1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጀርመኗ ቩፐርታል ከተማ የተከሰተ ፍንዳታ የመኖሪያ ሕንፃን አወደመ

እሑድ፣ ሰኔ 17 2010

በምዕራባዊ ጀርመን ቩፐርታል ከተማ በአንድ የመኖሪያ ህንጻ ላይ ትላንት ለሊቱን በደረሰ ፍንዳታ 25 ሰዎች መቁሰላቸውን ፖሊስ ዛሬ አስታወቀ። ከቆሰለኞቹ ውስጥ አራቱ የከፋ ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል። 

https://p.dw.com/p/30Au0
Detuschland Explosion in Wohnhaus in Wuppertal
ምስል picture-alliance/dpa/H. Kaiser

ትላንት እኩለ ለሊት አቅራቢያ በባለ በርካታ ፎቆቹ የመኖሪያ ህንጻ ላይ የደረሰው የፍንዳታ ድምጽ ከፍተኛ እንደነበር አሶሴትድ ፕሬስ ዘግቧል። ድምጹ በህንጻው አካባቢ ባሉ መኖሪያ ቤቶች ያሉ ነዋሪዎችን ጭምር በድንጋጤ ወደ ጎዳናዎች ያስወጣ እንደነበር ጠቁሟል። የጀርመን ዜና አገልግሎት በበኩሉ ፍንዳታው ከባድ ከመሆኑ የተነሳ የህንጻውን ጣሪያ እና ከላይ ያሉ ሶስት ፎቆችን ሙሉ ለሙሉ ማውደሙን አመልክቷል። ፍንዳታውን ተከትሎ ህንጻው በእሳት የተያያዘ ሲሆን የተወሰነው የፎቁ ክፍል መፈራረስ መጀመሩ ለእሳት አደጋ ተከላካዮች አደጋውን ለመቆጣጠር ያደርጉት የነበረውን ጥረት አዳጋች አድርጎባቸው ነበር ተብሏል። 
የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች አራት የከፋ ጉዳት የደረሰባቸውን ጨምሮ በህይወት ማትረፍ ችለዋል። ወደ ሆስፒታል የተወሰዱት ቁስለኞች የህክምና ክትትል እየተደረላቸው ይገኛል። የአካባቢው ፖሊስ የፍንዳታውን መንስኤ እየመረመረ መሆኑን ዛሬ አስታውቋል።  

ተስፋለም ወልደየስ

እሸቴ በቀለ