1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

"ሕገ-መንግሥቱ የታሰረ ሰው ግረፉ ይላል እንዴ?" ጠቅላይ ምኒስትር አብይ

ሰኞ፣ ሰኔ 11 2010

ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ መንግሥታቸውን ለመጣል በኤርትራ የመሸጉ ተቃዋሚዎቻቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል፤ በመንግሥቱ የተለያዩ መዋቅሮች ስቅየት ይፈጸም እንደነበር አስረድተዋል፤ በአገሪቱ ተፈጥሯል ያሉትን መግባባት፣ መነቃቃት፣ ሰላም፣ መረጋጋት እና አንድነት "ወደ ኋላ ለመመለስ የሚጥሩ ግለሰቦች እና ቡድኖች" አሉ ሲሉም ወቅሰዋል።

https://p.dw.com/p/2zo4W
Addis Abeba, Äthiopien, Äthiopischer Premierminister Abiy Ahmed im Parlament
ምስል DW/Y.Geberegziabher

Ber. A.A ( Dr Abyi Ahmed) - MP3-Stereo

ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ በተለያዩ እርከኖች በሚገኙ የመንግሥት መዋቅሮች ስቅየት ይፈጸም እንደነበር ተናግረዋል። ጠቅላይ ምኒስትሩ ከተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት "ሽብር ሥልጣን ላይ ለመቆየት ኢ-ሕገመንግሥታዊ በሆነ መንገድ ኃይል መጠቀምን ይጨምራል። ሽብር ሥልጣን ለመያዝ አለአግባብ ኃይል መጠቀምን ይጨምራል። ምንም ይሁን ማን ሕገ-መንግሥትን ማክበር አለበት የሚል እሳቤ መያዝ ያስፈልጋል። ኃላፊነትን የሚሰማን መንግሥት ስንሆን ደግሞ የዚህ ጉዳይ መዛነፍ ኃላፊነት መውሰድ ያለብን እኛ ነን" ብለዋል።

"ሕገ-መንግሥቱ የደኅንነት ተቋማት መከላከያውን ጨምሮ ከፓርቲ ገለልተኛ ሆነው ሕግ እና አገር የሚጠብቁ መሆን አለባቸው ብሎ ያስገድዳል። እኛ ያደራጀንው እንደዛ ነውይ?" ሲሉ የጠየቁት ጠቅላይ ምኒስትሩ "እንደዛ ካላደራጀንው ኢ-ሕገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ ተቋም ፈጥረናል ማለት ነው" ሲሉ ተደምጠዋል። "ሕገ-መንግሥቱ በፍርድ ቤት የታሰረ ሰው ግረፉ፣ ጭለማ ቤት አስቀምጡ ይላል እንዴ? አካል ማጉደል የእኛ የአሸባሪነት ተግባር ነው። ይኼን ሕገመንግሥታዊ ያልሆነ ድርጊት በእያንዳንዱ ቀበሌ በእያንዳንዱ ወረዳ በእያንዳንዱ ዞን ሲፈጸም ቆይቷል። በፌድራል መንግሥት ብቻ ሳይሆን በሁሉም ቀጠናዎች። የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ያጠናውን ሪፖርት ታውቃላችሁ። የየወረዳው ፖሊስ ሲገርፍ ነበር። ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ነው። አሸባሪ ነው እሱ ፖሊስ" ሲሉ ፈርጠም ብለው ተናግረዋል።

Addis Abeba, Äthiopien, Äthiopischer Premierminister Abiy Ahmed im Parlament
ምስል DW/Y.Geberegziabher

ጠቅላይ ምኒስትሩ ነፍጥ አንግበው መንግሥታቸውን ለመጣል ኤርትራ የገቡ ተቃዋሚዎች እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል። አብይ "ኤርትራ ያላችሁ ወገኖቻችን የያዛችሁት መንገድ በጣም ያረጀ ፋሽን ስለሆነ ለኢትዮጵያም ስለማይጠቅም በሰላም አገራችሁ መጥታችሁ በድርድር፤ በንግግር በውይይት ብቻ መሸናነፍ የሚሆንላት አገር እንፍጠር" ብለዋል።

ጠቅላይ ምኒስትሩ በንግግራቸውም ሆነ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በቀረቡላቸው ጥያቄዎች ኢትዮጵያ የገጠሟትን አንገብጋቢ ጉዳዮች አንስተዋል። የአገራቸው ኤኮኖሚ የገጠመውን ፈተና፤ የፖለቲካውን ውጥንቅጥ፣ የፍትኅ ሥርዓቱን ችግሮች፣ ስለ ሙስናና በተለያዩ አካባቢዎች ስለሚታዩ ግጭቶች ማብራሪያ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ምኒስትሩ እንዳሉት በ2010 ዓ.ም. የመጀመሪያ ስድስት ወራት ብቻ ኢትዮጵያ 688 ሚሊዮን ዶላር ለዕዳ ስትከፍል 1.3 ቢሊዮን ዶላር ተበድራለች። አጠቃላይ የአገሪቱ የብድር መጠን ደግሞ ወደ 24.7 ቢሊዮን ዶላር አሻቅቧል።

ዮሐንስ ገብረ እግዚዓብሔር

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ