1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

15 አመታት-ዓለም አቀፍ ሕዋ ሳይንስ ጣቢያ

ረቡዕ፣ ኅዳር 29 2008

ዩናይትድ ስቴትስ በዓለም አቀፉ የህዋ ሳይንስ ጣቢያ ለሚገኙት ስድስት ጠፈርተኞች ባለፈው እሁድ የላከችው የገና ስጦታ ዛሬ በእለተ ረቡዕ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።

https://p.dw.com/p/1HKsX
15 Jahre Internationale Raumstation ISS
ምስል Getty Images/NASA

15 አመታት-ዓለም አቀፍ ሕዋ ሳይንስ ጣቢያ

ለምርምር ጣቢያውና ባለሙያዎቹ እጅጉን አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶች የጫነችው አትላስ ቪ «Atlas V» የተሰኘች ሮኬት በዓለም አቀፉ ህዋ ሳይንስ ጣቢያ ከደረሰች ለዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ስኬት ነው። 7,400 ፓውንድ የሚመዝን ቁሳቁስ ጭና ወደ ጥልቁ ህዋ የተመነጠቀችው አትላስ ቪ ሮኬት ከዚህ ቀደም በነበረ ነፋሻማ የአየር ጠባይና ደመና ምክንያት ሶስት ጊዜ ጉዞዋ ተራዝሟል።
ዓለም አቀፉ የህዋ ሳይንስ ማዕከል በመሬት ዙሪያ ሲሽከረከር እነሆ 15 አመታት ሞላው። ጣቢያው በህዋ ሳይንስ ላይ ትኩረት ላደረጉት ጠፈርተኞች መኖሪያ እና ቤተ-ሙከራ ሆኖ ያገለግላል። ጣቢያው የተገነባው በዩናይትድ ስቴትስ፤ሩሲያ፤አውሮጳ፤ጃፓን እና ካናዳ የህዋ ማዕከላት በትብብር ነው። ዶ/ር ጥላዬ ታደሰ በአሜሪካ የጠፈር ምርምር ጣቢያ ወይም ናሳ ተመራማሪ ናቸው።
ጣቢያው የተገነባው እያንዳንዱ አካል በተናጠል ከተጓጓዘ በኋላ ጠፈርተኞቹ እጅ እዛው ሕዋ ላይ ነው። የጣቢያው ግንባታ የተጀመረው በጎሮጎሮሳዊው ኅዳር 1998 ዓ.ም ሲሆን ለግንባታው የሚያስፈልገውን ቁሳቁስ ይዛ ወደ ሕዋ የመጠቀችው ዛርያ የተሰኘች የሩሲያ ሮኬት ነበረች። ከሁለት ሳምንታት በኋላ ኢንዴቨር የተሰኘችው የዩናይትድ ስቴትስ መንኮራኩር እና የሩሲያ ዛርያ በአንድ ምህዋር ተገናኙ። የጣቢያ ግንባታው መሠረት አንድ ተብሎ ተጣለ። የጣቢያውን ግንባታ ሙሉ በሙሉ አጠናቆ በውስጥ ተመራማሪዎች እንዲኖሩበት ለማስቻል ግን የሁለት አመታት ጊዜ ወስዷል። በጎርጎሮሳዊው ኅዳር 2 ቀን 2000 ዓ.ም. የመጀመሪያዎቹ ተመራማሪዎች ከዓለም አቀፍ የሕዋ ሳይንስ ጣቢያው ደረሱ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ተልዕኮዎች ተመራማሪዎች ይገኙበታል። በጊዜ ሂደት ግን የሕዋ ሳይንስ ጣቢያው የተለያዩ የጥናትና ምርምር ቁሳቁሶች ተገጥመውለት ግንባታው ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀው በጎርጎሮሳዊው 2011 ዓ.ም. ነበር። ጣቢያው የሚሽከረከርበት ምህዋር ከምድር በአማካኝ 220 ማይል ወይም አራት መቶ ኪ.ሜትር አካባቢ ነው።
ዓለም አቀፍ ሕዋ ሳይንስ ጣቢያ በሰዓት 28,000 ኪ.ሜ. እየበረረ ምድርን በዘጠና ደቂቃ አንድ ጊዜ ይዞራታል። አሁን ከምድር በ400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ግዙፉ ዓለም አቀፍ የሕዋ ሳይንስ ጣቢያ ካሉት ስድስት የህዋ ተመራማሪዎች ጠፈርተኞች መካከል አሜሪካዊው ስኮት ኬሊ ይገኙበታል።
«በምድር ዙሪያ የሚሽከረከር ዓለም አቀፍ ቤተ-ሙከራ ነው። ዋናው ሥራ ደግሞ በሕዋ ውስጥ የሚደረገው አሰሳ እና የምንኖርበት ምህዋር(ኦርቢት) ለመረዳት የሚደረገው ጥናትና ምርምር ነው። አጠቃላይ የምንኖርበትን(ሥርዓተ ፀሐይ)«ሶላር ሲስተም» ለመረዳት የምናደርገውን ጥረት አሳድጎልናል።»
አሜሪካው ስኮት ኬሊ የተልዕኮው አዛዥ ናቸው። ከእሳቸው በተጨማሪ ሰርጌ ቮልኮቭ አሌክሳንድሮቪች ፤ኦሌግ ኮኖኔንኮ እና ሚካኼል ኮርኔይንኮ ከሩሲያ፤በትውልድ ታይዋናዊ በዜግነት ግን አሜሪካዊ የሆኑት ኪጄል ሊንድግረን እና ጃፓናዊው ኪሚያ ዩይ ጣቢያው ይገኛሉ። ስድስቱ የህዋ ተመራማሪዎች ጠፈርተኞች በዓለም አቀፉ የሕዋ ሳይንስ ጣቢያ ለአንድ አመት የሚቆዩ ሲሆን ዛሬ ድረስ ከ255 በላይ ቀናት አስቆጥረዋል። የተልዕኮው ዋና ዓላማ የሰው ልጅ ለሰነቀው የማርስ ጉዞ ጥናትና ምርምር ማድረግ ነው። የሰው ልጅ የመሬት ስበት በሌለበት ሁኔታ ውስጥ የሚያሳየውን አካላዊ እና ስነ-ልቦናዊ ለውጥ መፈተሽ ቀዳሚው ተግባሩ ነው። ለነገሩ ይህ የሰው ልጅ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሕዋ ከተጓዘበት ጊዜ ጀምሮ ትኩረት የተደረገበት የጥናት ዘርፍ ነው።ዶ/ር ጥላዬ ታደሰ ዓለም አቀፉ የሕዋ ሳይንስ ጣቢያ የሰው ልጅ ወደ ጥልቁ እና ውስብስቡ ሕዋ ሊያደርገው ላቀደው ጉዞ መረማመጃ እንደሆነ ይናገራሉ።
የሰው ልጅ ከመሬት ስበት ሲወጣ የሚገጥሙት ውስብስብ የጤና እክሎች በዓለም አቀፉ ሕዋ ሳይንስ ጣቢያ በትኩረት ጥናት ከሚደረግባቸው ዘርፎች አንዱ ነው። የሰውነት ፈሳሾች አቅጣጫቸው ወደ ደረትና ጭንቅላት መቀየር፤ የሰውነት ጡንቻዎች እና የአጥንት ጥንካሬ መዳከም ሰው ከመሬት ስበት ውጪ ሲሆን የሚገጥሙ ችግሮች መሆናቸውን በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ይጠቁማሉ። ወደ ሕዋ በሚደረግ ጉዞ በመሬት ላይ ያልተለመዱ ጨረሮች በሰውነት ላይ ሲያርፉ የሚያስከትሉት አደጋ፤ ተመራማሪዎቹ ከማህበራዊ ኑሮ እና አካላዊ እንቅስቃሴ ተገልለው በአንድ ቦታ ሲቆዩ የሚገጥማቸው ጫና አሁን በሕዋ ምርምር ዘርፉ ትኩረት ከሚደረግባቸው ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ።ይህን ከምድር ከባቢ አየር ውጪ ለሰው ልጅ ፈታኝ የሆነ አኗኗር ከሞከሩት መካከል አሌክሳንደር ጌርስት አንዱ ናቸው።ጀርመናዊው የህዋ ተመራማሪ ጠፈርተኛ አሌክሳንደር ጌርስት በዓለም አቀፉ ሕዋ ሳይንስ ጣቢያ ለስድስት ወራት ቆይታ አድርገው ተመልሰዋል።
«ወደ ሕዋ ሄዶ መኖር የሚከብድ ነገር የለውም። ተመልሰህ ወደ ምድር ስትመጣ ደግሞ የመሬት ስበት ስለሚያግዝህ በጣም ፈጣን ነው። እግርህ ከመንኮራኩሩ ሲወጣ ለስድስት ወራት ከመሬት ስበት ርቀህ እንደቆየህ ታስታውሳለህ። በዓለም አቀፉ የሕዋ ሳይንስ ጣቢያ በነበርንበት ጊዜ የሰውነት ጡንቻዎቻችንን እና የአጥንታችንን ጥንካሬ እንደነበር ለማቆየት ብዙ አካላዊ እንቅስቃሴ ስንሰራ ነበር። የሰውነት ጡንቻዎቼ እጅግ ጠንክረዋል። ነገር ግን ወደ መሬት ከተመለስክ በኋላ እንዴት ሰውነትህን መቆጣጠር እንዳለብህ፤የእጅህን እንቅስቃሴ እንደ አዲስ ትማራለህ። ምክንያቱም ከዚህ ሁሉ ርቀህ ቆይተሃል።»
ዶ/ር ጥላዬ ታደሰ በዓለም አቀፍ ሕዋ ሳይንስ ጣቢያ የሚደረገው ምርምር ለመጓጓዣ በሚያገለግሉት ሮኬቶችና መንኮራኩሮች ላይ ጭምር መሻሻሎችና ለውጦች ለማድረግ አግዟል ይላሉ።
አሌክሳንደር ጌርስት አምስት የመኝታ ክፍሎች አሊያም ሁለት የቦይንግ 747 አውሮፕላኖች ስፋት አለው በሚሉት የሕዋ ሳይንስ ጣቢያ ውስጥ ያሳለፉት ስድስት ወራት ያመጣው ለውጥ አካላዊ ብቻ አለመሆኑን ይናገራሉ። በነገራችን ላይ የሕዋ ሳይንስ ጣቢያው ስድስት ሰዎችና ጥቂት ጎብኚዎች የመያዝ አቅም እንዲኖረው ተደርጎ የተሰራ ነው። እንደ አሌክሳንደር ጌርስት አባባል የህይወት አተያያቸው በራሱ አዲስ ሆኗል።
«መሬትን ከላይ ሆኜ ስመለከታት ስለ ፕላኔታችን ያለኝን አመለካከት ቀይሮታል። በምድር ስለምንኖርበት አካባቢ አንጨነቅም። እጅግ በጣም ግዙፍ የማይጎዳ፤ተዝቆ የማያልቅ ሐብት አድርገን እንቆጥረዋለን። ነገር ግን ይህንን ከምድር ውጪ ሆነን ስንመለከተው ሁሉም ነገር በአንድ ጊዜ ይቀየራል። የምንኖርበት ምድር እጅግ በጣም ትንሽ የከባቢ አየሩ ጠባብ መሆኑን እንረዳለን። ሁሉም ነገር የሚያልቅ መሆኑን እንገነዘባለን። ምድርን ከሕዋ ለመጀመሪያ ጊዜ ስመለከት እጅግ አስደንጋጭ ነበር የሆነብኝ። ሊሰበር እና ሊበላሽ የሚችል እንደሆነ እንድረዳ አድርጎኛል። ካልተጠነቀቅን ልናጠፋው እንችላለን።»
በነገራችን ላይ ሩሲያ ከጎርጎሮሳዊው ከ1986-2001 ዓ.ም. ለ15 አመታት ያገለገለ ሚር የተሰኘ የሕዋ ምርምር ጣቢያ ነበራት። የቀድሞዋ ሶቭየት ሕብረት ከመፈራረሷ በፊት ወደ ሕዋ የተጓዘው ሚር በዘርፉ ቀዳሚ ሲሆን ተመራማሪዎችንና ጎብኝዎችን አስተናግዷል። አሜሪካውያኑ የአሁኑን ዓለም አቀፍ የሕዋ ምርምር ጣቢያ ለመገንባት ባደረጉት ጥረት ውስጥ የገጠሟቸውን ችግሮች ለመፍታት የሩሲያውያኑ ተመራማሪዎች እውቀትና ጥበብ ረድቷቸዋል። በተለይ ሕዋ ጣቢያው ለሚቆዩ ተመራማሪዎች የሚያስፈልገውን ውሃ ለማምረት የሩሲያውያኑን ጥበብ መጠቀም ግድ ብሏቸዋል።
በናሳ የ8 ቢሊዮን ዶላር አመታዊ በጀት እቅድ የተጀመረው ዓለም አቀፍ ሕዋ ሳይንስ ጣቢያ ከ150 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ እንደተደረገበት ይነገራል። የሕዋ ሳይንስ ጣቢያውን እቅድ እና ሙከራ የሚደግፉ የመኖራቸውን ያክል ተቺዎች አላጣም። የሚወጣበት እጅግ ከፍተኛ የገንዘብ መጠን እና ሰው አልባ መንኮራኩሮችና ሮቦቶች በአነስተኛ የገንዘብ መጠን የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ይችላሉ የሚለው አመክንዮ ለጊዜው ቀዳሚዎቹ ናቸው። ዶ/ር ጥላዬ ታደሰ ሕዋን ሊያስስ ለተነሳው የሰው ልጅ ዓለም አቀፉ የሕዋ ምርምር ጣቢያ ከፍ ያለ አስተዋጽዖ እንዳለው ይናገራሉ።
ሐብታም የዓለም አገሮችን የሚያስተባብረው የሕዋ ምርምር ጣቢያ የግል ኩባንያዎችንና የባለጠጎችን ትኩረት እየሳበ ነው። አሁን በጠፈር ለሚገኙት ስኮት ኬሊ እና ባልደረቦቻቸው ስንቅ እና አስፈላጊ ቁሳቁስ ሊያቀርብ የስራ ውል ከናሳ ወስዶ የነበረው ስፔስኤክስ(SpaceX) የተሰኘ የግል ኩባንያ ነበር። ኩባንያው ወደ ሕዋ ያስወነጨፋት መንኮራኩር ከምድር ከተነሳች ከጥቂት ሰኮንዶች በኋላ በመፈንዳቷ እቅዱ ሳይሰምር ቀርቷል። አሁን በጉዞ ላይ የሚገኘውና ዛሬ ከታቀደለት ቦታ ይደርሳል ተብሎ የሚጠበቀው አትላስ ቪ መንኮራኩርም ቢሆን ዩናይትድ ላውንች አትላስ (United Launch Alliance) በተሰኘ የግል ኩባንያ የተመረተ ነው።
እሸቴ በቀለ
ሒሩት መለሰ

PK Alexander Gerst
ምስል DW
SpaceX Falcon 9 Rackete mit Dragon Raumkapsel
ምስል picture alliance/dpa
15 Jahre Internationale Raumstation ISS
ምስል picture-alliance/dpa/NASA
15 Jahre Internationale Raumstation ISS
ምስል Reuters/NASA