1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የይቅርታ ባህላችን

ሐሙስ፣ ግንቦት 30 2010

«አንድ ፖለቲከኛ ማንን መምሰል ነዉ ያለበት ተብሎ ቢጠየቅ፤ የወጣበትን ማኅበረሰብ ነዉ ። በእዉቀት በአሰራር በብልሃት መቅደም አለበት እንጂ ጭራሽ ያፈነገጠ አካሄድ መያዝ የለበትም። ኢትዮጵያዉያን እጅግ በጣም ጥሩ የሆነ የይቅርታ ባህል አለን። ብዙ ባህል እያለን ፖለቲከኞች ብዙ ጊዜ እነዚህን ማኅበራዊ ባህላዊ ሥርዓቶች አይጠጉዋቸዉም።»

https://p.dw.com/p/2z6KP
Äthiopien Culture of Apology
ምስል DW/A. Tadesse

«ከታጠቡ ላይቀር ከክንድ ከታረቁ ላይቀር ከሆድ»

«የብዙ ፖለቲከኞችን፤ ኢህአፓ፤ መኤሶ፤ ኢዲዉ  ምናምን ብለዉ ተከፋፍለዉ ሲታኮሱ የነበሩ ወገኖች መጨረሻቸዉ እልቂት ነበር። እናም እልቂትና በእልቂት ነዉ ያለቅነዉ። የደርግ መንግሥትም ያለቀዉ በእልቂት ነዉ። ቀጥሎም ሰዎች እልቂት ሊመጣ ይችላል ብለዉ ሥጋትም ነዉ ያላቸዉ። እና ይህን ሁሉ ማከም የሚችለዉ ይቅርታ ብቻ ነዉ። ሂሳብ ማወራረድ ማናችንንም ሊክመን አይችልም ። እንዲህ ተደርገን ነበር፤ አሁን እንዲህ ማድረግ አለብን ፤ የሚል ጊዜ ጥበቃና ሁኔታዎችን የማመቻቸት ሂደት ማንንም ሃገር አቅንቶ አያቅም። ይቅርታ ግን ትልቅ ነዉ። »

Äthiopien - Thanksgiving in Irreecha 2015
ምስል DW/T. Waldyes

የዳንኤል እይታዎች የሚል የግል ድረ-ገጽ ያላቸዉና በተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ አስተያየታቸዉን የሚሰጡን ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ ይቅር ባይነትን እንዴት ይገልፁታል? ስንል ለጠየቅናቸዉ ከሰጡን አስተያየት የተወሰደ ነዉ። በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግሥት ለዓመታት በእስር ላይ የቆዩ ሰዎችን በይቅርታ እየለቀቀ ይገኛል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣናቸዉን ሲረከቡ «መጭዉ ጊዜ የፍቅርና የይቅርታ ነዉ» ባሉት መሠረት፤ የገቡትን ቃል እየተገበሩ ነዉ ሲሉ ብዙ ኢትዮጵያዉያን በተለያዩ ዘዴዎች ምስጋናቸዉንና ድጋፋቸዉን እየገለፁ ነዉ። እርሶስ ይቅር ባይነትን እንዴት ይገልፁታል? የኢትዮጵያዉያን የይቅርታ ባህልስ እንዴት ይገመገማል? ይቅር ባይነት አልያም የይቅርታን ምንንነት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ያስረዱናል።    

«ይቅርታ ቃል አማረኛ ሲሆን ከማስቀረት ጋር የተያያዘ ነዉ። አንድን የተደረገ ነገር  እንዳልተደረገ አድርጎ ከመሻር ጋር የተያያዘ ነዉ ይቅርታ።  ኢትዮጵያ ዉስጥ በሚገኙ ዩንቨርስቲዎች በሁሉም የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች፤ ባህላዊ የእርቅ ሥነ-ስርዓቶች በብዙ ተጠንቶአል።  በሁሉም ብሔረሰቦች ባህል ዉስጥ የምናገኘዉ አንድ ነገርን ይቅር ብሎ የማለፍን ባህል ነዉ። ይህ ያኖረን ባህል ነዉ። ይቅርታ በሕዝቦች መካከል ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ጎሳዎች መካከል እንኳ ችግሮች ተፈጥረዉ ያ በይቅርታ የሚያልቁባቸዉ ታሪኮችም አሉን፤ ባህሎችም አሉን።»

የኢትዮጵያዉያን የይቅርታ ባህል ምን ያህል የጎለበተ ነዉ? ይቅር ስንልስ ምን ያህል ከልባችን ነዉ?

Flüchtlingslager im Kongo nahe Aba
ምስል Simona Foltyn

«ፖለቲካዉ ባህሉን ሊወርሰዉ ስላልቻለ ነዉ እንጂ፤ በባህሉ እኮ የተጣላ እና ይቅር የተባባለ እስከ መጋባት ድረስ ይሄዳል። አንዱ አንዱን ገድሎ እንኳ መጨረሻ የእርቅ ሥነ ስርዓት አለዉ። መጀመርያ ሽማግሌዉ ይገባበታል። እንዲያ እያለ እርቁ ይካሄዳል ።በሃገራችን አባባል «ሃጥያት በንስሃ በደል በካሳ ይባላል»። ስለዚህ ያ የበደለ ሰዉ የቀማዉን መልሶ የበደለዉን ክሶ ይቅር ከተባባለ በኋላ፤ አንድላይ ይበላል አንድ ላይ ይጠጣል፤ ከዝያ በኋላ የበለጠ እርቁን እና ይቅርታዉን ጠንካራ ለማድረግ ልጆችን እስከማጋባት ድረስ ይሄዳል። እንደዉም በኛ «ከታጠቡ ላይቀር ከክንድ ከታረቁ ላይቀር ከሆድ» የሚባል አነጋገር አለ። »

በየትኛዉም አይነት ሃይማኖቶች አስተምህሮ ዘንድም ይቅር ባይነት አፍቃሪ፣ ቸር፣ ርኁርኁርና አዛኝ ከኾነው ከፈጣሪ ዘንድ ከተቀበልነው ገደብ የለሽ ይቅርታና ምሕረት ለሌሎችም ወዳጅና ጠላት ሳንልና ሳንለይ፣ ሳንሰስት የምናካፍለውና የምንከፍለው የፍቅር ዕዳችን እንደኾነ ነው አብዝተው የሚናገሩት፣ የሚያስተምሩት። ከሃይማኖታዊ አስተምህሮ ባሻገርም በጤና ሳይንስና እና በሥነ ልቦና ጥናት ረገድም ይቅር ባይነት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው እሙን ነዉ። የባለሙያዎች ጥናቶች እንደሚያሳዩትም ነገሮችን በይቅርታ ማለፍ መቻል የዕለት ተዕለት ማኅበራዊ ግንኑነታችንን ጤናማና ሚዛናዊ እንዲሆን ከማድረግም ባሻገር ከተለያዩ የጤና እክሎችና በሽታዎች እንደሚታደገንና፣ እንዲሁም ሕይወትን በፍቅርና በተስፋ፣ በደስታና በሰላም ለመኖር የሚያስችለንን ኃይል በሕይወታችን እንደሚጨምርልን ያስረዳሉ። ዲያቆን ዳንኤል ስለሰሞኑ የይቅርታ መስመር እንዲህ ይላሉ።  

«ወደኋላ አንድ ነገር መነሻ ላድርግ እና በኛ ሃገር ባህሎች፤ ይቅርታ ሰምሮ እንዲኖር አራት ነገሮች ያስፈልጋሉ ይባላል። አንደኛ የሁለቱ ይቅር ተባባዮች ፤ ይቅርታ ጠያቂዎች እና ይቅርታ ተቀባዮች፤ ወይም ሁለቱ ይቅርታ ጠያቂዎች፤ ሦስተኛ ይቅርታዉን የሚያከናዉኑት  ሽማግሌዎች አራተኛ ሕዝቡ ናቸዉ። እነዚህ አራቱ ናቸዉ በይቅርታዉ የሚተባበሩት ።አለበለዝያ በኋላ ላይ ይቅርታዉን ያፈረሰዉን ሰዉ ሽማግሌዎቹ ይረግማሉ፤ ሕዝቡም ያገለዋል። ከይቅርታ በኋላ አንድ ሰዉ አንድ አፍራሽ ነገር ቢያደርግ፤ በማኅበረሰባችን ዉስጥ በጣም በጣም ነዉር ነዉ። መጀመርያ ካጠፋዉ ጥፋት የባሰ ነዉ፤ ጥላቻ የሚደርስበት። እናም ሰሞኑን ከመንግስት በኩል የታየዉ ይቅርታ አካሄድ ከባህሉ አንጻር፤ ከኖርንበት ባህል አንጻር ስናየዉ፤ የሚያስደንቅ ባይሆንም፤ ከፖለቲካ ባህላችን አንጻር ስናየዉ ግን አዲስ መስመር ነዉ። እንደዉም ፖለቲካችን የባህላችን የይቅርታ አካሄድ ተከትሎ አለመሄዱና የመጠፋፋት መንገድን ይዞ መሄዱ ያደረሰብንን ኪሳራ ያየነዉ ነዉ። አሁን የተጀመረዉ የማይቻል የሚመስለዉን ከባድ የሚመስለዉን መራራ የሚመስለዉን ነገር በይቅርታ የማለፍ አካሄድ ግን እዉነት ሃገር የሚገነባ፤ ከባህሉ ጋር የተጣጣመ ስለሆነ ሕዝቡ በደስታ ነዉ የተቀበለዉ። ሕዝቡ በደስታ የተቀበለዉ ድሮም ባህሉ ይህን የሚፈቅድ ስለሆነ ነዉ። ድሮም ፖለቲከኞች የሄዱበት መንገድ ከሕዝቡ ባህል ዉጭ ስለሆነ ነዉ ። ከሁሉም ባህል ከሰሜኑም፤ ከደቡቡም፤ ከምዕራቡም፤ ከምስራቁም ባህል ዉጭ የነበረ ነገር ስለነበር ነዉ። ስለሆነም ሕዝቡ አሁን በታየዉ የይቅርታ አካሄድ በጣም ደስተኛ ነዉ።»

Äthiopien 199. Geburtstagsfeier Kaiser Tewodros II.
ምስል Gebeyehu Begashaw

የይቅርታ ባህላችንን ካለበት በይበልጥ ማጎልበት ይቻላል?

«አዎ በጣም ማጎልበት እችላለን ። እንደኔ አመለካከት ባህላችንን እንጠቀምበት ፖለቲከኞች ከባህሉ አይራቁ ። አንድ ፖለቲከኛ ማንን መምሰል ነዉ ያለበት ተብሎ ቢጠየቅ፤ የወጣበትን ማኅበረሰብ  ነዉ መምሰል ያለበት ነዉ ። በእዉቀት በአሰራር በብልሃት መቅደም አለበት እንጂ ጭራሽ ያፈነገጠ አካሄድ መያዝ የለበትም። እኛ እኮ አንዴ አሜሪካ ሄደን ከአሜሪካ ስንጎትት፤ ቀጥሎ ራሽያ ገብተን ከራሽያ ስንጎትት ፤ ከዝያ አልባንያ ሄደን ከልባንያ ስንጎትት፤ ቻይና ወርደን ከቻይና ስንጎትት ነዉ የኖርነዉ። ጦሱም የመጣብን በዝያ ምክንያት ነዉ። ወደ ባህላችን ገብተን ከባህላችን ብንነሳ ኖሮ እዚህ ሁሉ ደረጃ ላይ አንደርስም ነበር። ከባህሉ የተፋታ ፖለቲካ ይዘን ነዉ አሁን የደረስንበት ጦስ የደረስነዉ። ባህሉን መጠቀም ብንችል፤ የባህሉን እሴቶች መጠቀም ብንችል የፖለቲካዉን ሕመም ሊያክም የሚችል የይቅርታ ባህል አለን። የመጠፋፋቱን በሽታ ሊያክም የሚችል ባህል አለን። ትልቁን ቦታ የያዘዉ መንግስት ይህን ባህል ከጀመረዉ፤ ሌላዉ ሕዝብ ደግሞ ያንን ተከትሎ በየደረጃዉ ማስቀጠል አለበት። መንግስት ከላይ የጀመረዉን ማኅበረሰቡ በየደረጃዉ እስከታች ድረስ በመዉረድ ባህሉ ተጠናክሮ እንዲሄድ የሚያደርርገዉ ይመስለኛል።» 

Äthiopien Debre Zeyit - Thanksgiving
ምስል Amensisa Ifa

የዶይቼ ቬለ የማኅበራዊ መገናኛ ተከታታዮችና አድማጮች ስለይቅር ባይነት ያላቸዉን አስተያየት በጽሑፍ እንዲሰጡን ጠይቀን ነበር። አድማጮቻችን ሰሞኑን በኢትዮጵያ የታየዉን ምህረት በመጥቀስ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል።    

ሴኔራ ንጉሴ አምቦ የተባሉ የዶይቼቬለ ፌስ ቡክ ተከታታይ አስተያየታቸዉን እንዲህ ሲሉ አስቀምጠዋል። «የኢትዮጵያን የይቅርታን ባህል በወሬ ብቻ ነበር ሰምተን የምናዉቀዉ። አሁን ግን እውነቱን በዓይናችን አይተናል፤ ቀምሰነዋል፤ በእጃችን ዳሰናል፤ ፍሬውን በልተን ተጠቅመናልም ።» ብለዋል። ኤልሳ ማን ካዲማን የተባሉ ሌላዉ የፌስቡክ ተከታታይ ባስቀመጡት አስተያየት «በጣም ደስ ይላል ማንም ስው ብፁዕህ አይደለም ይሳሳታል ዋናውነገር ያጥፋም አያጠፋም በውይይት ጉዳይን መፍታት ነው እንጅ፤ እርስቤት አመፅን እንጅ የሚፈጥረዉ ለሀገር የሚበጅ ነገርየለም። አሁንም ብዙ ችግሮች ይፈታሉ ብለን እንጠብቃለን» ሲሉ አስተያየታቸዉ አስቀምጠዋል። ቶሎራ ፀጋዬ የተባሉ ሌላዉ የዶቸቬለ  የፌስ ቡክ ተከታታይ በፃፉልን አስተያየት፤ «በጣም የሚገርመዉ ነገር ጠ/ሚ ዶክተር አብይ አሕመድ ከተናገሩት በላይ ነው ቃላቸውን የጠበቁት። ለዘመናት በእስር ቤት ታጉረው ሲማቅቁ የነበሩ ዜጎችን በይቅርታ በሠላም ከቤተሰብ ጋር በማገናኘት በደስታ ያስፈነደቁት ።  1000 ዘመን ግዛልን ብለነዋል። » ብለዋል።

«በይቅርታ የሚገኝ ድል በጦርነት አይገኝም» ያሉን፤ በተለያዩ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ምክርና አስተያየት በመስጠታቸዉ የሚታወቁት አቶ ዉብሸት ወርቃለማሁ ናቸዉ።

Äthiopien Orthodoxes Weihnachtsfest in Addis Abeba
ምስል picture-alliance/abaca/M. W. Hailu

«ይቅርታ አስፈላጊ ነገር ነዉ። እግዚአብሔርም የሚወደዉ ይቅርታን ነዉ። በይቅርታ የሚገኝ ድል በጦርነት አይገኝም ።ይቅርታ ማድረግ ደግሞ ኢትዮጵያ ዉስጥ በሽማግሌዎች የተለመደ ነዉ። ይቅርታ ጥሩ መሆኑን እያመንም ቂም እንይዛለን። ቂም በመያዝ ራስን መጉዳት ነዉ እንጂ የሚጠቅመዉ ነገር የለም። »   

በአገራችን የፖለቲካ ባህል ጎልቶ የታየ የቅርታ አካሄድ መታየቱ ጥሩ ነዉ ሲሉ የተናገሩት በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የታሪክና የሥነ-ጥበብ ታሪክ መመህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር አበባዉ አያሌዉ ናቸዉ።

«ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አሕመድ ጥሩ ጅምር አምጥተዋል። ሃገሪቱን ወደፊት የምታድግበትን፤ የምትሻሻልበትን መንገድ እናምጣ ካልን መጀመርያ ይቅርታ ነዉ። ይቅርታ ቤተሰብን ያቆማል። ቤተሰብ ስንል ለማሳነስ ሳይሆን ሃገርን የሚመሰርተዉ ከታች ከቤተሰብ ጀምሮ የተነሳዉ መዋቅር ነዉ። ቤተሰብ ላይ ያለ ባህል አድጎ ነዉ ማኅበረሰብን የሚገነባዉ። በቀጣይ ማኅበረሰብ አድጎ ነዉ ሃገርን የሚገነባዉ ። ከዚህ አኳያ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አሕመድ የጀመሩት ትልቅ ነገር ነዉ። እስካሁን እንደ ዶ/ር አብይ የተጓዘ መሪ አይተን አናዉቅም። እንድያም ሆኖ ከማኅበረሰባችን ስንነሳ ኢትዮጵያዉያን እጅግ በጣም ጥሩ የሆነ የይቅርታ ባህል አለን። ብዙ ባህል እያለን ፖለቲከኞች ብዙ ጊዜ እነዚህን ማኅበራዊ ባህላዊ ሥርዓቶች አይጠጉዋቸዉም። እስከአሁን ፖለቲካችን ዉስጥ ባህላዊ እሴቶቻችን እና ማኅበራዊ እሴቶቻችንን እንደ አንድ የፖለቲካ ግብዓት የተጠቀመ መሪ የለም። ዶ/ር አብይም ይህን ያጤኑት አይመስለኝም። እነዚህ ትልቅ እሴቶች ናቸዉ ሃገርን ያቆሙ ኅብረተሰብን፤ ቤተሰብን ያቆሙ፤ ደም የተቃባዉን ሁሉ ያቆሙ ስርዓቶቻችን ናቸዉ። በሌላዉ ዓለም ያየን እንደሆነ የፖለቲካ ሥርዓቱ ከባህላዊ ሥርዓቱ የተስማማ ነዉ። እኛ ሃገር ጥሩ ባህላዊና ማኅበራዊ ስርዓት እያለን፤ አብሮ የሚያኖረን የሚያስታርቀን፤ አብሮ የሚያበላ ባህል እያለን በነበሩት ሥርዓቶች ተጠይፈናቸዉ አልተጠቀምንባቸዉም። »

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሠ