1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

ተመራማሪው ክትባት ለማግኘት ተስፋ ሰንቀዋል

ረቡዕ፣ ኅዳር 6 2010

ለተለያዩ ምርምሮች ወደ ህዋ የሚጓዙ ጠፈርተኞች ውኃ የሚያገኙት ከመንኮራኩራቸው ማጠራቀሚያ እየወሰዱ ነው፡፡ በውኃ ማጠራቀሚያ ውስጥ ራሳቸውን ሸሸገው የሚቆዩት በዓይን የማይታዩ ጀርሞች ጠፈርተኞችን ለበሽታ ሲያጋልጣቸው ቆይተዋል፡፡ የእነዚህን ጀርሞች ባህሪ ለበርካታ ዓመታት ሲያጠኑ የቆዩ አንድ ኢትዮጵያዊ ምሁር ክትባት ለማግኘት ተስፋ አድርገዋል፡፡

https://p.dw.com/p/2nhcn
Tesfaye Belay, äthiopischer Wissenschaftler
ምስል privat

ተመራማሪው ክትባት ለማግኘት ተስፋ ሰንቀዋል

በአሜሪካው የጠፈር ምርምር ተቋም (ናሳ) በጠፈርተኝነት ለመሰልጠን በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በየዓመቱ ማመልከቻቸውን ያስገባሉ፡፡ ተቋሙ ለጎርጎሮሳዊው ለ2017 የስልጠና መርሃ ግብሩ የተቀበላቸው 18‚300 ማመልከቻዎች ከምንጊዜውም በላይ የላቁ ነበር ብሏል፡፡ ናሳ ከዚህ ሁሉ አመልካቾች ውስጥ አወዳድሮ የመረጣቸው ግን አስራ ሁለቱን ብቻ ነው፡፡ ቁጥሩ ያነሰ ቢመስልም ተቋሙ ባለፉት 17 ዓመታት ይህን ያህል ሰልጣኞች በአንዴ ተቀብሎ አያውቅም፡፡ እነዚህ ሰልጣኝ ጠፈርተኞች የሁለት ዓመት ስልጠና ከወሰዱ በኋላ በናሳ የተለያዩ የህዋ ተልዕኮዎች ላይ እንደሚሳተፉ ተገልጿል፡፡ 

NASA Astronauten
ምስል picture-alliance/Newscom

ወደ ህዋ የሚጓዙ ጠፈርተኞች በአንድ ተልዕኳቸው በትንሹ ለስድስት ወር ይቆያሉ፡፡ እስካሁን በህዋ ረጅም ጊዜ በመቆየት ክብረ ወሰኑን የያዙት የሩሲያው ጠፈርተኛ ቫለሪ ፖሊያኮቭ 437 ቀናት ከምድር ተለያይተዋል፡፡ የጠፈር ጉዞ ለብዙዎች አጓጊ ቢሆንም በጠፈርተኞች ላይ የሚያስከትለው የጤና እክል በህዋ የሚደረገውን ቆይታ እንዲያጥር አድርጎታል፡፡ የአሜሪካንን የጠፈር የቆይታ ክብረ ወሰንን ባለፈው ዓመት ያሻሻሉት ስኮት ኬሊ በህዋ ላይ መቆየት የቻሉት 340 ቀናት ብቻ ነው፡፡ የናሳ ተመራማሪዎች የኬሊን ወደ አንድ ዓመት የተጠጋ ቆይታ ጠፈርተኞች በህዋ ላይ ቆይታቸው የሚያደርስባቸውን አካላዊ እና ስነ ልቦናዊ ተጽዕኖዎች ለመርመር ተጠቅመውበታል፡፡ 

የጠፈርተኞቹ ደህንነት የሚያሳስበው ናሳ ከራሱ ተመራማሪዎች ባሻገር በጠፈርተኞች ጤና ዙሪያ በግላቸው ምርምር የሚያደርጉ ግለሰቦችን በገንዘብ ይደግፋል፡፡ ከእነዚህ ተመራማሪዎች መካከል ኢትዮጵያዊው ፕሮፌሰር ተስፋዬ በላይ አንዱ ናቸው፡፡ ምዕራብ ቨርጂኒያ በሚገኘው ብሉፊልድ ስቴት ኮሌጅ መምህር ፕሮፌሰር ተስፋዬ ጠፈርተኞችን ለበሽታ በሚዳርግ ጀርም ላይ ላለፉት 10 ዓመታት ምርምር እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ናሳ ለዚህ ምርምራቸው እስካሁን የ100 ሺህ ዶላር የገንዘብ ድጋፍ አድርጎላቸዋል፡፡ ወደ ህዋ በሚጓዙ መንኮራኩሮች ላይ ስለማይጠፋው የጀርም አይነት ፕሮፌሰር ተስፋዬ አጭር ገለጻ አላቸው፡፡ 

“እኔ የማጠናው ጀርም psedomunas aeruginosa የተባለ ጀርም ነው፡፡ ዋናው ጠባዩ በውሃ መኖር የሚወድ ጀርም ነው፡፡ ለምሳሌ መታጠቢያ ቤት ውስጥ ወይም ሽንት ቤት ውስጥ የሳሙና ፍሳሽ ያለበት ቦታ መኖር ተደራርቦ መኖር ይወዳል፡፡ Biofilm formation ይባላል፡፡ እንደ ሻጋታ ነገር ነው፡፡ ሻወራችንን በየጊዜው ካላጠብነው እዚያ ውስጥ ይሻግታል፡፡ እንደ ፊልም ነገር ባክቴሪያ በመፍጠር ለብዙ ጊዜ መቆየት ይችላሉ” ሲሉ የጀርሙን መለያዎች ይገልጻሉ፡፡ 

Apollo 13 gerettet
ምስል AP

የእነዚህ ጀርሞች አስደናቂ ባህሪ በምድር ላይ ባሉ ቦታዎች ብቻ ሳይሆን ወደ ጠፈር በሚላኩ መንኮራኮሮች ላይ ለረጅም ጊዜ በህይወት መቆየታቸው ነው፡፡ በህይወት ለመቆየት ውሃማ ቦታ እንደመምረጣቸው በመንኮራኮር ውስጥም የውሃ ማጠራቀሚያ እና ማስተላለፊያዎችን የሙጥኝ ብለው ይሰነብታሉ፡፡ የእነዚህ ጀርሞች በመንኮራኮር ውስጥ መኖር የተደረሰበት በጎርጎሮሳዊው 1970 ወደ ጠፈር በተላከው ታሪካዊው የአፖሎ 13 ተልዕኮ ወቅት ነበር፡፡ በዚህ መንኮራኮር በህዋ ላይ ለስድስት ቀናት ቆይታ አድርገው ከተመለሱ ሶስት ጠፈርተኞች ውስጥ አንደኛው የኩላሊት በሽታ መጠቃቱ ነበር ለጀርሞቹ መገኘት መንስኤ የሆነው፡፡

“ያኔ ተመራምረው ምንድነው ያገኙት? ከሚጠጣው ውሃ ይህ በሽታ እንደያዘው አወቁ ማለት ነው፡፡ ይሄ ባክቴሪያ ወይም ጀርም የመንኮራኮሩ ቱቦ ላይ ተጣብቆ መኖር ይወርዳል፡፡ እንግዲህ አነዚህ ጠፈርተኞቹ ወደ ጠፈር በመሄዱበት ጊዜ ብዙ የሚያስጨንቃቸው ነገር አለ፣ የአካባቢው ሁኔታ ያጨናንቃቸዋል፡፡ የሰውነታቸው የመከላከያ አቅም በጣም ዝቅ ስለሚል በቀላሉ ይታመማሉ፡፡ ይሄ ሰውዬ ይሄን በሽታ ከያዘው በኋላ ከሚጠጣው ውሃ መሆኑን አወቁ ማለት ነው፡፡  እና ይህ በሚሆንበት ጊዜ የአሜሪካ የጠፈር ጥናት ክፍል ወይም ደግሞ ናሳ የጠፈርተኞችን ጤንነት ለመቆጣጠር ጥናቱን በሰፊው ጀመረ” ሲሉ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ያስረዳሉ፡፡ 

ኢትዮጵያዊው ተመራማሪ ከ10 ዓመት በፊት የጀመሩት ምርምር በሽታ የሚያስከትለው ጀርም በውሃ ውስጥ ስላለው ቆይታ እና በሚያሳያቸው ለውጦች ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ምርምራቸውን ሲጀምሩ ወደ 100 ሚሊዮን የሚጠጉ የባክቴሪያ ህዋሶችን በአንድ ትልቅ የቤተ ሙከራ ጠርሙስ ውስጥ በውሃ በማስቀመጥ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ባክቴሪያዎቹ የተቀመጡበት ውሃ ንጹህ እና ከሌሎች ጀርሞች ንኪኪ ነጻ እንዲሆን መደረጉን ያስረዳሉ፡፡ ለ10 ዓመት ያህል አየር ብቻ እንዲያገኙ ከተደረጉ እነዚህ ባክቴሪያዎች አሁንም በህይወት እንዳሉ ይናገራሉ፡፡

“እስካሁን ውሃ ውስጥ የተቀመጠው ባክቲሪየም ወይም ጀርም አልሞተም፡፡ ምንም የምንሰጠው ምግብ የለም፡፡ ውሃ ውስጥ ዝም ብሎ ይቀመጣል እና እንዴት እንደሚኖር ብዙ ቤተ ሙከራዎች ጥናት እያደረጉ ነው፡፡ ከየት መጥቶ ነው ይሄ ባክቴሪያ አለምግብ እዚህ መኖር የሚችለው የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ብዙ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ እና ሌላው ያደረግነው ነገር ይሄ የተራበው ጀርም የቤተሙከራ አይጦች በምን ሁኔታ ይገላል ብለን ስንጠይቅ የመግደሉ ኃይል ቀነሶ አገኘነው፡፡ ሌላው ደግሞ የተሰራበት genom sequence የሚባል እርሱ ሁሉ ተቀየረ፡፡ ወደ 18 ሺህ አቀማመጥ ተቀይሮ አየነው፡፡ ሌላው ነገር ደግሞ 22 ባህሪያት ወይም ጂኖች ጠፍተው አገኘናቸው፡፡

Symbolbild Grundsatzurteil USA zur Patentierung menschlichen Erbguts
ምስል Fotolia/Vasiliy Koval

ይህ እንዴት ነው ሊሆን የቻለው? በሚል ጥናታችንን በመቀጠል በአሁኑ ጊዜ 10 ዘሮች (strains ይባላሉ) ውሃ ውስጥ እየተራቡ ናቸው ያሉት፡፡ በሚቀጥለው ሶስት ወር ውስጥ ጠቅላላ ከመጀመሪያው ዋናው ዘር ጀምሮ የተራቡት ጀርሞች ምን ዓይነት ለውጥ አላቸው የሚለውን በመስራት ላይ እንገኛለን፡፡ የሚቀጥለው ይሄንን ከዋናው ዘር ጋር እናወዳድረዋለን፡፡ ካወዳድረን በኋላ በተለይ ይሄ የተራበው ብዙ አይጥ ስለማይገድል አንድ መጥፎ ክፍል ጠፍቷል ማለት ነው እና ይሄ ለክትባት ሊያገለግል ይችላል ወይ የሚለውን ጥያቄ በሚቀጥለው ጊዜ ለማጥናት እየተዘጋጀን ነው ያለነው” ሲሉ ፕሮፌሰር ተስፋዬ የወደፊት የምርምር ትኩረታቸውን ያስረዳሉ፡፡    

ለዚህ ጀርም ክትባት ተገኘ ማለት ጠፈርተኞቹን የሚያስቸግረውን የኩላሊት በሽታ ጨምሮ የሚያስከትላቸውን በርካታ በሽታዎች መከላከል ማለት እንደሆነ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ያብራራሉ፡፡ በዚህ ጀርም ምክንያት በማንኛውም ሰው ሊከሰት የሚችሉ በሽታዎች እንዲህ ይዘረዝሯቸዋል፡፡ “በሰዎች ላይ ለምሳሌ ሲስቲክ ፊብሮሲስ የሚባል የሳንባ በሽታ አለ፡፡ እና ይሄ ባክቴሪያ በሳንባችን ላይ ያንን አይነት ሻጋታ ይፈጥራል፡፡ በፎርሜሽን በጣም የታወቀ ነው፡፡ ስለዚህ ኒሞኒያ እና ዊንድ ኢንፌክሽን ያስከትላል፡፡ የፈለገውን አይነት በሽታ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ሰውነትህ ትንሽ የመላከል ድካም ያለበት ከሆነ ለምሳሌ ኤች አይ ቪ ያለበት ሰው ይሄ በሽታ ሊያጠቃው ይችላል፡፡ ምክንያቱም ሰውነቱ የመከላከል አቅም የለውም፡፡ 

በመሬት ላይ ሆስፒታል ውስጥ አንቲባዮቲክስ በጣም ይጠቀማሉ፡፡ ይሄ ጀርም በጣም የመቋቋም ችሎታ አለው፡፡ ስለዚህ የተለያዩ በሽተኞች በተለይ በሆስፒታል ውስጥ ያሉ ሽማግሌዎች በዚህ በሽታ በቀላሉ ሊጠቁ ይችላሉ፡፡ አንድ ሰው በእሳት ቃጠሎ ቁስል በሚኖርበት ጊዜ ባክቴሪያው ቁስሉ ላይ ሄዶ ሻጋታ ነገር (ፊልም) ይሰራል፡፡ ይህን ሻጋታ ነገር የሚሰራው የሰውነታችን ሴሎች እንዳይገሉት እንደዚሁም ደግሞ ሃኪም የሚሰጠንን እንደ መድኃኒት ነገር እንዳይገለው ነው፡፡ ተደራርቦ ነው የሚበቅሉት፡፡ የሆነ መድኃኒት ከላይ ብታደርግለት ላይ ያለውን ብቻ ነው ይገላል እንጂ ታች ያለውን አያገኘውም፡፡ ስለዚህ ባክቴሪያው አይሞትም” ሲሉ ተመራማሪው ያብራራሉ፡፡

NASA-Logo
ምስል picture-alliance/dpa/EPA/A. M. Sprecher

እንዲህ አይነት በሽታዎችን ለመከላከል ምርመራቸው እየጠቆማቸው ያለው ክትባት መፍትሄ ይሆን?  ፕሮፌሰር ተስፋዬ ምላሽ አላቸው “ክትባቱ ምንድነው? ለምሳሌ ወደ ጠፈር የሚሄዱ ከሆነ ይሄን ክትባቱን አስቀድመህ ትሰጣለህ፡፡ ስለዚህ ክትባቱ ሰውነትህ ውስጥ መከላከያ መንገድ ይፈጥራል ማለት ነው፡፡ እና ሰዎቹ ለወደፊቱ ላይታመሙ ይችላሉ፤ በመሬት ላይም ሊያገለግል ይችላል፡፡ አብዛኛው ህክምና እኮ ክትባት ከተደረገለት የመቆጣጠር ዘዴ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ በአሁኑ ጊዜ ፈንጣጣ ከዓለም ውስጥ ጠፍቷል፡፡ የጠፋው በክትባት ነው፡፡ እና ይሄ ጀርም የተለያዩ ቅርጾቹ ከታወቁ ክትባት ለማዘጋጀት ተስፋ ሊኖር ይችላል ማለት ነው፡፡  

በሽታ አምጪውን ጀርም ለመከላከል የሚሆን ክትባት የማግኘቱ ጉዳይ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ፕሮፌሰር ተስፋዬ ይናገራሉ፡፡ መቼ ለአገልግሎት ይውላል? በሚለው ላይ ግን በምርምር ላይ ስለሆነ ቁርጥ ያለ መልስ መስጠት ያስቸግራል ባይ ናቸው፡፡  “ምርምር በጣም ብዙ ጊዜ ይፈጃል፡፡ በዓመት ወይም ሁለት ዓመት እንደዚህ ስራ ላይ ይውላል ማለት አይደለም፡፡ ግን ጥናቱን የምቀጥልበት ሁኔታዎች እየታዩ ነው፡፡ ግን ይሄ እውነቴን ነው የምልህ ይሄንን የናሳን የማሳያ ፕሮጀክት ብዙ ትኩረት አለበት፡፡ ብዙ ሰዎች ይወዱታል፡፡ ወደ ስብሰባ በምወስድበት ጊዜ እና ተማሪዎች ወስደው በሚያቀርቡበት ጊዜ ህዋ ላይ የሚሄዱ ጠፈርተኞች ራሳቸው በጣም ነው የሚገርማቸው፡፡ የባክቴሪያው ባህሪ መቀየር በጣም ነው የሚስባቸው፡፡ እና አንድ ቀን ትልቅ ደረጃ ላይ ሳይደርስ አይቀርም” ሲሉ ተስፋቸውን በፈገግታ ታጅበው ያጋራሉ፡፡ 

ተስፋለም ወልደየስ

ሂሩት መለሰ