1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

64ኛዉ በርሊናለ እና «ድፍረት»

ሐሙስ፣ የካቲት 13 2006

የጀርመኑ ዓለም አቀፍ የፊልም መድረክ “በርሊናለ” ዘንድሮ ለ 64ኛ ግዜ የተካሄደ ሲሆን በዓለም ዙሪያ በተለያዩ አገሮች የተሠሩ ከ5000 በላይ ፊልሞች ቀርበዉ በመድረኩ ከ 400 በላይ ፊልሞች ታይተዉበታል። ለአስር ቀናት የዘለቀዉ የጀርመኑ ዓለም አቀፍ ፊልም ፊስቲቫል በኢትዮጵያዉያን የተሠራ ፊልምን፤ አቀርቦ ሸልሞአል።

https://p.dw.com/p/1BCBW
Berlinale Film Difret roter Teppich
ምስል DW

«በርሊናለ» የተሰኝዉ የጀርመኑ ዓለም አቀፉ የፊልም ፊስቲቫል በተለያዪ የዓለም ክፍሎች የተሰሩ ፊልሞችን ብቻ ሳይሆን ለዉድድር ያቀረበዉ የፊልም ተዋናዮችን የፊልም ሥራ ዓዋቂዎችን እና ደራሲዎችንም በመድረኩ አሳትፎአል። የጀርመኑ ዓለም አቀፍ የፊልም መድረክ በርሊናለ ዘንድሮ ለ64ኛ ግዜ ባዘጋጀዉ መድረክ፤ የበርሊን ከተማ መለያ የሆነዉን ዕዉቁን የድብ ቅርጽ ሽልማት የወሰደዉ የቻይናዉ ወንጀል ነክ ድራማ አዘል ፊልም ነበር። ዘንድሮ ኢትዮጵያዉያን የፊልም ተዋናዮች እና የፊልም ስራ ባለሞያዎች በእዉቁ የበርሊናለ የቀይ ምንጣፍ ላይ የኢትዮጵያን ባህል አልባሳት አድርገዉ ከመታየታቸዉም በላይ ይዘዉት የቀረቡት «ድፍረት» የተሰኘዉ ፊልም የበርካቶችን ቀልብ ስቦ ነዉ የሰነበተዉ። ፊልሙ ከርካታ ተመልካቾች ለእይታ እንዲቀርብ ድምፅ በማግኘቱም ሽልማትን አግኝቶአል። በእውነተኛ ታሪክ ላይ ስለተመሠረተው «ድፍረት» ስለተሰኘዉ ፊልም የፊልም መድረኮች ብቻ ሳይሆን፤ በጀርመን የሚገኙ የተለያዩ የብዙሃን መገናኛዎችም፤ ፊልሙ ስለሚተርከዉ፤ በተለይ በኢትዮጵያ ስለሚታየዉ የአስገድዶ ጋብቻና የጠለፋ አጉል ልምድ ላይ ዘግበዋል።
የ«ድፍረት» ፊልም ዋና አዘጋጅ አቶ ዘርእሠናይ ብርሃኔ እና የፊልሙ ተዋናዮችም ጀርመን በሚገኙ በተለያዩ የራድዮ ጣብያዎች እና ጋዜጦች ላይም ፊልሙ ስለሚያስተላልፈዉ መልክት ገለፃን ሰጥተዋል
የፊልሙ ዋና አዘጋጅ አቶ ዘርእሠናይ፤ ከራድዮ ጣብያችን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ፊልሙ በእዉነተኛ ታሪክ ላይ መመርኮዙን ተናግረዋል።
እንደ አቶ ዘርእሠናይ ፊልሙ ኢትዮጵያ ተሰርቶ እንዳለቀ ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ በተዘጋጀ የፊልም ፊስቲቫል በመቀጠል በበርሊኑ ዓለማቀፍ የፊልም መድረክ ከመቅረቡ በስተቀር ገና ብዙ ተመልካች አላየዉም፤ በዚህም ቀጣይ በኢትዮጵያ የፊልም መድረኮች እንደሚታይ ተናግረዋል። ሌላዋ የበርሊናለ ዓለማቀፍ የፊልም መድረክ እንግዳ የህግ ባለሞያዋ ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ በሃገራችን የሚካሄደዉ አጉል የጠለፋ ልማድ መቀነሱን በበርሊናለዉ የዓለማቀፍ የፊልም መድረክ ገልፀዋል።
በጀርመን በበርሊን ከተማ ላይ ቤተ- ኢትዮጵያ በተሰኘ ምግብ ቤታቸዉ፤ የኢትዮጵያን ባህላዊ ምግብ ፤ አልባሳትና የተለያዩ ባህላዊ ክብረ ባአላትን በማስተዋወቃቸዉ የሚታወቁት ወ/ሮ አሰገደች ደምሴ በበርሊናለዉ ዓለማቀፍ የፊልም መድረክ ተገኝተዉ ከኢትዮጵያዉን ድፍረት የተሰኘዉን ፊልም ተመልክተዉ አስተያየታቸዉን ሰተዉናል። ሌላዉ የበርሊን ነዋሪ አቶ ኤልያስ ደምሴም « ድፍረት » የተሰኘዉን የኢትዮጵያዉያን ፊልም አይተዉ ስለፊልሙ ጥራት መደነቃቸዉን እንዲሁም መልክቱ በተለይ ኢትዮጵያዉያን በሴት እህቶቻችን ላይ የሚደርሰዉን ጉዳት እንድናጤንና እንድንወያይበት የሚነሳሳን ነዉ ሲሉ ተናግረዋል። የዓለም የሲኒማ መድረክ ሆና የሰነበተችዉ የጀርመን መዲና በርሊን፤ ከቻይና የቀረበዉ ፊልም 64 ኛዉን የበርሊናለ ዉድድር በማሸነፉ፤ እዉቁን የወርቅ ድብ ቅርጽ ሽልማት፤ ለቻይናዉያኑ የፊልም ስራ አዋቂዎች አበርክታለች።

በርሊናለ የዛሪ ስድሳ አራት ዓመት ጀርመን በምስራቅ እና በምዕራቡ ርእዮተ ዓለም ተከፍላ፤ በርሊን ምስራቅ ጀርመንን ጨምሮ ሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም በሚከተሉ ሃገሮች ተከባ ሳለ፤ በርሊን የምዕራቡን ዓለም ሃገራት የፊልም ታዳሚዎች በመጋበዝ የፊልም ስራን ለማሳደግ፣ የባህል ልዉዉጥ በማድረግ የዓለም አቀፍ መድረክዋን ዘርግታለች። ከጎርጎረሳዊዉ 1951 እስከ 1966 ዓ,ም ድረስ፤ የበርሊን ከንቲባ የነበሩትና ከዝያም የምዕራብ ጀርመን ርዕሰ ብሄር የነበሩት ቪሊ ብራንት፤ በበርሊን ዛሪ የሚታየዉን በዓለም ሃገራት የሚንጸባረቅን፤ ባህል ፣ ፖለቲካ ፣ ነቀፊታን አልያም ተጽኖን የሚዳስሱ የተለያዩ እዉቀቶችን ያዘሉ ፊልሞች ለህዝብ እይታ እንዲበቁ፤ ዓለማቀፍ የፊልም መድረክ የመክፈት መሰረቱን መጣላቸዉ ይታወቃል። ቢሆንም ግን የፊልም ስራዎችን ከተለያዩ ሃገሮች በማስመጣት ስራዉን የጀመረዉ፤ በዝያን ግዜ አንድ አሜሪካዊ የፊልም ስራ አዋቂ የፖሊስ አዛዥ እንደነበረ ዘገባዎች ያሳያሉ። በመጀመርያዉ የበርሊናለ የዓለም አቀፍ የፊልም መድረክ፤ የዛሪ ስድሳ አራት ዓመት፤ ከ 36 ዓለም አገራት የተሰሩ ፊልሞች የታዩበት መድረክ እንደነበር ተዘግቦአል። በየዓመቱ በጀርመን መዲና በርሊን ላይ በሚካሄደዉ ዓለማቀፍ የፊልም ፊስቲቫል በርሊናለ ላይ ኢትዮጵያዉያን የፊልም ስራ አዋቂዎች ባህላዊ ገፅታን የሚያስተዋዉቁ ፊልሞችን ይዘዉ እንዲቀርቡ ድጋፍ አይለያቸዉ በማለት በለቱ ዝግጅት ቃለ ምልልስ የሰጡንን በሙሉ በዶቼ ቬለ ስም እናመሰግናለን። ሙሉዉን ቅንብር የድምፅ ማድመጫዉን በመጫን ያድምጡ።

አዜብ ታደሰ
ተክሌ የኋላ

Berlinale Film Difret
ምስል DW
Berlinale 2014 Filmstill Difret NO SOCIAL MEDIA
ምስል Berlinale
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ