1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

[No title]

ሰኞ፣ ጥር 23 1997
https://p.dw.com/p/E0f1
የጀርመን መራኄ-መንግሥት ጌርሃርት ሽሮኧደርና ቦኖ፧ በዳቮሱ ጉባዔ፧
የጀርመን መራኄ-መንግሥት ጌርሃርት ሽሮኧደርና ቦኖ፧ በዳቮሱ ጉባዔ፧ምስል AP
የዳቮሱ ጉባዔ ፍጻሜ፧
ዳቮስ፧ እስዊትስዘርላንድ ሲካሄድ የሰነበተው፧ ፴፭ኛው በዓለም ኤኮኖሚ ላይ ያተኮረው ዓመታዊ ጉባዔ፧ ትናንት ተደምድሟል። የዓለም የኤኮኖሚ መድረክ በመባል የታወቀውን ዓለም አቀፍ የኤኮኖሚ ተመልካች ጉባዔ የጠነሰሱት Klaus Schwab እንደገለጹት፧ በደቡብ ምሥራቅ እስያ፧ በውቅያኖስ ማዕበል ለተጎዱት፧ የታየው፧ ሰፊ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ዝግጁነት፧ የሰው ልጆች በመላ ዕጣ ፈንታቸው የተሣሠረ መሆኑን ያስረዳል። ከ ፺፮ አገሮች የተውጣጡ 2,250 ታዋቂ የኤኮኖሚ ጠበብትና የፖለቲካ ሰዎች ፭ ቀናት ሙሉ፧ ስለ ዓለም ኤኮኖሚ ይዞታ ሲመክሩ መሰንበታቸው የታወቀ ሲሆን፧ ስለዚህ ጉዳይ Joachim Schubert-Ankenbauer ያቀረበው ሐተታ ቀጥሎ ይሰማል።
በዳቮስ ተራራማ የመዝናኛ ሥፍራ ሲካሄድ የሰነበተው፧ ብዙ ህዝብም በአንክሮ የተከታተለው፧ በሚልዮን የሚቆጠር ፍራንክም ወጪ የተከፈለበት ጉባዔ፧ ምን ፋይዳ አስገኝቷል? ሱናሚ የተሰኘው የባህር ወለል የምድር ነውጥ የቀሰቀሰው የውቅያኖስ ማዕበል፧ በደቡብ ምሥራቅ እስያ፧ በመቶ ሺ የሚቆጠር ህዝብ በፈጀ በወሩ የተካሄደው ዓለም አቀፍ ጉባዔ፧ በዚያ ላይ ብቻ ሳይሆን፧ በዘመኑ ዐበይት ፈተናዎች ላይ እንዲተኮር አስችሏል። በመሆኑም፧ በዓለም ዙሪያ፧ በሽታንና ደህነትን ለመታገል ቆርጦ መነሳት እጅግ ተፈለጊ መሆኑ ከምር ሳይመከርበት አልቀረም። በተለይም የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ዣክ ሺራክና የብሪታንያው ጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ ብሌር፧ የድርጊቶችን ሂደት ምልክት በሚገባ ማሳየታቸው ነው የሚነገርላችው። ይህ በእርግጥ ተግባራዊ እንዲሆን፧ የታወቁ የኪነ ጥበብ ከዋክብት፧ ቦኖንና አንጀሊና ጆሊን የመሳሰሉት በሥፍራው በአካል በመገኘት አበረታትተዋል። ድህነት እጅግ የተዛመተበት የአፍሪቃው ክፍለ-ዓለምም፧ በዳቮሱ ጉባዔ፧ እንዲህ እንደ ዘንድሮ በዛ ያሉ ተወካዮችን አሳትፎ አያውቅም።
አፍሪቃን ከድህነት ማጥ ለማውጣት፧ ጠቀም ያለ ያለ ገንዘብ ብቻ ማቅረብ እንደማይገባ አንዳንድ የአፍፊቃ ተወካዮች ከማስገንዘብ አልቦዘኑም።። በመጀመሪያ የሠመረ የፖለቲካ አመራርና መረጋጋት የግድ ተፈላጊዎች ናችው። ይሁንና ይህን ሐቅ፧ በተለይ ቶኒ ብሌርን የመሳሰሉ አንዳንድ ታዋቂ ፖለቲከኞች ከልብ ሊያዳምጡት የፈለጉ አይመስሉም ነው የተባለው። ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ፧ የዳርፉሩን ዕልቂት ለማስቆም፧ ለምን በጊዜው ተገቢውን እርምጃ አልወሰደም፧ በኮንጎ የእርስ-በርስ ጦርነት አለመገታቱን እየተመለከተ፧ እንዴት፧ በኢራን ላይ ድንገተኛ ወታደራዊ እርምጃ ቢወሰድ፧ ከሚል ግምት በመነሳት ይወያያል? የሹበርት-አንከንባዎር የአንክሮ ጥያቄ ነው። ስለዓለም የንግድ ልውውጥ፧ የመንግሥታትን የግብርና ድጎማ ስለማስቀረት፧ በተለይ፧ ለአዳጊ አገሮች ጥሬ አላባዎች፧ ገበያውን ክፍት ማድረግ እጅግ ተፈላጊ ስለመሆኑ፧ ዳቮስ ላይ በሰፊው ተነግሮአል። ብዙ በጎ ቃላት ተሠንዝረዋል። ጥያቄው እንዴትና መቼ ነው በተግባር የሚተረጎመው? የሚለው ነው። ለምሳሌ ያህል፧ ትልቁ የቅመማ ፋብሪካ፧ Dow Chemical ፧ ስለ በጎ ምግባርና ኀላፊነት፧ ስብከት መሰል ዲስኩር አሰምቷል። ይሁን እንጂ ህንድ ውስጥ በቦፓል ከተማ በሚገኘው የቅመማ ፋብሪካው የሚሠሩ ሰዎች፧ በመርዘኛ ጋዝ እንዳይጎዱ፧ አስተማማኝ ሁኔታ አልተፈጠረላቸውም። እርስ በርስ የሚቃረኑ ይህን መሰል ጉዳዮች መኖራችው ቢታወቅም፧ ዘንድሮ ዳቮስ ላይ የተሰማው ንግግርና የታየውም ምልክት ተስፋ ፈንጣቂ ነው። ታላላቅ ፖለቲካኞች እንዳመላከቱት፧ አፍሪቃ ውስጥ ድህነትን መቋቋም፧ የሚለው ጉዳይ ላቅ ያለ ትኩረት ሳይሰጠው አልቀረም። ዓለም አቀፉን የኤኮኖሚ አጽናፋዊ ትሥሥር በተመለከተ፧ ተቃውሞው ዘንድሮ ጋብ ያለ ነው የመሰለው። ይሁንና፧ በድህነት፧ በኤኮኖሚ አጽናፋዊ ትሥሥርና በማኅበራዊ ኑር ዕድገት ላይ ያተኮረው ውይይት እንደቀጠለ ነው። ትንሹ የሥራ ጅምር ነክ ምልክት፧ በተግባር መከሰት ይኖርበታል።