱፐርማርኬት ውስጥ ዛሬ ሌላ የሽብር ጥቃት በመሰንዘር ቢያንስ ኹለት ሰዎችን እንደገደለ የተጠቀሰው የሽብር ተጠርጣሪም መገደሉ ይፋ ሆኗል።

https://p.dw.com/p/1EI8R
Schießerei und Geiselnahme in Pariser Supermarkt 09.01.2014
ምስል AFP/Getty Images/T. Samson

ይኽ ከባድ ጦር መሣሪያ የታጠቀ ሰው የሸቀጥ መደብሩ ውስጥ ዘልቆ በመግባት ኹለት ሰዎችን ከመግደሉም በተጨማሪ አምስት ሰዎችን አግቶ እንደነበር ተነግሯል። የሽብር ጥቃቱን የፈፀመው ትናንት በደቡባዊው የፓሪስ መዳረሻ አንዲት ፖሊስን ተኩሶ የገደለው ሰው ሳይሆን እንዳልቀረ ፖሊስ አስታውቋል። የዛሬውን ግድያ የፈፀመው አሸባሪ ከትናንት በስትያ ፓሪስ ውስጥ 12 ጋዜጠኞችን ከገደሉት ወንድማማቾች ጋር በአንድ የእስልምና ቡድን ውስጥ እንደሚተዋወቁም ፖሊስ ጠቅሷል። ኹለቱ ወንድማማቾች «ሻርሊ ኤብ» የተሰኘው የስላቅ ጋዜጣ ዋና /ቤትን ፓሪስ ውስጥ በመውረር ግድያ ከፈፀሙ በኋላ ወደ ሰሜን ፈረንሣይ መሸሻቸው ይታወቃል። ወንድማማቾቹ ዳማታን ኢን ሻሊዬ የተባለው አካባቢ በሚገኝ አንድ የኅትመት መጋዘን ውስጥ እንደተደበቁ መገደላቸው ተገልጧል። ቀደም ሲል ከፖሊሶች ጋር ሲደረግ በነበረው ድርድር ኹለቱ ወንድማማቾች ለመሞት ዝግጁ መሆናቸውን መናገራቸው ተዘግቦ ነበር።

ታጋቾች ከፀጥታ ኃይላት ጋር
ታጋቾች ከፀጥታ ኃይላት ጋርምስል D. Kitwood/Getty Images

ፖሊስ አካባቢውን በበርካታ ፖሊሶች እና በሔሊኮፕተሮች በመክበብ ወደ ከተማዋ መውጣትም ሆነ እና መግባት አግዶም ነበር። ከትናንት በስትያ አንስቶ በፓሪስ በተከታታይ የተከሰተውን ግድያ በዓለም ዙሪያ በርካቶች አውግዘውታል። የፈረንሣይ የሙስሊም ዲሞክራቶች ሊቀመንበር አብድራህሜ ዳህማኔ፦

«ለጽንፈንነት ፈጣን ምላሽ ያስፈልጋል። ዛሬ የእኛ መልስ፦ እዚያ ምንድን ነው የሚያደርጉት? የሚል ነው። ይኼ እስልምና አይደለም! እጅግ በጣም በግልጥ መናገር ያስፈልጋል። ወጣቶች ከእንግዲህ እነዚህን የወንጀለኞች ቡድን እና አክራሪ ኢማሞችን መስማት የለባቸውም። ያ ዝቅጠት ብቻ ነው የሚያስከትልብን!»

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ