1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሐራሬ፤ የሐራሬ ጎዳናዎች በወታደራዊ አጀብ እየተቃኙ ነዉ

ሐሙስ፣ ኅዳር 7 2010

የዚምባቡዌ ዋና ከተማ ሐራሬ ጎዳናዎች በወታደራዊ ተሽከርካሪዎች እየተቃኙ መሆኑን ዘገባዎች ያመለክታሉ። ዛሬ ማለዳ የሀገሪቱ ዜጎች ከቤታቸዉ ሲወጡ በየመንገዶቹ ወታደሮች መሠማራታቸዉን ማየታቸዉ እና ፕሬዝደንት ሮበርት ሙጋቤም በመኖሪያ ቤታቸዉ በቁም እስር ላይ እንደሚገኙ መስማታቸዉም ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/2nlms
Simbabwe Krise Straßenszenen aus Harare
ምስል Reuters/P. Bulawayo

የዚምባቡዌ  ምክር ቤትም በወታደሮች ቢከበብም የሕዝቡ ዕለታዊ ተግባር ግን እንዳልተስተጓጎለ ነዉ የተነገረዉ። ዛሬ ጠዋት ሲወጡ ያጋጠማቸዉን ማንነታቸዉ እንዲገለጽ ያልፈለጉ የሐራሬ ነዋሪ እንዲህ ይገልጹታል፤

«ታዉቃለህ ዛሬ ወደ ከተማ ስመጣ፤ እንዲህ ያለ የፀጥታ ፍተሻ በሕይወቴ አጋጥሞኝ አያዉቅም። ሰዉ በጣም ተደስቷል። የስኮች ጠርሙሶቹን በማዘጋጀትም ለደስታ እና ፈንጠዝያ እየተሰናዳ ነዉ። ታዉቃለህ ምክንያቱም ምንም ቢሆን፤ የትኛዉም አይነት ለዉጥ ባለፉት 20 ዓመታት ከነበርነት ሁኔታ በጣም ይሻላል።»

ሮይተርስ እንደዘገበዉም የ93 ዓመቱ ፕሬዝደንት ሮበርት  ሙጋቤ የሀገሪቱ ሕጋዊ መሪ እሳቸዉ መሆናቸዉን በአፅንኦት በመግለፅ በካቶሊክ ካህን አማካኝነት ለተሞከረዉ ሽምግልና አሻፈረኝ ብለዋል። በፕሬዝደንቱ እና በቁም እስር ባስቀመጧቸዉ ወታደራዊ ጀነራሎች  መካከል ሽምግልናዉን የሚያካሂዱት ቄስ ፊደሊስ ሙኮኖሪ መሆናቸዉን ስማቸዉ ያልተገለፀ የሮይተርስ የዜና ምንጭ ጠቁመዋል። ቀድሞ የዚምባቡዌ የስለላ ተቋም ኃላፊ የነበሩት እና ከምክትል ፕሬዝደንትነታቸዉ በሙጋቤ በቅርቡ የተባረሩት ኢመርሰን ምናንጋግዋ፤ ሙጋቤ ከስልጣን ከተነሱ በኋላ ያለ ምንም ደም መፋሰስ የጦር ኃይሉ እንዴት መንቀሳቀስ እንዳለበት እቅድ እየነደፉ መሆናቸዉንም ሮይተርስ ያገኘዉን መረጃ መሠረት አድርጎ ዘግቧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የአፍሪቃ ኅብረት ዚምባቡዌ ዉስጥ የተከናወነዉን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት እንደማይቀበል አስታዉቋል። ይህን ያስታወቁት የኅብረቱ ሊቀ መንበር አልፋ ኮንዴ፤ የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት እንዲከበር፤ ሕገ መንግሥታዊዉ ሥርዓት ወደ ቦታዉ እንዲመለስ እና በምንም መንገድ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥትን ኅብረቱ እንደማይቀበል ከፈረንሳይ ጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ መግለጻቸዉን አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ከፓሪስ ዘግቧል። ዉስጣዊ ችግር መኖሩን እናዉቃለን ያሉት ኮንዴ፤ መፍትሄ ሊያገኙ እሚገባዉ በዛኑ ፒ ኤፍ ፓርቲ አማካኝነት በፖለቲካዊ መንገድ እንጂ በወታደራዊ ጣልቃ ገብነት መሆን እንደሌለበትም አሳስበዋል። በአፍሪቃ ኅብረት የቻድ አምባሳደር እና የኅብረቱ የሰላም እና ፀጥታ ምክር ቤት ሊቀ መንበር ቻሪፍ ማማት ዜኔ፤ በበኩላቸዉ ለዶቼ ቬለ በጉዳዩ ላይ ተከታዩን ብለዋል።

Zitattafel Alpha Condé Präsident der Afrikanischen Union

«እንደምታዉቁት ሁሉ የአፍሪቃ ኅብረት የኮሚሽኑ ፕሬዝደንት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተዉት አቋማቸዉን ገልጸዋል። በመርህ ደረጃ የአፍሪቃ ኅብረት ማንኛዉንም ከሕገ መንግሥታዊ ዉች የሚደረገዉን ማንኛዉንም ለዉጥ ይቃወማል። ይህ በመርህ ደረጃ ነዉ፤ ስለዚህ ይህንን የሚመለከተዉ የደቡባዊ አፍሪቃ ሃገራት የልማት ተቋም ፕሬዝደንቱ የሽምግልናዉን ተግባራቸዉን ጀምረዋል። የአፍሪቃ ኅብረት የሰላምና የፀጥታዉ ኮሚሽን ማንኛዉንም የመጨረሻዉን አቋሙን የሚወስደዉ የደቡባዊ የማኅበረሰቡ ተቋም ፕሬዝደንት ዘገባቸዉን ካጠናቀቁ በኋላ ነዉ።»

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ