1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

ተጠቃሚዎችና ተጎጂዎች እነማን ናቸው? በገበያስ ላይ ምን አይነት ተፅዕኖ ያሳድር ይሆን? 

ረቡዕ፣ ጥቅምት 1 2010

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ብር ከዶላር አንፃር የነበረው የምንዛሪ ተመን ላይ ያደረገውን ቅናሽ ማስፈጸሚያ መመሪያ ይፋ አድርጓል። በአዲሱ መመሪያ የአገሪቱ ባንኮች 30 በመቶ የውጭ ምንዛሪያቸውን ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲያዛውሩ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል።

https://p.dw.com/p/2lf39
Äthiopien Währung Birr
ምስል DW/Eshete Bekele Tekle

የብር መዳከም የዋጋ ግሽበት ሊያስከትል ይችላል

ሰኞ መስከረም 30 ቀን 23.40 ይመነዘር የነበረው አንድ የአሜሪካን ዶላር በማግሥቱ ወደ 26.91 አሻቅቧል። ለውጡ የኢትዮጵያ መንግሥት "የውጭ ንግዱን ለማበረታታት" የወሰደው እርምጃ ውጤት ነው። ስለ እርምጃው ቀድመው ጥቆማ የሰጡት ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ ነበሩ። የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የ2010 ዓ.ም. የመክፈቻ ጉባኤ ሲከፍቱ የአገሪቱ የውጭ ንግድ "ባለበት በመቆሙ ምክንያት የውጭ ምዛሪ ፍላጎት እና አቅርቦቱን ለማሟላት ከፍተኛ እጥረት" አስታውሰው የውጭ ምንዛሪ ተመን ለውጥ እንደሚደረግ ተናግረው ነበር። 

"የ2010 እቅድ ዋነኛ ትኩረትም የኤክስፖርት ምርት እና ግብይት ጉዳይ የሞት ሽረት ተደርጎ መወሰድና ለኤክስፖርት ገቢያችን 80% አስተዋፅዖ የሚያበረክቱትን ቡና፣ሰሊጥ፣ጥራጥሬ፣አበባ እና የቁም እንስሳት በመጠን እና በጥራት በማሳደግ ከፍተኛ ለውጥ በማምጣት ላይ ሊሆን ይገባል። ከዚህ በተጓዳኝ ወርቅ እና ሌሎች ጌጣጌጥ ማዕድናት እንዲሁም እየተስፋፉ የመጡትን ኢንደስትሪ ፓርኮች ማዕከል በማድረግ የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች ኤክስፖርት በፍጥነት እንዲያድግ በማድረግ ላይ ይሆናል። ይኸንንም ለማበረታታት የውጭ ምንዛሪ ተመን ላይ በጥናት ላይ የተመሰረተ ማሻሻያዎች የሚደረጉ ይሆናል።"

Äthiopien Währung Birr
ምስል DW/Eshete Bekele Tekle

የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሐመድ ከዚህ ቀደም ድንገተኛ የተመን ለውጥ በማድረግ የሚታወቀው ብሔራዊ ባንክ አስቀድሞ ማሳወቁ አስገርሟቸዋል። ባለሙያው እንደሚሉት የኢትዮጵያ መንግሥት ለውጭ ምንዛሪ እጥረቱ መፍትሔ ለማፈላለግ ከዚህ ቀደም ችላ ያላቸውን የዓለም የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ ጥቆማዎች ሳይቀበል አልቀረም የሚል እምነት አላቸው። 

"ከአስር ቀን በፊት የዓለም የገንዘብ ድርጅት ያወጣው ዘገባ ስለነበር ጫናም ሳይኖርም አይቀርም የሚል ግምት አለኝ-እንዲያስተካክሉ። ከዚህ በፊት የዓለም ባንክ ያወጣውም ዘገባ ነበር። የዓለም ባንክ ፍተሻ ማድረግ አለባችሁ የሚል {ጥቆማ} ነው። በተደጋጋሚ የነበረ ጫና ስለነበረ እሱንም ከግንዛቤ አስገብቶ መፍትሔ ለመሥጠት ይመስለኛል። »

ማን ይጠቀማል? ማንስ ይጎዳል? 

ብር ባለፉት ሰባት አመታት የነበረውን የምንዛሪ ተመን ያዳከመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ውሳኔ ተጠቃሚዎች እና ተጎጂዎች አሉት። የልማት ኤኮኖሚ የጥናት ባለሙያው (Development economics) አቶ ብስራት ተሾመ በውጭ ንግድ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎችን ቀዳሚ የጥቅሙ ተቋዳሽ ያደርጓቸዋል። 

"ከሁሉም በፊት ኤክስፖርተሩ ተቀዳሚ ይሆናል። ምክንያቱም አንድ ኪሎ ቡና ወደ ውጭ የሚልክ ሰው በዓለም አቀፉ ገበያ የኢትዮጵያ ቡና ሁለት ዶላር ይሸጣል ብለን ብናስብ የውጭ ምንዛሪ 23 ብር አካባቢ በነበረበት ወቅት አንድ ኪሎ ሸጦ 46 ብር ነበር የሚያገኘው። አሁን 54 ብር ያገኛል ማለት ነው። ወደ ውጪ የሚልኩ ድርጅቶች የምንዛሪ ተመን ለውጥ በመደረጉ ምክንያት በአንድ ጊዜ እጃቸው ላይ የሚገባው ገንዘብ ይበዛላቸዋል። ከ46 ብር ወደ 54 ብር በአንድ ጊዜ ከፍ ይልላቸዋል።"

Äthiopien Währung Birr
ምስል DW/Eshete Bekele Tekle

ቡና፤ሰሊጥ፤ቆዳ እና አበባ የመሳሰሉ የኢትዮጵያ ምርቶችን ከኢትዮጵያ ሸምተው ወደ አገራቸው የሚያስገቡ የውጭ ነጋዴዎችም የብር የምንዛሪ ተመን መዳከም መልካም ዜና የሚሆንላቸው ይመስላል። 
"ከውጭ አገር ሆነው የኢትዮጵያን ምርቶች የሚገዙ የበለጠ ርካሽ ይሆንላቸዋል። ለምሳሌ አንድ ኪሎ ቡና በሁለት ዶላር ይገዙ ነበረ። ኢትዮጵያ ከዶላር ከብር ያለውን ምጣኔ በ15% ከፍ በማድረጓ ምክንያት አውሮጳ ውስጥ ያለ አስመጪ አንድ ኪሎ ለመግዛት 46 ብር ይዞ ነበር ይመጣ የነበረው። አሁን በአንድ {ወደ ኢትዮጵያ ይዞት የሚሔደው ገንዘብ}ጊዜ 54 ብር ሆነለት። በፊት አንድ ኪሎ ይገዛበት የነበረውን ወደ ሁለት ኪሎ አካባቢ ቡና ከኢትዮጵያ ሊገዛ ነው ማለት ነው። ይኸ ምን ያሳያል ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልካቸው ነገሮች ዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ርካሽ ሆነው ታዩ፤ ከኢትዮጵያ የሚሸጠው ቡና ርካሽ ነው በሚል መንፈስ ብዙ ገዢዎችን ያገኛል።"

አቶ ብስራት እንደሚሉት የብርን የምንዛሪ ተመን ማዳከም የኢትዮጵያ መንግሥት ከአመት አመት እየከፋ የመጣውን ይኸንንው ክፍተት ሊያግዘው ይችላል። 

"ከ7-10 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ሁልጊዜ የሚታይ የንግድ ሚዛን መጓደል አለ። ምክንያቱ ምንድነው ኢትዮጵያ የውጪ ንግዷ እና ወደ አገር ውስጥ የምታስገባው ሁልጊዜ አይመጣጠንም። ኤክስፖርት ስናደርግ በየዓመቱ ወደ ሶስት አራት ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ከውጭ ምንዛሪ እናገኛለን። ነገር ግን ከውጭ የምናስገባው እስከ 14 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል። የብር የምዛሪ ተመን በመቀነሱ ምክንያት ዓለም አቀፍ ገበያ ላይ የሚቀርቡ የኢትዮጵያ እቃዎች ረከስ ብለው መታየታቸው የኢትዮጵያ መንግሥት የንግድ ጉድለቱን እንዲያጠብ ያደርገዋል። ምክንያቱም ወደ ውጭ የሚላከው እቃ እየበዛ ወደ አገር ውስጥ የሚገባው ደግሞ እንዲቀንስ ያደርጋል።" አቶ አብዱልመናን መሐመድ ግን ብሔራዊ ባንክ የወሰደው እርምጃ ለዘመናት ሲድሕ የኖረውን የውጭ ንግድ በዘላቂነት ያሻሽላል የሚል እምነት የላቸውም። 

"በተወሰነ ደረጃ የውጭ ንግዱን ሊያሻሽለው ይችላል። ግን በገቢ ንግድ ላይ የሚመጣው የዋጋ ግሽበት እነዚሁ እቃዎች ላይ ጭማሪ ስለሚፈጥር ተመልሶ ወደ ነበረበት ነው የሚሆነው። ብዙ ጊዜ እንደዚህ አይነት ሽክርክሪት ውጥ ነው የምንገባው። እኛ በጣም ብዙ እቃ እናስገባለን። አምና ወደ 17 ቢሊየን ዶላር {የሚያወጣ እቃ} አስገብተናል። እነዚህ እቃዎች ሁላ ላይ ነው ጭማሪ የሚመጣው። እኛ ደግሞ የምንልከው በጣም ትንሽ ነው። ሶስት ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ነው የምንልከው። ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ላይ የሚኖረው የዋጋ ጭማሪ ቀጥታ ግሽበት ይሆንና የምንልካቸው እቃዎች ላይ ጭማሪ ያመጣል።"

Äthiopien Schuhfabrik Fabrik Herstellung Schuhe
ምስል Getty Images/Z. Abubeker

የኤኮኖሚ ባለሙያዎቹ የብር የምንዛሪ ተመን መዳከም የውጭ ምርቶችን ለኢትዮጵያ ገበያ ለሚያስገቡ ነጋዴዎች እና ኩባንያዎች መልካም ዜና እንዳልሆነ ይስማማሉ። ዳፋው ግን በነጋዴዎቹ ላይ ብቻ ተወስኖ አይቀርም። ለውጡ በገበያው ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ በቀጥታ ወደ ሸማቹ ይሸጋገራል።

ኢትዮጵያ ለመጨረሻ ጊዜ ብር ከዶላር አንፃር የነበረውን ተመን ያዳከመችው ከሰባት አመታት በፊት ነበር። የብር የምንዛሪ ተመን 17 ከመቶ ሲዳከም በኢትዮጵያ ገበያ ላይ ወደ 40 በመቶ ገደማ የዋጋ ግሽበት መፍጠሩ አይዘነጋም። ዛሬ ሥራ ላይ የሚውለውን እርምጃ የዓለም የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክን የመሳሰሉ ተቋማት በበጎ አይን ሊመለከቱት እንደሚችሉ ባለሙያዎቹ ይስማማሉ። በቂ ነው ብለው ስለመቀበላቸው ግን አቶ ብሥራት ጥርጣሬ አላቸው። 

"እነ ዓለም ባንክ ወይንም የዓለም የገንዘብ ድርጅት አስልተው የሚያመጡትን ቁጥር ብናይ አሁን ብር ከዶላር አኳያ የደረሰበት የምንዛሪ ተመን በቂ አይደለም የሚል ክርክር ሊያመጡ ይችላሉ ብዬ አስባለሁ። 
ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ የ2010 ዓ.ም. በጀት ዓመት የኢትዮጵያ መንግሥት የትኩረት አቅጣጫዎችን በጠቆሙበት ንግግራቸው ወደ ውጪ ከሚላኩ የግብርና ምርቶች አራት ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት መታቀዱን ተናግረዋል። አቶ አብዱልመናን ግን ይኸ አዋጪ ለመሆኑ ጥርጣሬ አላቸው። ኢትዮጵያ ግብርና ልትተማመንበት የምትችለው ዘርፍ አይደለም የሚሉት አቶ አብዱልመናን የማምረቻው ዘርፍ ማነቆዎችን መፍታት ሁነኛው መፍትሔ እንደሆነ ይጠቁማሉ።

እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ