1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

18 የስደተኞች አስክሬን በላምፔዱዛ ተገኘ

እሑድ፣ ነሐሴ 18 2006

የኢጣሊያ የባህር ኃይል ዛሬ እንዳስታወቀው በላምፔዱዛ የባህር መዳረሻ 18 አስክሬኖችን ሰብስቧል። የጀልባው ሞተር ላይ ጉዳት በመድረሱ ስደተኞቹ አደጋ እንደገጠማቸው ያስታወቀው የባህር ኃይል አክሎም «ሲሮ» የተባለው የባህር ኃይል መርከብ 73 ሰዎችን ከባህር ማትረፉን ገልጿል።

https://p.dw.com/p/1Czz5
Flüchtlinge Lampedusa
ምስል picture alliance / ROPI

ባለፈው ዓመት በመቶዎች የሚቆጠሩ የባህር ላይ ስደተኞች ባህር ሰምጠው ከሞቱ በኋላ የኢጣሊያ የባህር ኃይል በዚህ አካባቢ ቁጥጥር እንደሚያደርግ ይታወሳል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር በምህፃሩ «UNHCR» እንዳስታወቀው ካለፈው ጥር ወር አንስቶ ብቻ ከ100 000 በላይ ስደተኞች ኢጣሊያ ገብተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ በሊቢያ የባህር ጠረፍ አቅራቢያ በሰመጠው ጀልባው ላይ ተሳፍረው የነበሩ ከ250 በላይ ሰዎች ህይወት ሳይጠፋ እንዳልቀረ ዛሬ የሊቢያ የባህር ኃይል ለሮይተርስ ዜና ወኪል ገለፀ። ጀልባው ስደተኞችን ይዞ የሰመጠው ባለፈው አርብ ሌሊት ነበር።

ከምስራቅ ትሪፖሊ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘዉ በሊቢያ የባህር ዳርቻ፤ የጀልባ ስብርባሪ መገኘቱን የሃገሪቱ የባህር ዳርቻ ጠባቂዎች ትናንት አስታዉቀዋል። እንደ ሊቢያ የባህር ዳርቻ ጠባቂዎች 16 ተገን ጠያቂዎችን ከአደጋ ማዳን ተችሏል፤ 15 አስከሬን ደግሞ ከባህሩ ላይ ተለቅሟል። ጀልባዉ ላይ ተሳፍረዉ የነበሩ እና እስካሁን ደብዛቸዉ ያልተገኘ ወደ 170 የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በመፈለግ ላይ ናቸዉ። በሌላ ዜና ወደ 600 የሚሆኑ ከሶርያ እና ከፍልስጤም የመጡ ስደተኞች ኢጣልያ የባህር ዳርቻ መድረሳቸዉ ተዘግቧል። ተገን ጠያቂዎቹ ባህር ጠረፍ ለመድረስ የበቁት በኢጣልያ የባህር ላይ ሰራተኞች ርዳታ መሆኑም ተመልክቷል። ከተገን ጠያቂዎቹ መካከል በመቶዎች የሚቆጠሩ ህጻናት እና ሴቶች እንደሆኑም ተዘግቧል።

Lampedusa Flüchtlinge Lager Mineo
ምስል DW/K. Hoffmann

አዜብ ታደሰ

ልደት አበበ