1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፕሬዝደንታዊ ምርጫ በጅቡቲ

ዓርብ፣ መጋቢት 30 2008

የጅቡቲ ህዝብ ዛሬ ፕሬዝዳንቱን ለመምረጥ ድምፁን ሲሰጥ ውሏል። በአፍሪቃ ቀንድ ስልታዊ ጠቀሜታ ባላት በጅቢቲ በሚካሄደው ምርጫ ሃገሪቱን ለ17 ዓመታት የመሩት ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጉሌህ የተቃዋሚዎችን ኅብረት ወክለው የሚወዳደሩትን ተቀናቃናቸውን ኦማር ኤልሚ ክሃይሬህን በሰፊ ልዩነት ያሸንፋሉ ተብሎ ይጠበቃል ።

https://p.dw.com/p/1ISAc
Dschibuti Präsident Ismail Omar Guelleh
ምስል Picture-allaince/dpa/J. Warnand

[No title]

በተቃዋሚዎች ኅብረት ውስጥ ከተካተቱት 7 ፓርቲዎች ሦስቱ ራሳቸውን ከምርጫው አግለዋል። ስለ ምርጫው ዶቼቬለ ያነጋገራቸው የቻተም ሃውሱ የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ አህመድ ሱሌማን በአሁኑ ምርጫ ከበፊቶቹ የተለየ አሠራርና ውጤት እንደማይጠብቁ ገልፀዋል ።

« አጠቃላዩ ሁኔታ ነፃና ትክክለኛ ምርጫ እንደማያካሄድ የሚያስረዳ ይመስለኛል ። ይህ ደግሞ እስካሁን የቀጠለ አካሄድ ነው ። የምርጫው ውጤትም ለፕሬዝዳንቱ የሚያደላ ነው የሚመስለኝ »

Dschibuti Straßenszene Moschee
ምስል Getty Images/S.Gallup

የጉሌህን የሥልጣን ዘመን ማራዘም እንዲቻል የጅቡቲ ፓርላማ ሕገ-መንግሥቱን ካሻሻለ በኋላ በጎርጎሮሳዊው 2011 በተካሄደው ምርጫ 80 በመቶ ድምፅ በማግኘት ነበር ጉሌህ ያሸነፉት ። የ68 ዓመቱ ጉሌህ ጅቡቲ ከፈረንሳይ ነፃነቷን ካገኘችበት ከጎርጎሮሳዊው 1977 ወዲህ ሃገሪቱን የመሩ ሁለተኛው ፕሬዝዳንት ናቸው ። የመጀመሪያው የጅቡቲ ፕሬዝዳንት ሃሰን ጉሌድ ኦፕቲዶን የጉሌህ አጎት ናቸው ። ወደ 900 ሺህ ከሚጠጋ የጅቡቲ ነዋሪ 180 ሺህ ያህሉ ድምፅ መስጠት ይችላል ። የምርጫው ውጤት በ24 ሰዓት ውስጥ ይፋ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል ።

ጅቡቲ በአፍሪቃ ቀንድ ላይ ከአረብ ባህረ ሰላጤ ጋር ተያይዛ የምትገኝ ትንሽ ሀገር ናት። በቀይ ባህር የኤደን ባህረ ሰላጤን አቋርጦ ወደ ስዊዝ ካናል ለመሻገር የሚሻ የየትኛዉም ሀገር መርከብ መተላለፊያም ሆነ ማረፊያ በመሆኗም ትታወቃለች። አቀማመጧ እና ከአጎራባቾቿ ጋር ስትነጻጸር ያላት የፖለቲካ መረጋጋትም ለዓለም ንግድ ቁልፍ መዳረሻ አድርጓታል። በሌላ በኩል በአንድ ወቅት የባህር ላይ ወንበዴዎች የመርከቦችን እንቅስቃሴ የሚያወኩበት አካባቢ ሆኖም ታይቷል። ይህን ለመከላከልም የተለያዩ ሃገራት የባህር ኃይሎች እንደሚንቀሳቀሱም ይነገራል። የመርከቦች መነኻሪያዋ ጅቡቲ ዛሬ ምርጫ ታካሂዳለች። የዶቼ ቬለዋ ፍሪደርከ ሚዩለር ዩንግ እንደምትለዉ የስልጣን ለዉጥ ግን እጅግ አይጠበቅም፤ የበርሊኑ ዘጋቢያችን ይልማ ኃይለ ሚካኤል ዘገባዋን እንደሚከተለዉ አጠናቅሮታል።

Dschibuti spanisches Kriegsschiff im Hafen
ምስል Getty Images/AFP/C. De Souza

ይልማ ኃይለ ሚካኤል

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ