1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሰልፍ፥ግጭትና ግድያ፤ በኢትዮጵያና ኤርትራ  

ዓርብ፣ ጥቅምት 24 2010

በኢትዮጵያ የተለያዩ ሥፍራዎች ብሔር ተኮር ግጭቶች፤ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ደግሞ ነገሮችን የሚያባብሱ መልእክቶች ተስተውለዋል። መልእክቶቹ በርካቶችን የሚያሳስቡም የሚያስተዛዝቡም ነበሩ። የአቶ በቀለ ገርባ የዋስ መብታቸው ታግዶ ጉዳያቸው እንደገና ሊታይ መሆኑ አነጋግሯል። በአስመራ የተኩስ ሩምታ የታጀበበት የተቃውሞ ሰልፍ መከሰቱም ተደምጧል።

https://p.dw.com/p/2mw3Y
Eritrea, Hauptstadt Asmara, Busbahnhof
ምስል picture-alliance

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት፦ ጥቅምት 24 ቀን፤ 2010

እዚህም እዚያም በተቃውሞ እና ግጭት በምትናጠው ኢትዮጵያ የሚስተዋለው ግድያ እና ግድያውን ተከትሎ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚናፈሰው ወሬ አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰ ይመስላል። ግድያዎችን የሚመለከቱ በርካታ መልእክቶች በሟቾች ማንነት እና ብሔር ላይ ተጠምደው ተስተዋለዋል።  የዛኛው ብሔር ተወላጆች የዚህኛውን ይሄን ያህል ገደሉ፤ እነከሌ የአካባቢው ተወላጆች የእነእከሌ ብሔርን እንዲህ አድርገው ገደሉ ወዘተረፈ የሚሉ በአንድ ሀገር ውስጥ አንዱን ባለመሬት ሌላኛውን መጤ የሚያስብሉ ጽሑፎች ኃላፊነት በጎደለው መልኩ ሲሰራጭም ታይቷል። 

የነገሩን አስቀያሚ ገጽታ የአፈንዲ ሙተቂ የፌስቡክ ጽሑፍ ጠቅልሎ ይዞታል። አፈንዲ «አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሰናል።» የሚል ርእስ የሰጠውን ጽሑፍ፦«አንድ እንኳ ኃላፊነት የሚሰማው ሰው ይጥፋ ጓዶች!!» በሚል የምሬት ገለጣ ይጀምራል። 

«ሁሉም ያልተረጋገጠ ወሬውን ፌስቡክ ላይ እያመጣ ይሰልቃል። ተከታዩ ወሬውን በአፉፍቱ እያራገበው ትልቅ ነበልባል ያስነሳል። ያኛውም ከእሳቱ ችቦውን ለኩሶ የራሱንና የጎረቤቱን ቤት ሊያቃጥል ይሮጣል» ያለው አፈንዲ፦ «‘ተው‘ ስትለው ለማሸማቀቂያ ሰፍቶ የደረደረውን ጥብቆ ያለብስሀል» በማለት የሰላ ትችቱን ይሰነዝራል። 

Äthiopien Proteste | Ambo Town
ምስል DW/M. Yonas Bula

ቀጠል አድርጎም፦ «አቤት ሀገር! አቤት ህዝብ!! መነገጃ የሆነ ህዝብ!! አሳዛኝ ሀገር!! መቼስ ሀገሪቷ መንግስት የላትም። ታዲያ እኛም ከርሱ ጋር ተደምረን የገዛ ቤታችንን እናፍርሰው እንዴ??» ሲል የሚያጠይቀው አፈንዲ፦ «ሀገር አፍርሰን መግቢያችን የት ሊሆን ነው!» ይልና «የማጅራት መቺ ፖለቲካ!!» ሲል ይቀጥላል። «እንኳንም በውስጡ ገብቼ አላንቦጫረቅኩ» በማለትም አፈንዲ ሰዉ «በጸሎትና በምህላ» እንዲበረታ በመጠየቅ የፌስቡክ ጽሑፉን ይቋጫል።

የአቶ በቀለ ገርባ ዋስትና መታገድ

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ በዋስትና ሊፈቱ ነው የሚለው ዜና ተሰምቶ ብዙም ሳይቆይ ነበር ውሳኔው መታጠፉ የተነገረው። የአቶ በቀለ ገርባ በ30 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር ቤት ወጥተው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ የተላለፈው ውሳኔ ሲደመጥ በርካቶች ደስታቸውን የገለጡት ወዲያው ነበር። በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተቃውሞዋቸውን የሚያሰሙ ሰዎች ውሳኔውን «ያልተለመደ ግን መልካም ዜና» ሲሉ ነበር የገለጡት።

ብዙም ሳይቆይ ነበር አቶ በቀለ እንዲፈቱ የተላለፈው መዝገብ ቊጥር እና ታስረው የሚገኙበት ቊጥር የሚጣረስ ነው የሚል ሌላ ነገር የተሰማው። በማግስቱ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ ዋስትና በሠበር ሰሚ ችሎት መታገዱ ተገለጠ፤ ዜናው በፍጥነት በማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች ተሰራጨ። የአቶ በቀለ ጉዳይ ኅዳር 14 ቀን እንደሚታይ አቶ በቀለ ራሳቸዉ እንደነገሯት ልጃቸው ቦንቱ በቀለ ገርባ ከዶይቸ ቬለ ጋር ባደረገችው ቃለ መጠይቅ ገልጻለች።

«ጠብቂ ይመጣል ተባልኩኝ። ቆሜ ብዙ ሰአት ጠበክኹት።  በመጨረሻም ሲመጣ  ቢሮ ተጠርቼ እያናገሩኝ ነበር እና 'ሰበር ሠሚ ችሎት ለኅዳር ዐሥራ አራት ቀጠሮ ያዘ፤ እንደገና ክርክር ይደረጋል እናም አቃቤ ሕጎች ለሠበር ሰሚ ችሎት አቤቱታ አቀረቡ ስለዚህ አትወጣም ተባልኩኝ' አለኝ።»

Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Heimken

በርካቶች በውሳኔው የተሰማቸውን ቅሬታ እና ሐዘን ገልጠዋል። ሴና አኖሌ በትዊተር ገጿ «በቀለ ገርባ ወደ መብት ተቆርቋሪነት የተቀየረ ከአመጻ ውጪ የሆነ ተቃውሞ አቀንቃኝ የኮሌጅ ምሁር ነው እንጂ ወንጀለኛ አይደለም» ስትል በእንግሊዝኛ ጽፋለች።  

ኬሻ በጠረባ‏ በተሰኘ የትዊተር ገጽ የሰፈረ የእንግሊዝኛ ጽሑፍ ደግሞ  እንዲህ ይነበባል።  «የፍትኅ ሥርዓቱ በኢትዮጵያ ቧልት ነው። በቀለ ገርባን ፍቱት።» አቶ በቀለ ገርባ ከእስር በዋስትና እንዲፈቱ የሚል ውሳኔ ተሰጥቶ የነበረው የተጠናከረውን ተቃውሞ ለማስቀየስ ነበር ያሉ አስተያየት ሰጪዎች፤ በኦህዴድ ግፊት ነው ውሳኔው ተሰጥቶ የነበረው የሚሉትን የሚቃረን ጽሑፍ አስነብበዋል። ቅመም በተሰኘ የትዊተር ገጽ፦ «በቀለ ገርባ እንዲፈታ ያስወሰነችው ኦህዴድ ከሆነች፤ እግዲስ በማን ይሆን?» የሚል ጽሑፍ ሰፍሯል። «የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት  የአንድ እስር ቤት አስተዳደር ያክል ተሰሚነት የላትም?» ሲል ያጠይቃል የቅመም ጽሑፍ። አቶ በቀለ በየትኛውም አካል ግፊት ሊፈቱ ባለመቻላቸው የተሰጠ አስተያየት ነው።

ማራናታ ጌታሆይ ቶሎና በተሰኘ የፌስ ቡክ ስም የተሰጠ አስተያየት ደግሞ፦ «ህዝቡ በዚህ ምክንያት ሰልፍ እንዲወጣ ነው፡፡ ተባኗል!!!» ሲል ይነበባል።  እዩ ግራኝ ደግሞ በፌስቡክ ገጹ፦ «ቢቆይም መፈታቱ አይቀሬ ነው» ብሏል። እዩ «እሱ ብቻ ሳይሆን በየጫካውና መታጎርያ ያሉ ሁሉ ይለቀቃሉ፤ ድል የሕዝብ ነው» ሲል አክሏል። «የስርዓቱ ሂደት ነው» የሚል አጠር ያለ መልእክት ያስነበበው ደግሞ ቤሪ ኢትዮ ነው በዛው በፌስ ቡክ። አበበ ለታ ደግሞ «በየትኛው ዓለም ነው የሀገር ነፃነት ሳይከበር የግለሰብ መብት የሚከበረው?» ሲል በፌስቡክ ይጠይቃል። «ሀገረችን ራሷ በአምባገነኖች ቁጥጥር ስር ነው ያለችው» ያለው አበበ ሀገሪቱ ከቊጥጥሩ ነጻ ስትሆን «ከዛ በኋላ ከፖለቲካ የፀዳ ፍርድ ቤት መቋቋም የሚቻለው» ሲል ጽሑፉን ደምድሟል።

Äthiopien Politiker Bekele Gerba
ምስል Addis Standard Magazine

በዋትስ አፕ አድራሻችን በድምጽ ከደረሱን መልእክቶች አንዱ እንዲህ ይበባል፦«የፌዴራሉ ፍርድ ቤት የዋስ መብቱን ጠብቆ እንዲፈታ አዘዘ። ግን ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ያሉት አዛዦች የኢህአዴግ ጄነራሎች ናቸው። የፍርድ ቤቱን ትእዛዝ አንቀበልም ያሉት ለምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ከፍተኛው ፍርድ ቤት ምንም መብት እንደሌለው ነው  እዚህ ጋር የሚያሳየው። እነሱ ነው የሚያዙት፤ ሁሉን ነገር ማድረግ የሚችሉት እነሱ ናቸው። ስለዚህ የእሱ የመፈታት መብት ወረቀት አልሰጥም ያሉት ይመስለናል እስካሁን የፍርድ ቤት መብት ስላልተጠበቀ ነው። ትክክለኛ ፌዴራል ቢኖር ፍርድ ቤት ከፌዴራል በላይ ነበር።  ግን ፍርድ ቤቶች እስካሁን ምንም መብት እንደሌላቸው ነው የሚያሳየው።»

ሌላው በድምፅ የተላከልን የዋትስአፕ መልእክትም የፍትኅ ሥርዓቱ እና የማረሚያ ቤት አለቆች ሥልጣንን እያነጻጸረ ያብራራል። «በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱን እያስተዳደረ ያለው ወያኔ መራሹ ኢሕአዴግ ሀገሪቱን ማስተዳደር  እንዳቃተው ግልጽ እና አጭር ነው። ምክንያቱም ጥልቅ ተሀድሶ አድርጌያለሁ እያለ፤ የማናየውን ነገር  እተገብራለሁ እያለ እየተንቀሳቀሰ ይህን ፍርድ ቤት የወሰነውን ደግሞ ተራ የማረሚያ ቤት አዛዦች ‘አንቀበልም‘  እያሉ ባለጉዳይን እያጉላሉ ፤ ይባስ ብለው የእነሱን ሥራ ባለጉዳዮች እላይ ታች ብለው  እንዲያስፈጽሙላቸው ሲጥሩ፤ ጊዜ ሲገዙባቸው ይታያል። እንግዲህ አንዱ ጥልቅ ተሀድሶ አድርገናል ካሉበት ነገር ውስጥ  በፍትኅ ዙሪያ ያለውን ነገር  እንፈታለን ነበር።» «እዚህ አገር ፍትህ እንዳሌሌለ ግልጽ ነው አያስደንቅም...» የሚል አጠር ያለ የጽሑፍ አስተያየትም በዋትስአፕ ደርሶናል።

የተቃውሞ ሰልፍና የተኩስ ሩምታ በአስመራ

ባሳለፍነው ረቡዕ ከወደ ኤርትራ መዲና አስመራ የተሰማው ዜና ብዙም የተለመደ አይደለም። በአስመራ ከተማ የተቃውሞ ሰልፍ መደረጉ እና ሰልፉ በመንግሥት ታጣቂዎች ተኩስ መበተኑን ይገልጣል ዜናው፤ ይህም በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች በስፋት ተሰራጭቷል። ቆየት ብሎም ሐሙስ ከሰአት በኋላ የወጡ ዜናዎች በተኩሱ የሞቱት ሰዎች 28 እንደሚደርሱ መዘገባቸውን በርካቶች ተቀባብለውታል። ዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ በድረ ገጹ ባሰራጨው መረጃ ዜጎቹ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ በማሳሰብ ወደ መሀል አስመራ እንዳያቀኑም አስጠንቅቋል። የአሜሪካ ኤምባሲ መግለጫ የተቃውሞ ሰልፉ በምን ምክንያት እንደቀሰቀሰ ግን አይጠቅስም።

Eritrea, Hauptstadt Asmara, Busbahnhof
ምስል picture-alliance

በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በተለይ በትዊተር ዜናውን ያስተባበሉት የኤርትራ የማስታወቂያ ሚንሥትር አቶ የማነ ገብረ መስቀል፦ «አስመራ ውስጥ በአንድ ትምህርት ቤት የተከናወነ አነስ ያለ ሰልፍ ያለምንም ጉዳት ተበትኗል» ሲሉ ጽፈዋል። በዛው ትዊተር ላይ ዜናውን እከሌ የሚባል ጋዜጠኛ ነው አሳስቶ ያወጣው፤ ይኸኛው ደግሞ ተቀብሎ አሠራጨው፤ የተሳሳተ ነው የሚል መልእክት ከኤርትራ በኩል ተነቧል። 

በትዊተር እና በፌስቡክ የተሠራጩ አጠር ያሉ የቪዲዮ ምስሎች በከተማዪቱ ሂጃብ የለበሱ ሴቶችና ሌሎች ሰዎች ጦር መሣሪያ ከታጠቁ ወታደሮች ፊት ሲሮጡ ግን ያሳያሉ፤ ተደጋጋሚ የተኩስ ድምጽም ይሰማል። በሌላ ቪዲዮ ደግሞ አንድ የእስልምና አባት ለተሰበሰቡ ሰዎች ንግግር ሲያደርጉ ይደመጣል። ይህን ቪዲዮ ዳውድ ሳሌህ የተባለ ሰው በትዊተር ገጹ አያይዞ «ሁሉም ነገር የጀመረው ከዚህ ስብሰባ በኋላ ነው» የሚል ጽሑፍ አስፍሯል። «ኤርትራ እና ሐጂ ሙሳሣ ይፈቱ» የሚሉ መልእክቶችም ከቪዲዮው ጋር ተያይዞ ይነበባል። በርካቶች ይህን ቪዲዮ ተቀባብለውታል። 

በቪዲዮው ውስጥ የሚናገሩት አዛውንት የሐይማኖት አባት፥ «ሂጃብ ለብሰው ትምህርት ቤት የሚመጡት ሴቶች ልጆቻችን ናቸው።»፤ «የሚመጣውን ሁሉ ለመቀበል ዝግጁ ነን።»፤ «መብት አለን፤ ማንንም አንፈራም።» ሲሉ በትግርኛ ይደመጣሉ። ንግግራቸው በዐረቢኛ እና በእንግሊዝኛ ጽሑፍ ተተርጒሟል እዛው ቪዲዮ ውስጥ። ንግግሩ ከ2800 በላይ ወንዶች እና ሴቶች ተማሪዎች ያሉት አልድያ ትምህርት ቤትን የሚመለከት መሆኑም በቪዲዮው ተጠቅሷል። ተናጋሪው የመንግሥት ባለሥልጣናት ጠርተው እንዳነጋገሯቸው «ፖሊሲያቸውንም እንዲቀይሩ» እንደጠየቋቸው ያብራራሉ። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ