1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

2014 እና የሁለት ሙዚቀኞች ዕረፍት

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 23 2007

ሁለቱ አንጋፋ ሙዚቀኞች ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸዉ ከተሰማ በኋላ በአዉሮጳ በተለይም በጀርመን ሙዚቃዎቻቸዉ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃኖች ከፍ ብለዉ መሰማት ጀምረዋል፤ በተወዳጅ ሙዚቃ መጠይቅ መዘርዝርም የአንደኝነቱን ቦታ ይዘዋል። ኦስትርያዊዉ ሙዚቀኛ ኡዶ ዮርገንስና፤ ብሪታንያዊዉ ሙዚቀኛ ጆ ኮከር!

https://p.dw.com/p/1EDyW
Bildergalerie 80 Jahre Udo Jürgens
ምስል picture-alliance/dpa


በዓለማችን የሙዚቃ መድረክ ታዋቂነትን ያተረፈዉ ብሪታንያዊዉ የሮክ እና ብሉዝ ሙዚቃ አቀንቃኝ ጆ ኮከር ትናንት በሸኘነዉ የጎርጎርዮሳዊ 2014 ዓ,ም መጠናቀቅያ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቶአል። ጀርመናዉያን የሙዚቃ አፍቃሪዎች በታዋቂዉ የብሪታንያ የየሮክ እና ብሉዝ ሙዚቃ አቀንቃኝ በጆ ኮከር ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ብቻ ሳይሆን ያዘኑት፤ በጀርመንኛ ቋንቋ ታናጋሪ ማሕበረሰቦች ዘንድ ታላቅ ዝናን ያተረፈዉ በታዋቂዉ ኦስትሪያዊ ሙዚቀኛ ኡዶ ዮርገንስ ድንገተኛ ሞትም ነበር። በተለያዩ የእድሜ ክልል የሚገኙ የሙዚቃ አፍቃሪዎችን ቀልብ በመሳቡ የሚታወቀዉ ኡዶ ዮርገንስ ሰማንያ ዓመቱን ከደፈነ በኋላ በቅርቡ በሽዎች የሚቆጠሩ አፍቃሪዎቹ በተሰባሰቡበት ትልቅ የሙዚቃ ድግስን አሳይቶ ስለሱ ሙዚቃ ዝና ሲወራ ባለበት ጊዜ ነበር ፤ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ የተሰማዉ።


«አመሰግናለሁ የፍቅራችን ግዜ እጅግ ዉብና ድንቅ ጊዜ ነበር፤ አሁን ወደኋላ ሳይሁን ወደፊት ብቻ ተመልከች» እያለ የተሰናበተችዉን አልያም ለተሰናበታት ፍቅረኛዉ እዉቁ ኦስትርያዊ የሙዚቃ ደራሲና አንቃኝ ኡዶ ዮርገንስ በጎርጎረሳዉያኑ 1966 ዓ,ም እያለ አዚሞአል። ይህ ሙዚቃ አሁንም ከስድስት አስርተ ዓመታት በኋላ እጅግ ተወዳጅ በመሆኑ በአዲሶቹ ትዉልድ ሙዚቀኞችም ይዜማል።
ዛሬ አንድ ያልነዉ የጎርጎረሳዊ 2015 ዓመት ሊገባ በጣት የሚቆጠሩ ቀናቶች ሲቀሩት በጀርመንኛ ቋንቋ ተናጋሪ ማሕበረሰቦች ዘንድ ለስድስት አስርት ዓመታት ተወዳጅነትን ያተረፈዉ ከያኒ ኡዶ ዮርገንስ በድንገት ነበር መሞቱ የተሰማዉ። ኡዱ ዮርገንስ በቅርቡ ሰማንያ ዓመቱን ካከበረ በኋላም ትልቅ የሙዚቃ መድረክን አዘጋጅቶ አፍቃሪዎቹን አስደስቶአል፤ ኡዶ ዮርገንስ በድንገተኛ የልብ ህመም ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ የተሰማዉ ምዕራባዉያኑ የገና በዓልን ሊያከብሩ ሶስት ቀናት ሲቀራቸዉ ነበር።
ኡዶ ከስድሳ ዓመታት በላይ በዘለቀዉ የሙዚቃ ህይወቱ ከ 1000 በላይ ሙዚቃዎችን ደርሶ፤ አብዛኞቹ ሙዚቃዎቹ በተለይ በጀርመንኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ዘንድ ተወዳጅነትና ታዋቂነትን አትርፈዉለታል። በተለይ በጀርመንኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሃገሮች ዎች ዘንድ በሚዘጋጁ ሰፋፊ የሙዚቃ ድግሶች ባህላዊ መድረኮች ላይ የእዉቁ ኦስትርያዊ ሙዚቀኛ የኡዶ ዮርገንስ ስራዎች በመጀመርያ የሚቀርቡ ሙዚቃዎች እንደሆኑም ይታወቃል። ኡዶ የሙዚቃ ስራዎቹን አቅርቦ ከመቶ ሚሊዮን በላይ አልብምን በመሸጡም በመድረክ ላይ ብቻዉን በማቀንቀን እጅግ በርካታ የሙዚቃ ዓልብምን በመሸጥ ስኬታማ ከሆኑ ጥቂት የዓለም ከያኒዎች ረድፍ መሰለፉም ተነግሮለታል።
የምዕራባዉያኑ የገና በዓል ሊከበር ሶስት ቀናት ሲቀረዉ የ 80 ዓመቱ ታዋቂ ሙዚቀኛ ኡዶ ዮርገንስ ስዊዘርላን ካንቶን ቱርጋዉ ግዛት ዉስጥ ሽርሽር እያለ ሳለ ነበር፤ ድንገት ተዝለፍልፎ ወድቆ ነፍሱን የሳተዉ። እንድያም ሆኖ ነፍሱን ለማዳን ወድያዉ ርዳታን ቢቸርም ህይወቱን ማዳን እንልተቻለ እና በልብ ህመም ችግር የመሞቱ ዜና ሲሰማ፤ በአዉሮጳ በሚገኙ የኡዶ ሙዚቃ አፍቃሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ሃዘን ነገሰ፤ የብዙሃን መገናኛዎችም የህይወት ታሪኩን ይዘግቡ ሙዚቃዉንም ከፍ አድርገዉ ያስደምጡ ጀመር።
አርጀንቲና በጎርጎረሳዉያኑ 1978 ዓ,ም የዓለም የእግር ኳስ መድረክን ስታዘጋጅ «ኡዶ ቦኖስ ዲያስ አርጀንቲና» እንደምን ዋልሽ አርጀንቲና በሚል ያወጣዉ ሙዚቃዉ የወርቅ አልብም ተሸላሚ ለመሆን አብቅቶታል፤ ይህንኑ ሙዚቃዉንም በዝያዉ ግዜ ከጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ጋር ሆኖ ማቀንቀኑም ተዘግቦለታል።
ቦክልማን በተሰኘ አካባቢ ኦስትርያ ዉስጥ የተወለደዉ ሙዚቀኛ ኡዶ ዮርገንስ፤ አምስት ዓመት ሲሆነዉ ነዉ በአንድ አርሞኒካ የሙዚቃ ጨዋታን የጀመረዉ። ከዝያም በ 15 ዓመቱ የራሱን የመጀመርያ ሙዚቃ ድርሰትን ፃፈ። በቤተሰቦቹ መኖርያ አካባቢ ለሚገኙ ነዋሪዎች አንዳንድ የስብስብ ምሽት ላይ በግል ሙዚቃን በመጫወት ነዉ የመድረክ ህይወትንም መተዋወቅ የጀመረዉ። ከዝያም ኡዶ በከፍተኛ የትምህርት ተቋም የፒያኖ የጊታር አጨዋወት፤ የሙዚቃ ቅላፂ ትምህርትን ተከታተለ። ኡዶ በወጣትነት ዘመኑ ከሂትለር አድናቂዎች አንድ ግዜ የደረሰበት ከፍተኛ የጥፊ ምት የመስማት ችግር ላይ ጥሎት አለማለፉ፤ ትልቅ እድለኛ እነደሆነ ተዘግቦለታል። በዝያን ጊዜ ይህን አደጋ እድል ብሎት ባይድን ኖሮ እዚህ ታዋቂነትን ያተረፈለት የሙዚቃ መድረክ ላይ ባልተገኘም ነበር ሲባል ተዘግቦአል። ኡዶ ስድሳ ስድስት ዓመት ሲሞላዉ የጡረተኞችን የሚኮረኩር ወደ ጡረታዉ የሚያመራዉንም ወጣት የሚያስፈነድቅ ሙዚቃን ተጫዉቶ ነበር። በስድሳ ስድስት ዓመት ጣፋጩ ህይወት ይጀምራል ሲል፤ በጀርመንኛ ቋንቋ።
በጀርመናዉያን ዘንድ እጅግ ተወዳጅ የሆነዉ ሙዚቀኛ ኡዶ ዮርገንስ ቀደም ሲል በሰጠዉ ቃለ-ምልልሱ
« ወጣት ሳለሁ ጥረቴ ሁሉ የተዋጣለት ሙዚቀኛ መሆን ነበር። የሙዚቃ ተሰጥኦ እንዳለኝ አዉቀዉ ነበር፤ ግን ፍላጎቴ በሙዚቃ ህይወት ኖሪ ራሴን ማኖር ምናልባትም ቤተሰቤን ከዚሁ ከሙዚቃ ገቢዬ መመገብ መቻል ነበር»
ኡዶ በስድሳ ስድስት ዓመቱ የደረሰዉን ሙዚቃ ይዞ « አሁን ካልሆነ መቼም አይሆን» በሚል በጀርመን በተለያዩ ከተሞች ባዘጋጀዉ የሙዚቃ ድግስ አምስት ሚሊዮን ህዝብ ተገኝቶአል። ኡዶ ባለፈዉ ዓመት ባልነዉና፤ በተሰናበትነዉ በጎርጎረሳዉያኑ 2014 ዓ,ም ሰፊ የሙዚቃ ድግሥ በሽዎች ለሚቆጠሩ አድናቂዎቹ በተለያዩ የአዉሮጳ ሃገራት በመዞር አሳይቶአል። በዚህም ኡዶ ለአድናቂዎቹ ከፍተኛ ብሩህ ተስፋን እንደፈነጠቀ ነዉ ተነግሮለታል።
ስዊዘርላንድን መኖርያ ሃገሩ ያደረገዉ ኡዶ ዮርገንስ ፤ ከዚህ ዓለም በሞት በተለየ በሁለተኛዉ ቀን አስክሪኑ ቅርብ ዘመዶቹ ብቻ በተገኙበት መቃጠሉ ተመልክቶአል። ይህ ደግሞ የራሱ ፍላጎት እንደነበረ ነዉ የተገለፀዉ። እንድያም ሆኖ ዛሬ አንድ ባልነዉ የጎርጎረሳዉያኑ ዓመት መጀመርያ ወር መጠናቀቅያ ላይ ይፋዊ የሃዘን ሥነ-ስርዓት እንደሚደረግ ተመልክቶአል ። ትዉልድ ሃገሩ ኦስትርያ በበኩልዋ የኡዶን ዘመናት የማይሽሩትን ሥራዎቹን ይዛ ለከያኒዉ ማስታወሻ ለማቆም ዝግጅት ላይ መሆንዋ ተመልክቶአል።
በመሰናዶዬ መግብያ ላይ ጠቀስ እንዳደረኩት ባሳለፍነዊዉ የጎርጎረሳዉያኑ ዓመት መጨረሻ የጀርመን የሙዚቃ አፍቃሪ በኡዶ ዮርገንስ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ብቻ ሳይ ሆን ያስደነገጠና ያሳዘነዉ፤ ብሪታንያዊዉ የፖፕ ሙዚቃ አንቃኝ የጆ ኮከር ከዚህ ዓለም በሞት መለየት መሰማትም ነበር ኡዶ ዮርገንስ ከዚህ ዓለም በሞት እንደተለየ ከተሰማ ከአንድ ቀን በኋላ ብሪታንያዉ የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ከሳንባ ነቀርሳ በሽታዉ ጋር የጀመረዉን ትግል ማሸነፍ እንዳልቻለ እና ከብዙ ግዜ ህመም በኋላ ማሸለቡ የተሰማዉ።
ጆ ኮከር ልዩ በሆነዉ ድምፁ የብሉዝና የሮኮ ሙዚቃን ሲያቀነቅን በተለይ በምዕራባዉያኑ ዘንድ ያልተለመደ ጎርናና አይነት ድምፁ የሙዚቃ አፍቃሪዎቹን መሳብ ችሏል። በተመስጦ ሲያቀነቅንም ዳንሱ ለየት ያለች በመሆንዋ በዳንሱ ልዩ እዉቅናንም አግኝቶአል።
«with a little help from my friends» በተሰኘዉ በዚህ ሙዚቃ ነበር፤ በጎርጎረሳዉያኑ 1968 ዓ,ም ጆ ኮከር ዓለማቀፍ የሙዚቃ መድረክ የጀመረዉ አሃዱ ያለዉ። የከቢትልስ የሙዚቃ አልበም የተወሰደዉ ይህ የጆ ኮከር ነጠላ ዜማ፤ በዝያን ወቅት በብሪታንያ የሙዚቃ ተወዳጅነት መዘርዝር፤ የመጀመርያዉን ቦታ ይዞ በሌሎች የአዉሮጳ ሃገራትም ተወዳጅነትና ታዋቂነትን አተረፈ። ኮከር በዚህ አላበቃም፤ ይህኑ ሙዚቃዉን ይዞ ወደ ሰሜን አሜሪካ አመራ ። በዩኤስ አሜሪካ ባዘጋጀዉ የሙዚቃ መድረክ ላይ የቴሌቭዥን ጣብያዎችን በመጋበዙ በርካታ የሃገሪቱ ነዋሪዎች፤ ሙዚቃዉን በቀጥታ ስርጭት ሊያዩትና ሊተዋወቁትም በቅተዋል። ይህንኑ ተከትሎ በርካታ የቴሌቭዝን ጣብያዎች ጆ ከርን በመጋበዝ ቃለ መጠይቅ በማድረጋቸዉ ይበልጥ ታዋቂነትን ለማትረፍ መብቃቱ ተመልክቶአል።
መካከለኛ ገቢ ካለዉ ቤተሰብ በጎርጎረሳዉያኑ 1944 ዓ,ም በብሪታንያዋ የኢንዱስትሪ ከተማ ሺፈልድ ዉስጥ የተወለደዉ ጆ ኮከር፤ በአስራ ሁለት ዓመቱ አነስ ያለ መድረክ ላይ ነበር፤ የሙዚቃ ተሰጦዉን ለተመልካች ያሳየዉ።
ጆ ኮከር በ1964 ዓ,ም «I'll Cry Instead» በሚል ያቀረበዉ ነጠላ ዜማ ብዙም ተወዳጅነትን አላገኝም ነበር። ነገር ግን መጀመርያ ያዜመዉ «with a little help from my friends» የተሰኘዉን ሙዚቃ እስከ 1970ዎቹ ድረስ ያለ እረፍት በተለያዩ የሙዚቃ መድረኮች አቅርቦአል። በዚህም ነበር የጭንቀት ችግር ስላጠላበት በአልኮል መጠጥ እና በሱስ አስያዥ እፅ እየተዘፈቀ መምጣቱ ተመልክቶአል።
በ1980ዎቹ መጀመርያ ጆ ኮከር አሜሪካዉን የሙዚቃ ማኔጀር ሚሻኤል ላንግን በማግኘት ዳግም ወደ መድረክ ከፍ መዉጣቱ ተዘግቦአል። ኮከር የተጠመደበትን የአልኮል መጠጥና የእፅ ሱስም ታግሎ እርግፍ አድርጎ ትቶትም ነበር፤ ከዝያም ነዉ ዳግም በዓለም የሙዚቃ መድረክ ተፈላጊነቱና ተወዳጅነቱ እየጎለ የመጣዉ። ኮከር «you can leave your hat on» የተሰኘዉ ሙዚቃ በጀርመን ከዘጠኝ ሳምንታት በላይ የመጀመርያ ዝርዝር ላይ ተቀምጦ በርካታ አልብም ተሸጦለታል። ጆ ኮከር በ1987 ዓ,ም ትዳርን ይዞ ካሊፎርኒያ አካባቢ ራቅ ያለ የእርሻ ቦታ አካባቢ ቤቱን ሰርቶ እየኖረ እንደነበርም ተዘግቦአል። ኮከር ለመጨረሻ ግዜ በጎርጎረሳዉያኑ 2013 ዓ,ም ለመጨረሻ ግዜ ትልቅ የሙዚቃ ድግስን ካሳየ በኋላ የሳንባ በሽታዉ ጠንቶበት ለረጅም ግዜ ህመም ላይ እንደነበር ተመልክቶአል።
መልካም የአዉሮጳዉያኑ 2015 አዲስ ዓመት እያልን ሙሉዉን መሰናዶ የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን ያድምጡ በማለት እንጋብዛለን።

Bildergalerie Joe Cocker 70. Geburtstag
ምስል picture-alliance/dpa
zum 70. Geburtstag - Joe Cocker
ምስል Getty Images/Afp/Samuel Kubani
Singer Joe Cocker Woodstock-Urschrei
ምስል picture-alliance/dpa
Udo Jürgens
ምስል picture-alliance/ dpa
Bildergalerie 80 Jahre Udo Jürgens
ምስል picture-alliance/dpa


አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሃመድ