1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ንጉስ ቻርልስ ሣልሳዊ ኬንያን ለመጎብኘት ናይሮቢ ገቡ

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 20 2016

የብሪታንያዉ ንጉስ ቻርልስ ሣልሳዊ የንግሥናዉን መንበር ከያዙ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ የኮመንዌልዝ አባል ሃገር የሆነችዉን ኬንያን ለመጎብኘት ዛሬ ከባለቤታቸዉ ከንግሥት ካሚላ ጋር ናይሮቢ ገቡ። ንጉስ ቻርልስ ሣልሳዊ ዛሬ ለአራት ቀናት ኬንያን ለመጎብኘት ናይሮቢ ሲገቡ በፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ አቀባበል አድርገዉላቸዋል።

https://p.dw.com/p/4YGFr
የብሪታንያዉ ንጉስ ቻርልስ ሣልሳዊ ከባለቤታቸዉ ጋር ኬንያን ለመጎብኘት ናይሮቢ ገቡ
የብሪታንያዉ ንጉስ ቻርልስ ሣልሳዊ ከባለቤታቸዉ ጋር ኬንያን ለመጎብኘት ናይሮቢ ገቡምስል Arthur Edwards/The Sun/empics/picture alliance

የብሪታንያዉ ንጉስ ቻርልስ ሣልሳዊ የንግሥናዉን መንበር ከያዙ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ የኮመንዌልዝ አባል ሃገር የሆነችዉን ኬንያን ለመጎብኘት ዛሬ ከባለቤታቸዉ ከንግሥት ካሚላ ጋር ናይሮቢ ገቡ። ንጉስ ቻርልስ ሣልሳዊ ዛሬ ለአራት ቀናት ኬንያን ለመጎብኘት ናይሮቢ ሲገቡ በፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። የብሪታንያዉ ባኪንግሃም ቤተ-መንግሥት ይፋ ባደረገዉ ጋዜጣዊ መግለጫ መሰረት፤ ንጉስ ቻርልስ ሣልሳዊ የኬንያ ጉብኝት በብሪታንያ እና  ኬንያ መካከል በምጣኔ ሀብት ልማት፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና ደህንነትን በተመለከተ የሚያደርጉትን የጋራ የትብብር፤ ማሳያ መሆኑን ገልጿል። ከዚህ በተጨማሪ ንጉስ ቻርልስ ሣልሳዊ በዚህ የኬንያ ጉብኝታቸዉ ወደ ሰባት አስርት ዓመታት ገደማ በዘለቀው የብሪታኒያ ቅኝ ግዛት ዘመን የተፈጸመዉን "አሳዛኝ ገጽታ" አምነው ይቀበላሉ ተብሎ ይጠበቃል። ኬንያ በዚህ ዓመት ከብሪታንያ ቅኝ ግዛት የተላቀቀችበትን 60ኛ ዓመት የነጻነት ቀንዋን ታከብራለች። ንጉሱ እና ባለቤታቸዉ ንግሥት ካሚላ በኬንያ አዲስ የተገነባ ብሔራዊ የታሪክ ሙዚየምን ብሎም ኬንያ በጎርጎረሳዉያኑ 1963 ዓም ከብሪታንያ ነፃ መዉጣትዋን ያወጀችበትን ቦታ ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። ንጉሱ ታዋቂዋን ኬንያዊት የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋች ዋንጂራ ማታይን ለማግኘት ዕቅድ መያዛቸዉም ተገልጿል። 
የብሪታንያ መንግሥት ኬንያን በቅኝ ግዛት በያዘበት ዘመን በተለይም ከጎርጎረሳዉያኑ 1952-1960 ዓም ባለዉ ጊዜ፤ በማዕከላዊ ኬንያ በማው ማው ዓመፅ ወቅት ስለተፈፀመዉ ግፍ እንደተጸጸተ መግለፁ ተሰምቷል። የኬንያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ይፋ እንዳደረገዉ በዚህ አመጽ ወቅት 90,000 ሰዎች እንደተገደሉ እና የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው እንዲሁም ወደ 160,000 ሰዎች በቅኝ ግዛት ባለ ሥልጣናት ታስረዉ፤ ነበር ሲል ግምቱን አስቀምጧል።
 

አዜብ ታደሰ 

ኂሩት መለሰ