1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢትዮጵያ የሴቶች መብት ይዞታ

ሐሙስ፣ የካቲት 29 2010

ሴቶች ላይ የሚፈፀሙ አካላዊ እና ስነልቦናዊ ጥቃቶች የትኛዉንም የኅብረተሰብ ክፍል እንደማይለዩ ነዉ የሚነገረዉ። የፊታችን ሐሙስ በሚታሰበዉ የዓለም የሴቶች ቀን «በገጠር እና በከተማ የሴቶችን ሕይወት ለማሻሻል እንቅስቃሴ የማድረጉ ጊዜ አሁን ነዉ» የሚል መሪ ቃል ተሰጥቶታል።

https://p.dw.com/p/2tnUS
Gemälde von Haimanot Messele
ምስል Haimanot Messele/Foto: DW/A. Tadesse Hahn

ዛሬም ትኩረት የሚያሻቸዉ ጥቃቶች አሉ፤

ኢትዮጵያ ዉስጥ በሴቶች አካልም ሆነ ስነልቡና ላይ የሚፈፀመው ጥቃት የድሮ ታሪክ ሳይሆን አሁንም ያለ መሆኑን የሚያመላክቱ የተለያዩ መረጃዎች እንደሚደርሱት ነዉ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማሕበር የሚገልፀው። የጥቃቱ ሰለባዎች ታዲያ በሁሉም የኑሮ ደረጃ እና የኅብረተሰብ ክፍል ዉስጥ የሚገኙ መሆናቸዉንም ልብ ይላል። ማሕበሩ በአንድ ዓመት ብቻ ማለትም የዛሬ ሦስት ዓመት የደረሱትን አቤቱታዎች መሠረት አድርጎ ባወጣዉ መረጃ መሠረት በአንድ ዓመት ዉስጥ ከትዳር ጋር የተገናኙ 3,754 የቤቱታዎችን አስተናግዷል። እንደማሕበሩ 2,105ቱ ሴቶች የተፈፀሙ ጥቃቶች የሚያሳዩ ናቸዉ። የማሕበሩ የሥራ አስፈፃሚ ዳይሬክተሯን ወ/ሮ ሜሮን አራጋዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ የሴቶች መብት ሙሉ ለሙሉ እንዲከበር ገና ብዙ ጥረት ይጠይቃል ነዉ የሚሉት።

«እንደሚታወቀዉ በሀገርን ላይ የፆታ እኩልነት ሙሉ ለሙሉ ለመከበር ገና እጅግ ብዙ ጥረት እና ጊዜ የሚፈልግ ነዉ። ምክንያቱም አሁንም በማኅበረሰባችን ዘንድ ፆታን መሠረት አድርገዉ የሚፈፀሙ ጥቃቶች ቀጥታ ምክንያታቸዉ ማኅበረሰቡ የፆታን እኩልነት አስመልክቶ ካለዉ የተዛባ አመለካከት ስለሆነ ከዚያ ጋር ተያይዞ ሴቶች ላይ የተለያዩ ጥቃቶች ይፈጸማሉ።»
ጥቃቶቹ በአካል እና በስነልቦና ላይ የሚፈፀሙ መሆናቸዉን አልፎ ተርፎም እስከ ግድያ እንደሚደርስም ያብራራሉ። ላለፉት 22 ዓመታት የሴቶችን መብት ከማስከበር አኳያ የተደረጉ እንቅስቃሴዎች ካስገኙት ዉጤቶች መካከልም በትዳር ዉስጥ በሚፈጠሩ ችግሮች ሰበብ ሴቶች ላይ ይደርሱ የነበሩ ጥቃቶች በሕግ መፍትሄ እንዲያገኙ ያመቻቸዉ የቤተሰብ ሕጉ ላይ ማሻሻይ መደረጉንም ያነሳሉ። የወንጀል ሕጉ ላይም ተመሳሳይ ማሻሻያዎች መካተታቸዉንም እንዲሁ።

«በፊት ጥቃት ሆነዉ ያልተያዙ ወንጀል ሕጉ የማይሸፍናቸዉ ወንጀል ሆነዉ እንዲካተቱ ፤ ወንጀል ህጉ ዉስጥ ተካተዉ የቅጣት መጠናቸዉ አነስተኛ የሆኑ ከፍተኛ እንዲሆኑ ለማድረግ እና ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች የተሻለ የሕግ ሽፋን እንዲኖራቸዉ ተደርጓል። ነገር ግን አሁንም ቢሆን የማኅበረሰባችን አመለካከት ብዙ መቀየር የሚፈልግ ነዉ። የጥቃት ሰለባ ሴቶች አሉ በብዛት፤ ለእነሱ ደግሞ ያሉትን ሕጎች ከማስፈፀም አንጻር የሕግ አፈጻጸሙ ላይ መሥራት እጅግ ያሻል። ምክንያቱም ከፍተኛ የሕግ አፈጻጸም ክፍተት ስላለ ማለት ነው።»
አፈፃጸሙ ጥያቄ ማስነሳቱ እንዳለ ሆኖ ሕግን በተመለከተ ኢትዮጵያ ጥሩ ጥሩ ሕጎች እንዳሏት የሚናገሩት የሕግ ባለሙያዋ፤ በአሁኑ ወቅት ሴቶች ስለመብታቸዉ የመጠየቅ የግንዛቤ ደረጃቸዉ እያደገ መምጣቱንም አስተዉለዋል ወ/ሮ ሜሮን። ግን አሁንም ብዙ ሊሠራበት የሚገባ ትኩረት የሚሻ መሆኑን ያስገነዝባሉ።

«ሴቶች ላይ ያለዉ የየራሳቸዉን መብት ከማወቅ እና ሲጣሱ ደግሞ የመጠየቅ ብቃት በተሻለ ሁኔታ አለ። ምክንያቱም የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማሕበር ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱ ላይ ሴቶች መብቶቻቸዉ እንዲከበሩ የሚደረጉ ጥረቶች ሴቶች መብቶቻቸዉን እንዲያዉቁ፣ ግንዛቤ እንዲያገኙ እና ራሳቸዉን እንዲከላከሉ እንዲሁም ደግሞ ጥሰት በሚኖርበት ጊዜ እንዲጠይቁ የሚያስችል ሥርዓት እና የሚያግዙ ተቋማት ስላሉ። ነገር ግን አሁንም ቢሆን እጅግ ችግሩ ትኩረት የሚሻ እና ልንሠራበት የሚገባ ጉዳይ ነው።»
የሴቶች መብት ጉዳይ ሲነገር በቀጥታ የሚፈጸምባቸዉ ፆታዊ ጥቃት ይታሰባል። የአንድ ኅብረተሰብ መሠረት የሆኑት ሴቶች የመብት ጉዳይ ግን ከዚህም ያለፈ ነው። ማኅበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊ እንዲሁም የፖለቲካ መብቶቻቸዉን ሁሉ ያካትታል። በዚህ ረገድ ያሉ መብቶቻቸዉ ሙሉ በሙሉ እንዳይከበሩ ታዲያ የማኅበረሰቡ አመለካከት አሁንም እንቅፋት እንደሆነ ነዉ ወ/ሮ ሜሮን የሚያስረዱት።
እንዲህ ያለዉ የተዛባ አመለካከትም ከተማ ሆነ ገጠር ልዩነት እንደሌለ የሚያሳየዉም አዲስ አበባ ላይ የቤት ንብረትን ጉዳይ አስመልክቶ የሚፈፀሙ ድርጊቶች መሆናቸዉንም ይናገራሉ። እንዲህ ያሉ የመብት ጥሰቶች ሲያጋጥሙም ሴቶቹ የት ሄደዉ አቤቱታ ማቅረብ እንዳለባቸዉ አለማወቃቸዉ እና ድጋፍም አለማግኘታቸዉ ተጠቂዎች እንዳደረጋቸዉ ነዉ የሕግ ባለሙያዋ የገለፁት። 
የኢትዮጵያን የሴቶች የመብት ይዞታ ከሌሎች የአፍሪቃ ሃገራት ሴቶች ሁኔታ ጋር ለማነፃፀር ጥናት መደረግ እንዳለበት የሚናገሩት የሕግ ባለሙያ፤ በተጻፉ ሕጎች ደረጃ ሲታይ ግን ኢትዮጵያ ጥሩ ሕጎች እንዳሏት ነዉ ያመለከቱት።  አሁንም ቢሆን ሕግ ሊወጣላቸዉ የሚገቡ የጥቃት ዓይነቶች እንዳሉም ግን ጠቁመዋል። ማሕበራቸዉ ከሚያስተናግዳቸዉ አብዛኛዎቹ የቤት ዉስጥ ጥቃት ሰለባዎች መሆናቸዉን ያመለከቱት ወ/ሮ ሜሮን አቤቱታዎቹ የሚታዩበት መንገድ ለችግሩ መባባስ ምክንያት መሆኑን ነዉ የሚናገሩት።
ሁሉም በሚባል ደረጃ ኢትዮጵያዉያን ሴቶች ለወሲብ ትንኮሳ እና ጥቃት የተጋለጡ መሆናቸዉን የሚገልፁት የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማሕበር የሥራ አስፈፃሚ ዋና ዳይሬክተር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአሲድ የሚፈፀምባቸዉ ጥቃት አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል ይላሉ።
«ሁሉም ኢትዮጵያዉያን ሴቶች ማለት ያስደፍረኛል፤ ትንሹ ከምንለዉ ሕይወት እስከማጣት ድረስ የሚደርስ ጥቃት የሚደርስባቸዉ በወሲባዊ ትንኮሳ አማካኝነት ነው። ስለዚህ ሴቶች ከቤታቸዉ ጀምሮ እሥራ ቦታቸዉ፣ እትምህርት ቦታቸዉ ወይም ሌላ ማኅበራዊ ኑሯቸዉን ሊያከናዉኑ በሚሄዱባቸዉ መንገዶች ሁሉ ከማድነቅም ጋር ተያይዞ ፤ ከስድብ ጋር ተያይዞ ከመጎንተል ጋር ተያይዞ የወሲብ ትንኮሳ ሰለባዎች ናቸዉ። በተለይ አሁን ደግሞ እየተለመደ የመጣዉ አገራችን ላይ የአሲድ መድፋት ጉዳይ ነው።» 
ይህ ማሕበር የጥቃት ሰለባ ለሆኑ ሴቶች በሚሰጠዉ አገልግሎት በተለይ የአካል ጉዳተኛ ለሆኑት በየደረጃዉ የሚችለዉን እያበረከተ መሆኑን ነዉ የሚገልጸዉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ ሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ፆታዊ ጥቃቶችን አደባባይ በማዉጣት አቅም ለሌላቸዉ ተጎጂዎች የነፃ የሕግ አገልግሎት ሲሰጥ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ማሕበራቸዉ ባከናወናቸዉ የማንቃት ሥራዎቹ ዉጤት አምጥቷል ብለዉ ያምናሉ ወ/ሮ ሜሮን።   
በተቃራኒዉ ግን ዛሬም ይህ መረጃ የሌላቸው በጓዳ እና በገጠር ያሉ በርካታ ሴቶች መኖራቸዉን ሳያስገነዝቡ አላለፉም። ከነገ በስተያ የሚታሰበዉ የዓለም የሴቶች ቀን የዘንድሮዉ መሪ ቃል «በገጠር እና በከተማ የሴቶችን ሕይወት ለማሻሻል እንቅስቃሴ የማድረጉ ጊዜ አሁን ነዉ» የሚል ነዉ።

Ethiopian Women Lawyers' Association Logo
Äthiopien - 55 days of Ethiopian fasting
ምስል DW/J. Jeffrey

 ሸዋዬ ለገሠ 

አዜብ ታደሰ