1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

ሳይንስን የሚያስተዋውቁት ውድድሮች

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 25 2010

በኢትዮጵያ ወጣቶች በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ መስኮች ፍላጎት እንዲያድርባቸው የሚያተጉ ውድድሮች እና ትምህርታዊ ጉብኝቶች እየተለመዱ መጥተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል ዩቴልሳት የተባለው የሳተላይት ኩባንያ ከዲ.ኤስ.ቲቪ የቴሌቪዝን ስርጭቶች አቅራቢ ድርጅት ጋር በዓመቱ የሚያዘጋጀው አኅጉራዊ ውድድር አንዱ ነው፡፡

https://p.dw.com/p/2qJ6Y
Deutschland EMC Satellite Earth Station At Raisting  Weilheim in Oberbayern
ምስል Getty Images/S. Gallup

ሳይንስን የሚያስተዋውቁት ውድድሮች

መቀመጫውን በፈረንሳይዋ መዲና ፓሪስ ያደረገው የሳተላይት ኩባንያ ዩቴልሳት በሳተላይት ግንኙነት ስማቸው በቀዳሚነት ከሚጠራ ድርጅቶች አንዱ ነው፡፡ ወደ 6‚700 የቴሌቭዥን ጣቢያዎች ስርጭትን ተሸክሞ በመላው ዓለም ለሚገኙ አንድ ቢሊዮን ገደማ ተመልካቾች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ኩባንያው ከአፍሪካ እሰከ አውሮፓ፣ ከመካከለኛው ምስራቅ እስከ እስያ እና አሜሪካ ያሉ ቦታዎችን ሽፋን የሚሰጠው ወደ ህዋ ባመጠቃቸው 39 ሳተላይቶች ነው፡፡ እንዲህ መዳረሻው የሰፋው ዩቴልሳት የአፍሪካ አዳጊ ወጣቶችን ኢላማ ያደረገ ውድድር ማገዝ ከጀመረ ስድስት ዓመታት ተቆጠሩ፡፡

ኩባንያው ከደቡብ አፍሪካው የሳተላይት የቴሌቪዥን ስርጭቶች አቅራቢ ድርጅት ጋር በመሆን እያካሄደው የሚገኘው ውድድር ዕድሜያቸው ከ14 እስከ 19 ያሉ አፍሪካውያንን ኢላማ ያደረገ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ውድድሮች እና የመዝናኛ ቴሌቪዥን ጣቢያዎችን ዲ.ኤስ.ቲቪ በተሰኘ አገልግሎቱ ለአፍሪካውያን እያቀረበ የሚገኘው መልቲ ቾይስ አፍሪካ ከዩቴልሳት ኩባንያ ጋር ጥምረት የፈጠረው በጎርጎሮሳዊው 1999 ነበር፡፡ ከአስራ ሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ ይፋ ያደረጉት “የኮከብ ሽልማቶች” የተሰኘው ውድድር በሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶችን አሳትፏል፡፡

Kasachstan Hispasat Amazonas 5 Raketenstart
ምስል Reuters/S. Zhumatov

ኢትዮጵያውያን ወጣቶችም በመልቲቾይስ የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ አማካኝነት በውድድሩ ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ አቶ ኢዛና ውብሸት በመልቲ ቾይስ ኢትዮጵያ የኮሚዩኒኬሽን ክፍል ኃላፊ ናቸው፡፡ ስለ ውድድሩ ዓላማ ያስረዳሉ፡፡

ተማሪዎች ለሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ፍላጎት እንዲያድርባቸው የማድረግ እና የፈጠራ አስተሳሰቦችን የማበረታታት ዓላማ ያነገበው ይሄው አህጉራዊ ውድድር ዘንድሮም ለሰባተኛ ጊዜ እንደሚካሄድ ሰሞኑን ይፋ ተደርጓል፡፡ በውድድሩ የሚሳተፉ አዳጊ አፍሪካውያን ከሳተላይት ቴክኖሎጂ ጋር በተያያዙ አርዕስተ ጉዳዮች ላይ ሀሳባቸውን በጽሁፍ እንዲገልጹ አሊያም በስዕላዊ መግለጫ (ፖስተር) እንዲያሳዩ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ተወዳዳሪዎቹ የሚልኳቸው ጽሁፎች እና ፖስተሮች መጀመሪያ በሀገር አቀፍ ደረጃ በዳኞች ይፈተሻሉ፡፡ ከእነርሱ ውስጥ አብላጫውን ድምጽ ያገኙት ለአህጉራዊ ውድድር ይላካሉ፡፡

ስለዳኞቹ ስብጥር እና የውድድር መስፈርት አቶ ኢዛና ተከታዩን ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡   

Satellite Dish in Ethiopia
ምስል F. B. Hassen

ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በውድድሩ ላይ እንዲሳተፉ በመልቲ ቾይስ ኢትዮጵያ በኩል ለትምህርት ቤቶች ግብዣ እንደሚላክ አቶ ኢዛና ያስረዳሉ፡፡ በውድድሩ ላይ ሁሉንም ትምህርት ቤቶች ማሳተፍ አዳጋች እንደሆነ የሚያብራሩት አቶ ኢዛና ድርጅታቸው የተወሰኑትን ትምህርት ቤቶች በየጊዜው ለውድድር እንደሚመረጥ ተናግረዋል፡፡ በምርጫው በተቻለ መጠን የግል እና የመንግስት ትምህርት ቤቶችን ለማሳተፍ ጥረት እንደሚያደርጉም አስረድተዋል፡፡ የእስካሁኑ የተማሪዎች ተሳትፎ ጥሩ የሚባል እንደሆነ የሚናገሩት የኮሚዩኒኬሽን ክፍል ኃላፊው ውድድሩም በጉጉት የሚጠበቅ ሆኗል ይላሉ፡፡

በባለፈው ዓመት ውድድር የኢትዮጵያውያኑን ተማሪዎችን ጉጉት የሚያንር አንድ ክስተት ሆኗል፡፡ የዛሬ ዓመት በየሀገራቸው ያለውን ውድድር በበላይነት ተወጥተው ለመላው አፍሪካ ውድድር ስራዎቻቸው ከቀረቡላቸው ተማሪዎች መካከል ኢትዮጵያዊው ተማሪ አሸናፊ መሆኑ ተበስሯል፡፡ ስሙ ልዑል መስፍን ይባላል፡፡ ተማሪነቱ ደግሞ በአዲስ አበባ በሚገኘው ጊብሰን ዩዝ አካዳሚ ውስጥ ነው፡፡ በጽሁፍ ውድድር ቁንጮ መሆኑ ሲነገረው የ11ኛ ክፍል ተማሪ እና የ16 ዓመት ወጣት የነበረው ልዑል አሁን በክፍልም፣ በዕድሜም በአንድ ዓመት ጨምሯል፡፡ ለውድድር ያቀረበውን ጽሁፍ ጭብጥ እንዲያብራራ ጠይቄው ነበር፡፡  

Satellitenschüssel
ምስል Lockheed-Martin

ያለፈው ዓመት የመወዳደሪያ ርዕስ “የሳተላይት ቴክኖሎጂ ለአፍሪካ መጻኢ የሚጫወተው ሚና” የሚል ነበር፡፡ የውድድሩ አሸናፊዎች የተዘረዘሩበት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚያትተው ልዑል አርዕስተ ጉዳዩን ከአፍሪካ እና ከየሀገራቱ ፍላጎቶች ጋር በማዋሃድ ያቀረበው ትንታኔ ዳኞችን ማርኳቸዋል፡፡ እንደ ልዑል አይነቶቹ ተማሪዎች በየውድድሩ የሚያቀርቧቸው ጥልቅ ሀሳቦች የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊውን ኢዛናንም እንዳስደነቋቸው አሉ፡፡

በጊብሰን ዩዝ አካዳሚ የሳይንስ ተማሪ የሆነው ልዑልም ቢሆን ስለሳተላይት እና ቴክኖሎጂው እምብዛም እውቀቱም ሆነ ፍላጎቱ አልነበረውም፡፡ ስለውድድሩ በትምህርት ቤቱ ሲወራ ሲሰማ ግን ስለጉዳዩ ጥናት ማድረግ ጀመረ፡፡ የሳተላይትን  አጠቃቀም አስመልክቶ በጥናቱ የደረሰበትን ወደ ጽሁፍ ቀይሮ ተወዳደረ፡፡ ልዑል ትምህርቱን በሚከታተለበት በጊብሰን ዩዝ አካዳሚ ሲ.ኤም.ሲ ካምፓስ የቡድን መሪ የሆኑት አቶ ነብዩ ደምሰው ስለ ወጣቱ ተማሪ ምስርክነታቸውን ይሰጣሉ፡፡ እንዴት ትምህርት ቤታቸውን ወክሎ ለመወዳደር እንደበቃም ያስረዳሉ፡፡   

አህጉራዊውን ውድድር ያሸነፈው ልዑል የዩቴልሳት ዋና መስሪያ ቤት ወደሚገኝበት ፈረንሳይ ፓሪስ የመጓዝ እድሉን አግኝቷል፡፡ በዚያ የገጠመውን እና ያሳደረበትን ስሜት እንዲህ ያስረዳል፡፡ ልዑል ጉብኝቱ የህዋ ሳይንስን የማጥናት ፍላጎት እንዳሳደረበት አልሸሸገም። ነገር ግን ቀደም ሲል የመረጠውን የኮምፒውተር ኢንጂነሪንግ ትምህርት ከህዋ ሳይንስ ጋር ማቀናጀት ይሻል። ወጣቱ ተማሪ እንደተሳተፈበት ዓይነት ውድድሮች በየጊዜው መካሄዳቸው ለሌሎችም ተማሪዎች ጠቀሜታቸው ከፍ ያለ እንደሆነ መምህር ነብዩ ያስረዳሉ፡፡

ተስፋለም ወልደየስ

ሸዋዬ ለገሠ