1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፓሪስ፤ የሽብር ጥቃት እና ሐዘን

ቅዳሜ፣ ኅዳር 4 2008

የአውሮጳ መሪዎች የፓሪስ ሽብር ሰለባዎችን ለማሰብ በዕለተ ሰኞ የአንድ ደቂቃ የሕሊና ጸሎት እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል። መሪዎቹ በጋራ ባወጡት መግለጫ ኅዳር 4 በየዓመቱ የአውሮጳ የሐዘን ቀን ሆኖ ይታወሳል ብለዋል። በዕለተ ሰኞ 510 ሚሊዮን የአውሮጳ ዜጎች በሕሊና ጸሎቱ በመሳተፍ ለፓሪስ ሽብር ሰለባዎች አጋርነታቸውን እንዲያሳዩ ጥሪ ተላልፏል።

https://p.dw.com/p/1H5vX
Frankreich Trauer
ምስል Reuters/Ch. Hartman

ከፈረንሳዩ የሽብር ጥቃት በኋላ ከብራስልስ የሞሌንቤክ የመኖሪያ ሰፈር ጋር ግንኙነት ያለው የኪራይ መኪና በፓሪስ ተገኝቷል። እስካሁን በሞሌንቤክ አምስት ሰዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል። ከጥቃት ፈጻሚዎች መካከል ሶስቱ ከሞሌንቤክ የመኖሪያ መንደር የመጡ መሆናቸውን የፈረንሳይ ጋዜጣ ዘግቧል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ «የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አዉጄያለሁ። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በመላዉ ፈረንሳይ ተግባራዊ መሆኑን ክትትል ይደረጋል።» ሲሉ ከጥቃቱ በኋላ የፈረንሳይ የጸጥታ ሁኔታ እንዲጠናከር ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

ፕሬዝዳንቱ የፈረንሳይ ድንበር እንዲዘጋ ትዕዛዝ ያስተላለፉ ሲሆን በመላ አገሪቱ ጥብቅ የጸጥታ ቁጥጥር እንዲደረግ ወታደሮቻቸውን አሰማርተዋል። ጥቃት ከተሰነዘረባቸው አምስት ቦታዎች መካከል ባታክላን የተሰኘው የሙዚቃ ትዕይንት መድረክ ይገኝበታል። በፓሪስ አቅራቢያ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች፤ ምግብ ቤቶች፤ የስፖርት ማዘውተሪያዎች፤ የግብይት ማዕከላትና ህዝብ የሚሰበሰብባቸው አደባባዮች እንዲዘጉ የፈረንሳይ መንግስት ትዕዛዝ አስተላልፏል።

Frankreich Attentat Paris Spurensicherung
ምስል picture-alliance/dpa/J. Warnand

ከፓሪስ ተከታታይ የሽብር ጥቃቶች በኋላ የዓለም መሪዎች ለፈረንሳይና ዜጎቿ አጋርነታቸውን በመግለጥ ላይ ናቸው። የጀርመኗ መራሂተ-መንግስት አንጌላ ሜርክል ሽብርተኝነትን በቃላትና በተግባር ልንታገለው ይገባል ሲሉ ተናግረዋል። ዛሬ ማለዳ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት መራሒተ-መንግስቷ ጀርመናዉያን የፈረንሳይ ሕዝብ የሀዘን ተካፋይ መሆናቸዉን አመልክተዋል።

«ለመላዉ ፈረንሳዉያን በዛሬዉ ዕለት ከዚህ የተሰማንን መግለፅ እፈልጋለሁ። እኛ ጀርመናዉያን ወዳጆቻችሁ ይበልጥ ወደእናንተ የቀረብን እንደሆን ይሰማናል። አብረናችሁም እናለቅሳለን። ለመግለፅ በሚያዳግት መል እናንተን በጎዳዉ ሽብር ላይ በሚካሄደዉ ዘመቻ ከእናንተ ጋር በመሆንም እንሳተፋለን።»

የአሜሪካን ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በበኩላቸው ለፈረንሳይ መንግስትና ህዝብ አስፈላጊውን እገዛ ሁሉ ለማቅረብ በተጠንቀቅ እንደሚጠባበቁ ተናግረዋል። የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንም የሐዘን መግለጫቸውን ለፕሬዝዳንት ፍራንሷ ኦሎንድና ፈረንሳውያን ልከዋል። የተ.መ.ድ. የጸጥታው ምክር ቤት፤ የአውሮጳ ሕብረትና የሰሜን ቃል ኪዳን ጦር (ኔቶ) የፓሪሱን ጥቃት ካወገዙ መካከል ይገኙበታል። ሳዉድ አረቢያና ሌሎች የአረብ ሃገራትም ጥቃቱን በጥቅብ ማዉገዛቸዉን እየገለፁ ነዉ። የሶርያው ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ በበኩላቸው ፈረንሳይ የምትከተለው ፖሊሲ ለሽብርተኝነት መስፋፋት አስትዋጽዖ እያበረከተ ነው ሲሉ የፕሬዝዳንት ፍራንሷ ኦሎንድን መንግስት ተችተዋል።

Frankreich Präsident Francois Hollande
ምስል Getty Images/T. Chesnot

ትናንት ዓርብ እኩለ ሌሊት በፓሪስ በተፈጸሙ ተከታታይ የሽብር ጥቃቶች የተገደሉት 130 ደረሱ፤ ከ200 የሚበልጡ ሰዎችም ተጎድተዋል። ራሱን «እስላማዊ መንግስት» በማለት የሚጠራው ጽንፈኛ ቡድን ስምንት ታጣቂዎች ለፈጸሙት አሰቃቂ ጥቃት ኃላፊነቱን ወስዷል። ጽንፈኛ ቡድኑ በፓሪስ ትናንት ሌሊት በተከታታይ በሙዚቃ አዳራሽ፤ ምግብ ቤቶችና መጠጥ ቤቶች ላይ የፈጸሙት ጥቃቶች የደረሱት የቦንብ ቀበቶ የታጠቁና ክላሽንኮቭ የጦር መሳርያ ባነገቱ አባላቱ መሆኑን አስታውቋል። ከጥቃቱ ፈጻሚዎች መካከል ሰባቱ የታጠቁትን የቦምብ ቀበቶ በማፈንዳት ራሳቸውን ያጠፉ ሲሆን አንዱ ከጸጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት ተገድሏል። ከጥቃት ፈጻሚዎቹ በአንዱ አስከሬን አጠገብ የሶርያ ፓስፖርት መገኘቱን ፖሊስ አስታውቋል።
እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሰ