1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመን ፖሊሲ በሃማስ

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 6 2016

ጀርመን የኢሚግሬሽን ህጓን እያሻሻለች መሆኑን የጠቀሱት ክሊንግቢል ጸረ ሴማዊነትን እና ሽብርን የሚደግፉት ግን የጀርመን ፓስፖርታቸውን ይነጠቃሉ ብለዋል።

https://p.dw.com/p/4Xdle
ኦላፍ ሾልስና ቤንጃሚን ኔታንያሁ
የጀርመን መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልስና የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁምስል Maya Alleruzzo/Pool/AP/picture alliance | Kay Nietfeld/dpa/picture alliance

በእስራኤል ሃማስ ጦርነት ጀርመን የምትከተለው ፖሊሲ

በእስራኤል ሃማስ ጦርነት ጀርመን የምትከተለው ፖሊሲ
ጀርመንን ጨምሮ በአውሮጳ፣ አሜሪካና ሌሎች ሃገራት "አሸባሪ" ተብሎ የተሰየመው ሐማስ በጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ጥቅምት 7 ቀን 2023 ዓ.ም የጋዛን አጥር ሰብሮ በመግባት በሙዚቃ ድግስ ላይ የነበሩትን ስቪል እስራኤላውያን ላይ በፈጸመው ጥቃት ከ260 በላይ እስራኤላውያን መሞታቸውን ተዘግቧል። ከዚያም ቀጥሎ ሃማስ ወደ እስራኤል በተኮሳቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ተወንጫፊ ሮኬቶችና ከባድ መሳሪያዎች እንዲሁም እስራኤል በወሰደችው የአጸፋ እርምጃ ከሁለቱም ወገኖች በርካታ ንጹሃን ስቪል ዜጎች አልቀዋል። እስከዛሬ ረፋዱ ድረስ የነበሩ የጉዳት መጠንን የሚያመላክቱ ይፋዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት እስራኤል በፈጸመችው የበቀል እርምጃ ከፍልስጤማውያን በኩል 2,800 ገደማ ሲሞቱ  ሃማስ ባስወነጨፋቸው ሮኬቶችና መድፎች ደግሞ ከ 1,400 በላይ እስራኤላውያን ሞተዋል።  ከሁለቱም ወገን ከ6ሺህ የማያንሱ ሰዎች እንደቆሰሉም የተለያዩ ዘገባዎች ያመላክታሉ።
በሁለቱም በኩል የቀጠለውና ሁለተኛ ሳምንቱን ያሳለፈው ጦርነት ወደ አካባቢው ሐገራት እንዳይዛመት አስግቷል። በተለይም "ከጀርባ አለች" የምትባለው ኢራን በቀጥታ እጇን ካስገባች ጦርነቱ ከቀጠናዊ ጉዳይንነት ወጥቶ ዓለም አቀፋዊ ቅርጽ ሊይዝ እንደሚችል የፖለቲካ ተንታኞች ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።
የተለያዩ የዓለም ሃገራት በዚህ ጦርነት ላይ የሚከተሉት ፖሊሲና ሊኖራቸው ስለሚገባ ሚና በይፋ እየገለጹ ነው። ጀርመንም ጦርነቱን በተመለከተ የምትከተለውን ፖሊሲና በሃገር ውስጥም መተግበር ስለሚገባቸው መመሪያዎች ይፋ አድርጋለች።
የጀርመን መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልስ ለምክር ቤት እንደራሴዎች ባደረጉት ንግግር እንደተናገሩት።

" በዚህ ወቅት ጀርመን አንድ አማራጭ ብቻ ነው ያላት፤  ከእስራኤል ጎን መቆም። ይህም  ለእስራኤል ደህንነት መቆም ትልቁ የጀርመን መንግስት ቁርጠኝነት ነው ማለታችን ነው። ከራሳችን ታሪክ ከሆሎኮስት የመነጨው ሃላፊነት፤ የእስራኤልን መንግስት ህልውና እና ደህንነት መደገፍ ዘልአለማዊ ያደርገዋል።
 በእስራኤል የሃገሪቱን ዜግነት የወሰዱ በሺዎች የሚቆጠሩ ጀርመናውያን አሉ። በዚህ በጀርመንም በሺዎች የሚቆጠሩ የጀርመን ዜግነት የወሰዱ እስራኤላውያን ይኖራሉ። በሃማስ ከታገቱት መካከል በርካታ ጀርመናውያን ይገኙበታል።"

ስለ ኢራን

ከሃማስ ጀርባ ኢራን እንዳለችበት አሜሪካን ጨምሮ በርካታ ሃገራት ይከሳሉ። መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልስም ከኢራን ድጋፍ ውጭ ሃማስ ይህን ጥቃት ሊፈጽም እንደማይችል ነው ያስረዱት።

"ሃማስ ከአለፉት ዓመታት ጀምሮ ያለኢራን ድጋፍ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ጥቃት በእስራኤል ግዛት ውስጥ ሊፈጽም አይችልም። የኢራን አገዛዝ ባለስልጣናትና አንዳንድ የመንግስት ተወካዮች ጥቃቱን አስመልክተው የሰጡአቸው መግለጫዎች በጣም የወረዱ እና ደስ የማይሉ ናቸው። በቴህራን ውስጥ ያለው አመራር ያለምንም ሃፍረት እውነተኛ ገጽታውን እየገለጠ ነው። ይህም በጋዛው ጦርነት ላይ ያለውን ሚና ያረጋገጠ ነው።"

ስለፍልስጤም ባለስልጣናት

 ከዚ በተጨማሪ ሾልስ በእስራኤል ስለደረሰዉ ጥቃት የፍልስጤም ባለስልጣናት ዝምታን አውግዘዋል።

"የፍልስጤም ባለስልጣናት እና ፕረዚደንት ማህሙድ አባስ ለምን ይህን የሽብር ጥቃት አላወገዙም ብዬ እራሴን እጠይቃለሁ። ዝምታቸው አሳፋሪ ነው ለማለት እወዳለሁ።"

መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልስ
መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልስ ጀርመን ጦርነቱን በተመለከተ የምትከተለውን ፖሊሲና በሃገር ውስጥም መተግበር ስለሚገባቸው መመሪያዎች ይፋ አድርገዋል።ምስል Fabian Sommer/dpa/picture alliance

ለፍልስጤም ስለሚደረጉ የልማት ድጋፎች

 ሾልስ ለፍልስጤማውያን ስለሚደረገው ድጋፍም መንግስታቸው የሚከተለውን ፖሊሲ ይፋ አድርገዋል። ከፍልስጤም ጋር የሚኖረው የልማት ትብብር እንደሚያጤኑት እና የእስራኤልን ደህንነትና ጸጥታን በሚያረጋግጥ መልኩ እንደሚፈጸም አስረድተዋል። ከጀርመን መንግስት በኩል የሚደረጉ ማንኛውም ድጋፎች በሃማስ እጅ እንዳይወድቁ መንግስታቸው ብርቱ ጥንቃቄ እንደሚያደርግም ነው መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልስ ይፋ ያደረጉት።


በጀርመን ስለሚኖሩ የሃማስ ደጋፊዎች
ሌላው መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልስ ያነሱት ጉዳይ በጀርመን ውስጥ የሚኖሩ የሃማስ ደጋፊዎችን በተመለከተ ነበር። የሃማስ ደጋፊዎች በተለያዩ የጀርመን ከተሞች ባካሄዷቸው ሰልፎች የእስራኤልን ባንዴራ አቃጥለዋል፤ ጀርመንን ጨምሮ በአውሮጳና አሜሪካ እንዲሁም በሌሎች ሃገራት "አሸባሪ" ተብሎ የተፈረጀውን ሃማስን እንደሚደግፉ ገልጸዋል። መራሄ መንግስቱ በእነዚህ ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ነበር አስረግጠው የተናገሩት። የሃማስን ድርጊት አጥብቀን እናወግዛለን ያሉት ሾልስ ከምንም በላይ ይህን ጥቃት በመላው አካባቢው ላይ ወደለየለት ግጭት እንዳይቀየር የምንችለውን ሁሉ እያደረግን ነው፤ እናም ሁሉም ሰው በዚህ ሁኔታ ሽብርን ከማባባስና ከማስቀጠል እንዲቆጠብ እናስጠነቅቃለን ሲሉም አክለዋል።
ይህን ሽብር የሚያወድስና የሚደግፍ ሁሉ ተጎጂዎችን ማዋረድ ብቻ ሳይሆን ሰብአዊ ክብርንና የጀርመንን ህገመንግስት የረገጠ ተግባር ነው። እንደዚህ አይነት ተግባር ያስደነግጠኛል ትክክልም አደለም። በማለትም ለሸንጎው አስረድተዋል።

የጀርመን ካርታ
የጀርመን ፌደራላዊ ክፍለግዛቶችምስል DesignIt/Zoonar/picture alliance

በጀርመን ለሃማስ ድጋፍ ያረርጋሉ የተባሉት የተለያዩ አደረጃጀቶችም እንደሚታገዱም ነው ጀርመን ያስታወቀችው። ከነዚህም አንዱ ሳሚ ዱን የተባለ የፍልስጤም የትብብር መረብ እንደሚገኝበት ተጠቁሟል። የትብብር መረቡ አባላት በጀርመን ዋና ከተማ በርሊን ሃማስ በእስራኤላውያን ላይ ጥቃት በመፈጸሙ ደስታቸውን ሲገልጹ፤ እንዲሁም ለአላፊ አግዳሚው እንደቸኮሌት ያሉ ጣፋጭ ነገሮችን ሲበትኑ ታይቷል። መራሄ መንግስት ሾልስ ይህን ድርጊት የጀርመንን እሴቶች እንደሚጻረር በመግለጽ በጀርመን ውስጥ በምልክት ጭምር የሃማስን የወንጀል ድርጊቶችን ማወደስ በሕግ እንደሚያስጠይቅ በአጽንኦት አስረድተዋል።
በጀርመን ውስጥ ወደ 500 የሚሆኑ የትብብር መረቡ አባላት ያሉ ሲሆን አብዛኛዎቹ የጀርመን ዜግነት ያላቸው መሆኑን ይነገራል። የጀርመን የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ እንዲህ ዓይነት ድርጊት የሚፈጽሙትን ፓስፖርታቸው እንደሚነጠቁና እንደሚባረሩ ነው ያስጠነቀቀው።
ሚንስቴር መስሪያቤቱ  በሃማስ ደጋፊዎች ላይ ጠንከር ያለ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ በገለጸበት መግለጫው  የሃማስ ደጋፊዎችን ከሃገሩ እንደሚያባርራቸው በሚኒስትሯ በኩል ይፋ አድርጓል። የጀርመን የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር  ናንሲ ፌዘር የሃማስ ደጋፊዎችን ለማባረር ማንኛውም ሕጋዊ እርምጃ እንጠቀማለን ሲሉ ነው በመግለጫቸው የተናገሩት።
የ ናንሲ ፌዘር መግለጫ በሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ መሪም ድጋፍ አግኝቷል። የፓርቲው መሪ ሎርስ ክሊንግቢል "የሃማስ ደጋፊዎች፤ በጎዳናዎች ላይ ወጥተው ሃማስን የሚደግፉ ከሆነ  ከጀርመን ይባረራሉ" ሲሉ ዝተዋል። አክለውም በሃማስ ደጋፊዎች ላይ ሁሉም ሕጋዊ እርምጃዎች ይወሰዳሉ ብለዋል።
ጀርመን የኢሚግሬሽን ህጓን እያሻሻለች መሆኑን የጠቀሱት ክሊንግቢል ጸረ ሴማዊነትን እና ሽብርን የሚደግፉት ግን የጀርመን ፓስፖርታቸውን ይነጠቃሉ ብለዋል።

 ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

አዜብ ታደሰ