1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማርቲን ሹልትስ

ሐሙስ፣ መስከረም 11 2010

በየካቲት እና በመጋቢት 2017 በተካሄዱ የህዝብ አስተያየት መመዘኛዎች ሹልትስ ሜርክልን በልጠው ተወዳጅ ፖለቲከኛ ተባሉ። ያኔ የመራሄ መንግሥት ቀጥተኛ ምርጫ ተካሂዶ ቢሆን ኖሮ ሹልትስ ያሸንፉ ነበር ተብሏል።

https://p.dw.com/p/2kUn1
ARD-Wahlarena mit Kanzlerkandidat Martin Schulz
ምስል picture-alliance/dpa/J. Büttner

ማርቲን ሹልትስ

የጀርመን ሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ በምህጻሩ ኤስ ፔ ዴ  እጩ መራሄ መንግሥት ማርቲን ሹልትስ የጀርመን መራሄ መንግሥት እሆናለሁ እያሉ ነው። ይህን ማሳካት ይችሉ ይሆን? በህዝብ አስተያየት መመዘኛዎች የተፎካካሪያቸው የእጩ መራሂተ መንግሥት የአንጌላ ሜርክል  ፓርቲ«የክርስቲያን ዴሞክራቶች ህብረት»በምህጻሩ ሴ ዴ ኡ በሰፊ ልዩነት እየመራ ነው። ለመሆኑ የሜርክል ተፎካካሪ ሹልዝ ማን ናቸው? የጀርመን አጠቃላይ ምርጫ የሚካሄድበት ጎርጎሮሳዊው 2017 የባተው ለሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ እጩ ማርቲን ሹልትስን ተስፋ ባማለምለም ነበር። የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ ሊቀ መንበር ዚግማር ጋብርየል ሳይታሰብ ከሃላፊነታቸው እንደተነሱ ሹልትስ በምርጫው የፓርቲው እጩ መራሄ መንግሥት ሆኑ። ወዲያውኑም  ሁሉም ነገር በፍጥነት መለዋወጥ ያዘ። ፓርቲው የህዝብ ድጋፍ  አደገ። ተዳክሞ የነበረው ኤስ ፔ ዴ ከመቅጽበት አንሰራራ። በሺህዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ አባላት ፓርቲውን ተቀላቀሉ። የህዝብ አስተያየት መመዘኛ ተንታኞች የአውሮጳ ፖለቲከኛው ሹልትስ በሀገር ውስጥ ፖለቲካ ጥቅም ላይ አለመዋላቸውን እያነሱ የለውጥ ተስፋን አጫሩ። በዚህ የሹልትስ ተጽእኖም የክርስቲያን ዴሞክራቶች ህብረት  ፓርቲን ሴዴኡ ተረብሾ ነበር። የኤስ ፔዴው እጩ መራሄ መንግሥት የ61 ዓመቱ ማርቲን ሹልትስ የጎላ የፖለቲካ ተሳትፎአቸው በሀገራቸው ሳይሆን በአውሮጳ ፓርላማ ነበር ። በጎርጎሮሳዊው 2012 ነበር የፓርላማውን ፕሬዝዳንትነት ሥልጣን የያዙት። ይወዱት በበነበረው በዚህ ሃላፊነት ላይ የቆዩት እስከ ጥር 2017 ነው። ሹልትስ ከዚያ በኋላ ፊታቸውን ወደ በርሊን አዞሩ። ፓርቲያቸው ኤስፔዴ በወቅቱ ራሱን በማስተካከል ላይ ነበር። ያኔ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት የኤስፔዴው ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ለጀርመን ፕሬዝዳንትነት ሲመረጡ  የፓርቲው ሊቀመንበር እና የኤኮኖሚ ሚኒስትር የነበሩት ዚግማር ጋብርየል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነቱን ሃላፊነቱን ወሰዱ። ጀርመንን ተጣምሮ በሚመራው የሴዴኡ እና የኤስፔዴ መንግሥት ውስጥ ሃላፊነት የሌላቸው ሹልትስ  እጩ መራሄ መንግሥትነት እና የፓርቲው ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ። ለፓርቲያቸው አባላት እና ለደጋፊዎቻቸው ተስፋ ሰጭ መልዕክት አስተላለፉ።
«ገጽታችንን ይበልጥ እናጠናክራለን። ማሸነፍ አለብን። በኖርድራይን ቬስትፋልያ እንገጥማቸዋለን። »
የፓርቲውን አባላት ሙሉ ድምጽ አግኝተው የፓርቲው ሊቀመንበር የሆኑት ሹልትስ በአጭር ጊዜ ውስጥ አለመረጋጋት ይታይበት የነበረውን የፓርቲውን ተስፋ አለመለሙ። ንግግራቸው ብቻ ሳይሆን ሰዎችን የመቅረብ ችሎታቸው ብዙዎችን አነቃቃ። በየካቲት እና በመጋቢት 2017 በተካሄዱ የህዝብ አስተያየት መመዘኛዎች መሠረት ሹልትስ ሜርክል በመብለጥ ተወዳጅ ፖለቲከኛ ነበሩ። ያኔ ቀጥተኛ የመራሄ መንግሥት ምርጫ ተካሂዶ ቢሆን ኖሮ ሹልትስ ያሸንፉ ነበር ተብሏል። ይሁን እና ርሳቸው የፓርቲውን መሪነት ከያዙ በኋላ በዛርላንድ በሽሌሽቪክ ሆልሽታይን እን በኖርድ ራይን ቬስት ፋልያ ፌደራዊ ክፍለ ግዛቶች በተካሄዱ ምርጫዎች ኤስፔዴ አልተሳካለትም። በህዝብ አስተያየት መመዘኛዎች ፓርቲው ያገኛል የሚባለው ድጋፍ ቀንሷል። ይሁንና ሹልትስ ግቤ ማሸነፍ ነው ብለዋል።
« አስተያየት መመዘኛዎቹን እኔም አነባቸዋለሁ። ሁሉም መመዘኛዎቹ የሚጋሩት ነገር አለ። ከሁለት መራጮች አንዱ ማንን እንደሚመርጥ አልወሰነም። እስካሁን ወዳልወሰኑት ነው የምሄደው። የነርሱን ድምፅ ሳገኝ የጀርመን ምክር ቤት ምርጫን አሸንፋለሁ ያ ነው የኔ ግብ። 
የሹልትስ የፖለቲካ ህይወት የሚጀምረው አኽን በተባለችው የምዕራብ ጀርመን ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው በቩርስል ነው። በወጣትነታቸው ታዋቂ የእግር ኳስ ተጫዋች መሆን ነበር ምኞታቸው።  በዚህ የተነሳም የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ሳይወስዱ ቀሩ። በደረሰባቸው ከባድ ጉዳት ሰበብ የሚወዱትን የእግር ኳስ ጨዋታ ካቋረጡ በኋላ የመጠጥ ሱሰኛ ሆኑ። የያኔውን ሥራ አጥ እና ጠጭውን ሹልትስን ወንድሞቻቸው እና ወዳጆቻቸው አግዘዋቸው አንሰራሩ። በአንድ ወቅት ሹልትስ አሁን ለሚገኙበት ቦታ ከመብቃታቸው በፊት ከዝቅተኛ ደረጃ መነሳታቸውን ገልጸው ነበር።
« ትምህርቴን አቋርጫለሁ። ዓለምን ከስር ጀምሮ አይቻታለሁ። ያም ሆኖ አሁን የደረስኩበት ደረጃ ላይ በመገኘቴ እኮራለሁ።»  
ሹልትስ ችግሩን ተቋቁመው ካንሰራሩ በኋላ ቩርስል ከተማ ውስጥ መጻህፍት ቤት ከፈቱ። ባለትዳር እና የሁለት ልጆች አባት ሹልትስ ንባብ የህይወቴ የደም ስር ነው ይላሉ። የሹልትስ የመፀሐፍ መደብር እስለዛሬም ድረስ አለ። ሹልትስ በ31 ዓመታቸው ነበር ያደጉባት የቩርስልን ከተማ ከንቲባ ለመሆን የበቁት። እስካለፈው ጥር ድረስ ለ5 ዓመታት በፕሬዝዳንትነት የመሩት ሹልትስ የአውሮጳ ህብረት ፓርላማ አባል የሆኑት ደግሞ በጎርጎሮሳዊው 1994 ነበር። ከወዲሁ የሚሰጡ አስተያየቶች ሶሻል ዴሞክራቶች በምርጫው ጥሩ ውጤት ለማግኘት እስከ መጨረሻው ሰዓት ድረስ መታገል ይኖርባቸዋል ይላሉ። 

Deutschland wählt BTW-Reise ARD-Wahlarena Schulz SPD
ምስል DW/R. Oberhammer
Deutschland wählt DW Interview mit Martin Schulz
ምስል DW/R. Oberhammer
Deutschland wählt BTW-Reise ARD-Wahlarena Schulz SPD
ምስል DW/R. Oberhammer

ኒና ቬርክሆይዘር

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ