1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

700 ስደተኞችን የያዘች መርከብ ሰመጠች

ዓርብ፣ ግንቦት 26 2008

በሜዲተራንያን ባህር ደቡባዊ ክሬታ አዋሳኝ ላይ አንድ 700 ሰዎችን አሳፍራ ትቀዝፍ የነበረ ጀልባ መስመጥዋ ተመለከተ። የግሪክ የባህር ወደብ ጠባቂዎች መግለጫ እስካሁን ጀልባዉ ላይ የነበሩ ወደ 300 የሚሆኑ ሰዎችን ሕይወት ማትረፍ ተችሎአል።

https://p.dw.com/p/1J0HR
Mittelmeer Libyen Flüchtlingsboot Rettungsaktion
ምስል Reuters/Marina Militare

እንደ የግሪክ የብዙኃን መገናኛዎች የግሪክ የባህር ወደብ ጠባቂዎችን ዋቢ በማድረግ እንደዘገቡት እስካሁን የሦስት ሰዎች አስክሪን ተገኝቶአል። በዘገባዉ መሠረት በገሚስ በተሰበረችዉ መርከብ ላይ አሁንም ሰዎች ይገኛሉ። የነፍስ አዳኝ ቡድኑ የመርከቡን ገሚስ እየፈለገ መሆኑም ተያይዞ ተዘግቦአል። የሰመጠችው ጀልባ ከግብጽ የባህር ወደብ ሳትነሳ እንዳልቀረ ነዉ የተገመተዉ።

ባለፈዉ ሳምንት የሜድትራኒያን ባሕርን አቋርጠዉ ወደ አዉሮጳ ለመግባት ሲሞክሩ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 1000 መድረሱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማስታወቁ ይታወቃል። ዓለም አቀፉ የስደተኞች መርጃ ድርጅት «UNHCR» እንደሚለዉ የጎርጎረሳዉያኑ 2016 ከባተ ጀምሮ ባንድ ሳምንት በርካታ ስደተኞች ሲያልቁ ያለፈዉ ሳምንቱ ከፍተኛዉ ነዉ።የኢጣሊያ መንግሥት በበኩሉ ስደተኞቹን ለማዳንና ለመርዳት የአዉሮጳ ሕብረት እንዲተባበረዉ ላቀረበዉ ጥያቄ ሕብረቱ ተገቢ መልስ አልሰጠም በማለት ወቅሶታል። በተያያዘ ዜና የኢጣሊያ ፀጥታ አስከባሪዎች 16 ስደተኛ አሸጋጋሪዎች መያዛቸዉን አስታዉቀዋል።አንዱ ኢትዮጵያዊ ነዉ።


አዜብ ታደሰ
አርያም ተክሌ