1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፓሪስ፤ የሽብር ጥቃቱ አቀነባባሪ ተገደለ

ሐሙስ፣ ኅዳር 9 2008

ባለፈዉ ዓርብ ፓሪስ ፈረንሳይ ላይ የደረሰዉን የሽብር ጥቃት በማቀነባበር የሚጠረጠረዉ አብደልሀሚድ አባዑድ መገደሉን ፖሊስ ዛሬ አረጋገጠ። የፈረንሳይ ፖሊስ ትናንት በሰሜን ፓሪስ አካባቢ በሚገኝ አንድ መኖሪያ ቤት ላይ ባካሄደዉ ከበባ በነበረዉ የተኩስ ልዉዉጥ ነዉ ተፈላጊዉ የተገደለዉ።

https://p.dw.com/p/1H99H
Abdelhamid Abaaoud Mastermind der Anschlagsserie von Paris
ምስል Reuters/Social Media Website

ትዉልዱ ከሞሮኮ የሆነዉ ይህ ግለሰብ ሶርያ ዉስጥ ሰልጥኖ እንደመጣ እና ባለፈዉ ዓመት ጥር ወር የቤልጅየም ፖሊስን ሊገድል ሞክሮ እንደከሸፈበትም ተገልጿል። በወቅቱ አንዲት ሴት አጥፍቶ ጠፊ የታጠቀችዉን የፈንጂ ቀበቶ ካነጎደች እና ሰባት ሰዓት ከፈጀዉ የተኩስ ልዉዉጥ በኋላም ቢያንስ ሁለት አስከሬን በስፍራዉ መገኘቱን አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል። የእጅ አሻራን የሚመረምሩ ባለሙያዎች ከሟቾቹ አንዱ ተፈላጊዉ የቤልጂየም ዜጋ መሆኑን መለየታቸዉንም አመልክቷል። ትናንት ከተካሄደ ከበባዉና የተኩስ ልዉዉጥ በኋላ የሀገሪቱ የምክር ቤት አባላት ዛሬ በፈረንሳይ የተደነገገዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም እንዲራዘም ወስኗል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ፖሊሶች እና የፀጥታ ኃይሎች መሣሪያቸዉን ከሥራ ሰዓት ዉጭም ይዘዉ እንዲንቀሳቀሱ እና የፈረንሳይ መንግሥትም የኢንተርኔት እና የማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን ግንኙነቶችን እንዲዘጋም ይፈቅዳል። ምክር ቤቱ አዋጁን ሲያራዝም ጠቅላይ ሚኒስትር ማኑዌል ቫልስ አሁንም ፈረንሳይ ምናልባትም የኬሚካል ጦርመሳሪያ አደጋ እንደሚያሰጋት አሳስበዋል።

Frankreich Premierminister Valls Rede im Parlament
ጠቅላይ ሚኒስትር ማኑዌል ቫልስምስል Getty Images/AFP/F. Guillot

«አሁንም የኬሚካል ወይም ባዮሎጆካል ጦር መሣሪያ እንደሚያሰጋን እናዉቃለን። ድንበር አልፎ ሊሄድ የሚችል አዲስ የጦርነት ዓይነት እያየን ነዉ። በእስላማዊ መንግሥት ወይም በአልቃይዳ የግንኙነት ሰንሰለት አማካኝነት ከረዥም ርቀት የሚካሄድ ጦርነት። በዚህ አማካኝነት ተዋጊዎች ይመለመላሉ፤ ይሰለጥናሉ፤ ንጥረነገሮች ይቀመሙና ትዕዛዝ ይተላለፋል። በአንድ ትዕዛዝ ብቻም ትርምሱ ተደራጅቶ ይጀመራል።»

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ