1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ግንቦት 6 ቀን፣ 2010 ዓ.ም

ሰኞ፣ ግንቦት 6 2010

የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ስፖርት ወደ አደገኛ አቅጣጫ እያመራ ነው። በተለይ ቡድኖች እና ደጋፊዎች ከኳሱ ይልቅ ብሔር እና ጎሣ ላይ ይበልጥ ማተኮራቸው ችግሩን እያባባሰው ነው። ለዚህ መገለጫው ደግሞ  በቅርቡ  የወልዋሎ አዲግራት ተጨዋቾች እና የቡድን መሪ  ከመከላከያ ጋር በነበረው ጨዋታ ዳኛን መደብደባቸው ይጠቀሳል። 

https://p.dw.com/p/2xhxC
WM 2014 Gruppe C 1. Spieltag Kolumbien Griechenland
ምስል Reuters

በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ሜዳ በተጨዋቾች እና በደጋፊዎች የሚስተዋለው የሥነ-ምግባር ጥሰት ለረዥም ጊዜ ሲንከባለል የቆየ ነው። የወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲ ቡድን ከመከላከያ ጋር በነበረው ግጥሚያ ላይ የተስተዋለው ግን የነገሩን ክረት እና የሥነ ምግባር ጥሰት ፈጻሚዎች ማን አለብኝነት ገኖ የወጣበት ነው።  የትሪቡን ስፖርት ዋና አዘጋጅ እና የረዥም ጊዜ የስፖርት ጋዜጠኛ ፍቅር ይልቃል ስር የሰደደው የሥነ ምግባር ጥሰት መነሻ ጥናት ቢያስፈልገውም ዋና ዋና የሚላቸውን ይጠቅሳል። «የተልፈሰፈሱ የፌዴሬሽን አሠራር፣ ግልፅ ያልኾነ፤ አላስፈላጊ ሰአት ላይ የሚወሰኑ፤ ተወስነውም የሚነሱ  አንዳንዴ ሁለቱንም ቡድኖች በአንድ ዐይን» ያለመመልከት ለችግሩ ሰበብ ከኾኑ ነጥቦች ይጠቀሳሉ ብሏል። 

ከሥነ-ምግባር ጥሰቱ ባሻገር መገናኛ ብዙኃን የስፖርታዊ ጨዋነት ላይ ግልጽ የኾነ አቋም ያለመያዛቸው ኹኔታም ለሥነ ምግባር ጥሰቱ መባባስ ራሱን የቻለ ሚና አለው ይላል ፍቅር። «ድርጊቶች ሲፈጸሙ ነገሮችን ከፍ አድርጎ መዘገብ» እንዲሁም፦ «ድርጊቶች ዝም ሲባሉ ከመከታተል ይልቅ የመጥፋት ኹኔታ» የችግሩ አባባሽ ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ» ብሏል። ከዚያ ባሻገር ግን  የእግር ኳስ ቡድኖችን አካባቢያዊ ማድረግ ሌላኛው ችግር እንደኾነ ጠቅሷል። «የጎሠንነት እና ብሔርተኝነት» አዝማሚያም ሌላው ዋነና ችግር መኾኑን አክሏል

ይኽን ሥር የሰደደ የሥነ ምግባር ጥሰት ለማስተካከል ራሱን የቻለ ጥልቅ ጥናት እንደሚያስፈልገው የተናገረው ፍቅር፦ መፍትኄ ይኾናሉ ያላቸውን ሐሳቦች ጠቅሷል። «በጎሰኝነት የሚታማ የፌዴሬሽን አሠራር መስተካከል አለበት» ብሏል። 

የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ቡድን የቀድሞ መሪ አቶ ማሩ ገብረፃዲቅ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በሚከናወኑ ማናቸውም ውድድሮች ላይ እንዳይሳተፉ የዕድሜ ልክ እገዳ እንደተጣለባቸው ተዘግቧል።  በመሀል ዳኛው እያሱ ፈንቴ ላይ ድብደባ በመፈጸሙ ነው ውሳኔው የተላለፈው። የተወሰኑ ተጨዋቾች የስድስt ወራት እገዳ እና የብር ቅጣት ተላልፎባቸዋል።  

Champions League  Liverpool vs AS Rom Salah
ምስል Reuters/C. Recine

በተጠናቀቀው የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የሊቨርፑሉ አጥቂ ሞሐመድ ሳላኅ በፕሬሚየር ሊጉ ታሪክ በርካታ ግቦች በማስቆጠር ክብር ወሰን ሰብሯል። ቡድኑ ሊቨርፑል የአራተኛ ደረጃን በማግኘት ለቀጣዩ ዙር የሻምፒዮንስ ሊግ ማለፉንም አረጋግጧል። ሊቨርፑል 15ኛ ኾኖ የጨረሰው ብሪንግተንን በሜዳው አንፊልድ 4 ለ0 ባደባየበት የትናንቱ ግጥሚያ ቀዳሚዋን ግብ በ26ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው  ይኸው ግብጻዊ አጥቂ  ነው።  ግንቦት 18 በሚከናወነው የሻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ግጥሚያ የሊቨርፑሉ አጥቂ ሞሐመድ ሳላኅ ሪያል ማድሪድ ላይ ተጨማሪ ግብ ሊያስቆጥር ይችል ይኾናል።  በአጠቃላይ የፕሬሚየር ሊጉ 38 ጨዋታዎች ሞሐመድ ሳላኅ 32 ግቦችን አስቆጥሯል። በዚህም 30 ግቦችን ከመረብ ያሳረፈው የቶትንሀም ሆትስፐሩ ሐሪ ኬን ለሦስተኛ ጊዜ በተከታታይ ወርቃማውን ጫማ እናዳያነሳ አድርጎታል። ቶትንሀም፤ ከዋንጫ ባለድሉ ማንቸስተር ሲቲ፣ ሁለተኛ ኾኖ ከጨረው ማንቸስተር ዩናይትድ እና ሊቨርፑል ጋር ለሻምፒዮንስ ሊግ ማለፉን አረጋግጧል።

በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በተጠናቀቀው የጀርመን ቡንደስ ሊጋ ባለድሉ ባየር ሙይንሽን እና ሻልከእንዲሁም ሆፈንሃይም፣ ለሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር በቀጥታ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ለሻምፒዮንስ ሊግ ማጣሪያ አልፏል። ባየር ሌቨርኩሰን እና በስድስተኛነት ያጠናቀቀው ላይፕሲሽ ለአውሮጳ ሊግ አልፈዋል።  

UEFA Champions League Halbfinale | AS Rom - FC Liverpool -Spielende
ምስል Reuters/A. Lingria

በቡንደስሊጋው የመጨረሻግጥሚያ ኮሎኝን ቅዳሜ ዕለት 4 ለ1 ያሸነፈው ቮልፍስቡርግ በቡንደስ ሊጋው ሁለተኛ ዲቪዚዮን 3ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ሆልሽታይን ኪዬል ጋር ከቡንደስ ሊጋው ላለመውረድ የፊታንችን ሐሙስ ለመጀመሪያው ዙር ይፋለማል።  የሐምቡርግ ቡድን እና ኮሎኝ ከቡንደስሊጋው ወራጅ ኾነው ተሰናብተዋል። ሐምቡርግ በቡንደስ ሊጋ ታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሰናበት ደጋፊዎች በስታዲየም ተቀጣጣይ ነገሮችን በማብራት ንዴታቸውን ገልጠዋል።

አንድ ቀሪ ውድድር በሚቀረው የስፔን ላሊጋ ከወዲሁ ለሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ማለፋቸውን ያረጋገጡ ቡድኖች የሚከተሉት ናቸው። መሪው ባርሴሎና፣ አትሌቲኮ ማድሪድ፣ ሪያል ማድሪድ እና ቫሌንሺያ ።

ሩስያ የምታስተናግደው የዘንድሮ የዓለም ዋንጫ ሊጀምር 31 ቀናት ብቻ ይቀሩታል። እግር ኳስ ጨዋታዎቹን ለመዘገብ እና ለመከታተል በመላው ዓለም ዙሪያ የሚገኙ ጋዜጠኞች የጉዞ መሰናዶ እያደረጉ ነው። ከዚህ ቀደም የሩስያ ስፖርተኞች ፈጽመውታል ስለተባለው መጠነ ሰፊ የኃይል ሰጪ ንጥረ ነገር ሰፊ ዘገባ ያቀረበው የጀርመኑ አ ኤር ዴ ቴሌቪዥን ጣቢያ ተንታኝ ሐዮ ዜፐልት የሩስያ ቪዛ መከልከሉ ተገልጧል።

ጉዳዩን የጀርመን መንግሥት በቀላሉ አልተመለከተውም። የጀርመን መንግሥት ቃል አቀባይ ሽቴፋን ዛይበርት ከበርሊን በሰጡት መግለጫ፦ «የሐዮ ዜፐልት ቪዛ ሕጋዊነት የለውም ማለታቸው ስህተት ነው» ብለዋል። «የሩስያ ባለሥልጣናት ይኽ የጀርመን ዘጋቢ የዓለም ዋንጫ እግር ኳስን ለመዘገብ እንዲቻለው ጉዞውን እንዲያመቻቹለት እንጠይቃለን» ብለዋል። 

Russland Fußballweltmeisterschaft Moskau 2018 - Baustelle Ekaterinburg Arena
ምስል Reuters/Stringer

በሩዋንዳ አስተናጋጅነት ከፊታችን ዐርብ አንስቶ በሚከናው የሴካፋ እግር ኳስ ለመሳተፍ የኢትዮጵያ የሴቶች ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ሉሲዎቹ ወደ ሩዋንዳ ሐሙስ እንደሚያቀኑ ተገልጧል። ውድድሩ ከግንቦት 10 እስከ 20 ድረስ ይከናወናል።

ትናንት ቻይና ውስጥ በተከናወነው የማራቶን ሩጫ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሙሉ ሰቦቃ በአንደኛነት አጠናቃለች። ሙሉ የገባችበት ሰአት 2:28:59 ሲኾን፤ በዚህ የማራቶን ሩጫ ከ30,000 በላይ ሯጮች መታደማቸው ተገልጧል።

የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማሕበራት ፌዴሬሽን (FIFA) ኢትዮጵያዊቷ ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ የፊፋ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን እንድትዳኝ መርጧታል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ