1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሜርክል ለፓርቲያቸዉ መሪነት በድጋሚ ተመረጡ

ማክሰኞ፣ ኅዳር 27 2009

ሜርክል ከሁለት ዓመት በፊት በተደረገዉ ተመሳሳይ ምርጫ ለሊቀመንበርነት የተመረጡት በ96,7 ከመቶ በሆነ ድምፅ ነበር።ሜርክል በመጪዉ የጎርጎሪያዉያን 2017 በሚደረገዉ ምርጫ ለመራሔ መንግሥትነት እንደሚወዳደሩ ይፋ አድርገዋል።

https://p.dw.com/p/2TqRW
Deutschland CDU Bundesparteitag in Essen Rede Merkel
ምስል Imago/R. Wölk

 

 የጀርመንዋ መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል እንደተጠበቀዉ የፓርቲያቸዉ ሊቀምንበር ሆነዉ በድጋሚ ተመርጠዋል።ኤሰን የተሰየመዉ የወግ አጥባቂዉ የክርስቲያን ዴሞክራቶች ሕብረት (CDU) ጉባኤ ሜርክልን የመረጠዉ በ89.5 ከመቶ በሆነ ድምፅ ነዉ።ሜርክል ከሁለት ዓመት በፊት በተደረገዉ ተመሳሳይ ምርጫ ለሊቀመንበርነት የተመረጡት በ96,7 ከመቶ በሆነ ድምፅ ነበር።ሜርክል በመጪዉ የጎርጎሪያዉያን 2017 በሚደረገዉ ምርጫ ለመራሔ መንግሥትነት እንደሚወዳደሩ ይፋ አድርገዋል።ለዚሕ ዓላማቸዉ ስኬት ዛሬ የተሰየመዉ የፓርቲያቸዉ ጉባኤ ለፓርቲዉ ሊቀመንበርነት እንዲመርጣቸዉ ጠይቀዉ ነበር።

ሜርክል በመራሔ መንግሥትነት በቆዩባቸዉ አስራ-አንድ ዓመታት መንግሥታቸዉ ሥራ-አጥነትን በመቀነስ፤ የምጣኔ ሐብት ድቀት ለማስወገድ፤  የአዉሮጳ አንድነትን ለማስከበር፤ አሸባሪነትን ለመዋጋት  ያደረገዉን ጥረትና ያስገኘዉን በጎ ዉጤት ዘርዝረዋል።ስደተኞችን በማስተናገዱ ረገድ ግን ከ8መቶ ሺሕ በላይ ስደተኛ ወደ ጀርመን በገባበት በ2015 በጋ ማብቂያ የተከሰተዉ ዓይነት ቀዉስ  ጨርሶ አይደገምም ብለዋል።

«ከአንድ ዓመት በፊት ካርልስሩኸ ባደረግነዉ የፓርቲያችን ጉባኤ ላይ ተነጋግረናል።ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በተደጋጋሚ ተነጋግረናልም።በ2015 በጋ ማብቂያ ላይ የተፈጠረዉ ሁኔታ ከእንግዲሕ ሊደገም አይችልም።መደገም የለበትምም።ይሕ የኛ እና የኔ ግልፅ ፖለቲካዊ መርሕ ነዉ።»

ሜርክል 80 ደቂቃ በፈጀ ንግግራቸዉ የጀርመን ሕግ በሚፈቅደዉ መሠረት ቡርቃ መልበስ ሊከለከል እንደሚችል አስታዉቀዋልም። በኤሰኑ ጉባኤ ላይ ከ አንድ ሺሕ የሚበልጡ የወግ አጥባቂዉ ፓርቲ የክርስቲያን ዴሞክራቲክ ሕብረት ተወካዮች ተካፍለዋል።

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ