1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፔጊዳ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 28 2007

ፔጊዳ የተባለውን በአውሮፓ ፀረ እስልምና ንቅናቄን ዓላማ ና እንቅስቃሴ በመቃወም ትናንት ማምሻውን በበተለያዩ የጀርመን ከተሞች ሰላማዊ ሰልፎች ተካሂደዋል ። በተመሳሳይ ጊዜ የንቅናቄው አባላትና ደጋፊዎቻቸውም በአንዳንድ የጀርመን ከተሞች አደባባይ ወጥተዋል ።

https://p.dw.com/p/1EFq0
Protest gegen Pegida in Köln
ምስል picture-alliance/dpa/M. Hitij

«የምዕራብ ፀረ-እስልምና የአውሮፓ አርበኞች» በጀርመንኛው ምህፃሩ ፔጊዳ የተባለው ህብረት በጀርመን የተለያዩ ከተሞች የሚያካሂደው የተቃውሞ ሰልፍ 3 ወራት አስቆጥሯል ።እስልምና በአውሮፓ እንዳይስፋፋ እታገላለሁ የሚለው ይኽው ኅብረት ባለፈው ጥቅምት የአደባባይ ተቃውሞውን የጀመረው በጥቂት መቶዎች የሚቆጠሩ አባላትና ደጋፊዎችን ይዞ ነበር ። ከ3 ወራት በኋላ ግን ትናንትኅብረቱ በጠራው ሰልፍ የተካፈሉት ቁጥር ወደ 18 ሺህ ከፍ ብሏል ።የንቅናቄው መስፋፋትና ተቃውሞውም ተጠናክሮ መቀጠሉ በጀርመን ዋነኛ የመነጋገሪያ ርእስ ሆኗል ። የውጭ ዜጎች ከጀርመን ይውጡ ጀርመን ለጀርመናውያን ብቻ የሚል አቋም ያለውን የህብረቱን እንቅስቃሴ የሚቃወሙ ሰልፎችም በየጊዜው መካሄዳቸው ቀጥሏል ። ትናንት በድሬስደን በበርሊን በኮሎኝና በሽቱትጋርት ፔጊዳ ሰልፍ ባካሄደበት ተመሳሳይ ጊዜ የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል ። ኮሎኝ ውስጥ ፔጊዳን በመቃወም በተጠራው ሰልፍ በከተማዋ የሚገኙ የተለያዩ የሃይማኖት ድርጅቶች ተጠሪዎችና አባላት እንዲሁም የሰራተኛና አሰሪ ማህበራት ናቸው የተቃውሞ ድምፃቸውን ያሰሙት ። በተቃውሞ ሰልፍ የተካፈሉት በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሃላፊ ሊቀ ካህናት ዶክተር መርዓዊ ተበጀ የሃይማኖት ተቋማት በህብረት ድምፃቸውን ለማሰማት የወጡበትን ምክንያት ገልፀውልናል ።
በተለይ በኮሎኝ ታዋቂውን የዶም ካቴድራልን ጨምሮ በከተማዋ የሚገኙ ድርጅቶች የተለያዩ ተቋማትና ና አብያተ ክርስቲያን የፔጊዳን ዓላማ እንደሚያወግዙ የህንፃዎቻቸውን መብራት በማጥፋት ጭምር ነበር ያሳወቁት ።በዚሁ ሰልፍ ላይ ኮሎኝን ያካተተው የኖርድራይንቬስትፋለን ፌደራዊ ክፍለ ግዛት ሙስሊሞች ማህበር ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት አቶ ሲራጅ መሀመድም ተካፍለዋል ። የቦን ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሲራጅ የፔጊዳ እንቅስቃሴ ጀርመን ነዋሪ የሆነውን የሙስሊሙን ማህበረሰብ ስጋት ላይ ጥሏል ይላሉ ።
ሊቀ ካህናት ዶክተር መርዓዊ ተበጀ እንደሚሉት ደግሞ ፀረ እስልምናና የውጭ ዜጎች አቋም ያለው ፔጊዳ አስጊነቱ ጀርመን ለሚኖሩ የውጭ ዜጎች ብቻ አይደለም ።
25 ዓመታት ጀርመን የኖሩት አቶ ሲራጅ እንደሚሉት ፔጊዳ የተባለው ኅብረት ለፀረ እስልምና አቋሙ የሚሰጠው ምክንያትና ተጨባጩ ሁኔታ የተለያየ ነው ። በርሳቸው አስተያየት ኅብረቱ በአውሮፓ የእስልምናን መስፋፋት ለንቅናቄው ምክንያት አድርጎ ያቅርብ እንጂ ከበስተጀርባው የያዘው ዓላማ ግን የተለየ ነው ።

Protest gegen Pegida in Berlin
ምስል Reuters/H. Hanschke


በአቶ ሲራጅ እምነት ፔጊዳንና ዓላማውን የሚያራምዱ ኃይሎችን ለመከላከል ከሚያስችሉ መንገዶች አንዱ ህብረተሰቡ ስለ ሙስሊሞችም ሆነ በአጠቃላይ ጀርመን ስለሚኖሩ የውጭ ዜጎች የአመለካከት ለውጥ እንዲያመጣ ማድረግ ነው ።
ሊቀ ካህናት ዶክተር መርዓዊ ተበጀ በበኩላቸው ተጠናክሮ ለቀጠለው በጀርመንኛ ቋንቋ የውጭ ዜጎች ጥላቻ መፍትሄው ውይይት ነው ይላሉ።
የፔጊዳ እንቅስቃሴ በበርካታ የጀርመን ታዋቂ ሰዎችም ተወግዟል ። ቢልድ የተባለው ጋዜጣ ዛሬ እንደዘገበው ቁጥራቸው 50 የሚሆኑ ፖለቲከኞችና ታዋቂ ጀርመናውያን እየተስፋፋ የሄደው የውጭ ዜጎች ጥላቻ እንዲቆም ጠይቀዋል ።የጀርመን መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል በአዲስ ዓመት መልዕክታቸው ህብረተሰቡ በፔጌዳ ሰልፍ እንዳያካፈል ጥሪ አስተላለፈው ነበር ።

Protest gegen Pegida in Köln
ምስል picture-alliance/dpa/O. Berg

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ