1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአማራ ክልል የቀጠለው የመከላከያ ሰራዊትና የፋኖ ታጣቂዎች ግጭት

ሐሙስ፣ የካቲት 21 2016

በአማራ ክልል በመከላከያ ሰራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚደረገውን ውጊያ ተከትሎ በክልሉ በተለይ በምዕራብ ጎጃም ዞን ፈረስቤት በተባለ ቦታ ንፁሃን መገደላቸውን የአይን እማኝ ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል። በክልሉ በሚደረገው ውጊያ በከተሞች መደበኛ እንቅስቃሴ በመገታቱ ለችግር መጋለጣቸውንም በአዊ ብሄረሰብ ዞን አንድ የእንጅባሪ ነዋሪ ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/4d2j4
ባህርዳር ፤የአማራ ክልል ዋና ከተማ
ባህርዳር ፤የአማራ ክልል ዋና ከተማ ምስል Matyas/Pond5 Images/IMAGO

በምዕራብ ጎጃም ፈረስቤት ንፁሃን ተገድለዋል ተባለ


በአማራ ክልል በምዕራብ ጎጃም ዞን  ፈረስ ቤት ተብሎ በሚጠራዉ ቦታ ልዩ ስሙ ዝቋላ ወገብ ቀበሌ  አንድ ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉ ነዋሪ ለዶቼቬለ እንደገለፁት በአካባቢው ከሰኞ ጀምሮ በመከላከያ ሰራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ከፍተኛ ዉጊያ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን ውጊያው ጋብ ብሎ አካባቢው በመከላከያ ስር መሆኑን አስረድተዋል።ነዋሪው አያይዘውም በአካባቢው በሁለቱ ተፋላሚ ሀይሎች የተካሄደውን  ግጭት ተከትሎ ንፁሃን መገደላቸውንም አብራርተዋል። 
ከዚህ በተጨማሪ በአካባቢው በተፈጠረው ችግር መደበኛ እንቅስቃሴ ለማድረግ ነዋሪዎች መቸገራቸውን አስረድተዋል።በመሆኑም የደረሰውን ጉዳት ለሚመለከተው አካል እንዲደርስ ጠይቀዋል።

በክልሉ የአዊ ብሄረሰብ ዞን እንጅባራ ከተማ ነዋሪ የሆኑ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የከተማው ነዋሪ በበኩላቸው በከተማው ዙሪያ ውጊያ እና ተኩስ መኖሩን ትናንት ምሽት ለዶቼ ቬለ ልጸዋል።በዚህ ሳቢያ ከቤት መውጣት እና መደበኛ እንቅስቃሴ መከወን እንዳልቻሉ ገልፀዋል። 

የፋኖ ታጣቂዎች በአማራ ክልል አዊ የብሄረሰብ አስተዳደር ዞን
የፋኖ ታጣቂዎች በአማራ ክልል አዊ የብሄረሰብ አስተዳደር ዞንምስል Awi zone communication office

እንደ ነዋሪው ገለፃ ግጭቱ በወንድማማች መካከል የሚካሄድ በመሆኑ፤ ለውይይት ቅድሚያ ተሰጥቶ ችግሩ እንዲፈታ  ጠይቀዋል።
የክልሉን ልዩ ኃይል ለመበተን እና ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት የተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱት የፋኖ ታጣቂዎች ከመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ጋር ግጭት ውስጥ ከገቡ ወራቶች ተቆጥረዋል። ይህንን ተከትሎ የክልሉ ነዋሪዎች ለሞት እና  ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች እየተጋለጡ መሆናቸውን እየገለፁ ነው።
የሰብዓዊ ተሟጋች ድርጅቶችም በክልሉ የሚፈፀም የንፁሃን ግድያ እንዳሳሰባቸው ሲገልፁ መቆየታቸው ይታወሳል። በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የክልሉን የሰላም እና የፀጥታ ሀላፊ  እንዲሁም  የኮማንድ ፖስት አባል ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።


ፀሀይ ጫኔ
ማንተጋፍቶት ስለሺ