1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«መከላከያ» ከወልድያ እንዲወጣ ወጣቶች መጠየቃቸዉ 

Merga Yonas Bula
ሰኞ፣ ጥር 14 2010

በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን ወልደያ ከተማ ቅዳሜ ዕለት የቃና ዘገሊላን በዓል እያከበሩ በነበሩ ወጣቶች እና በፀጥታ አስከባሪ ኃይሎች መካከል በተፈጠረ ግጭት የሰባት ሰዎች ሕይወት እንዳለፈ እና 15 ሰዎችም እንደተጎዱ የክልሉ የመንግሥት ኃላፊዎች ይፋ አድርገዋል።

https://p.dw.com/p/2rJzI
Karte Äthiopien Amhara, Tigray, Oromia Englisch

Waldiya youth request military to leave - MP3-Stereo

አለመረጋጋቱ ትናንትም ቀጥሎ እንደዋለ ከአካባቢዉ እማኞች ለዶቼ ቬለ አመልክተዋል። የአማራ ክልል ርዕሰ-መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸዉ ትላንት ምሽት ከአማራ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ከአካባቢዉ ሽማግሌዎች ጋር በመሆን ወጣቶቹን እንዳወያዩ ተናግረዋል።

ወጣቶቹ ካቀረቧቸዉ ጥያቄዎች አንዱ የመከላከያ ኃይል ከተማዋን ለቆ እንዲወጣ የሚል እንደሆነ ይህንንም ጉዳይ ትናንት ከአቶ ገዱ ጋር መነጋገራቸዉን ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የከተማዋ ነዋሪ ለዶይቼ ቬሌ ተናግሯል። ወጣቶቹ ትናንት ከርዕሰ መሰተዳደሩ ጋር  ያደረጉትን ዉይይት ተከትሎ የፀጥታዉ ሁኔታ ትንሽ እንደተረጋጋና እስከ ዛሬ ጥዋት የመረጋጋት ሁኔታዎች እንደሚታይም የዓይን እማኙ ይናገራል።

ከወልድያ 42 ኪሎ ሜትር አካባቢ ርቀት ላይ የሚገኝ ግለሰብ ግን የሕዝብ መጓጓዣ አገልግሎት በአካባቢው እንደሌለ ይገልጻል።

በዛሬዉ ዕለት ወጣቶቹ ከክልሉ ፕሬዝደንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸዉ እና ከሃይማኖት አባቶች ጋር በመሆን ሁኔታዉን ለማረጋጋት ጥረት እያደረጉ መሆነቸዉን የመላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ፕሬዝዳንት ዶክተር በዛብህ ደምሴ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል።

የሰሜን ወሎ ዞን የፀጥታ ጉዳይ ኃላፊ አቶ አደራዉ ፀዳሉ ደግሞ ዛሬ ወጣቶች፣ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም አቶ ገዱ አንደርጋቸዉ ዉይይት ማካሄዳቸውን አረጋግጠዋል።

በዶይቼ ቬሌ የፈስቡክ ገፅ ላይ በወልድያ ከተማ ሆነ በአቅራቢያው የሚገኙ ሰዎች ያለውን ሁኔታ እንዲያጋሩን በጠየቅነው መሠረት፤ ሙሴ በምነቱ «ሰበር መረጃ ከወልድያ» በሚል በላኩልን አሰተያየት «ትናንት ህዝቡ መከላከያ ሰራዊቱን ከወልድያ አስወጥቶ ተቆጣጥሯት ነበር፣ አሁን ግን መከላከያ ሰራዊቱ ሀይል ጨምሮ ገብቷል፣ ግን ቢገባም ህዝቡን አልቻለውም እና አሁን ያለው አውራ ጎዳና አካባቢ ነው» ብለዋል። አሹ ኃይሉ የተባሉት ደግሞ «ዛሬም የ3 ሰዎች የቀብር ስነስርአት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል። በተረፈ ግን የሃዘን ድባብ ላይ እንገኛለን» ሲሉ ጽፈዋል።

መርጋ ዮናስ

ሸዋዬ ለገሠ