1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተሀድሶ ይደረግበት የሚባለው የዚምባብዌ የምርጫ ሕግ

ሰኞ፣ ሰኔ 4 2010

በዚምባብዌ የፊታችን ጎርጎሪዮሳዊው ሐምሌ 30፣ 2018 ዓም ፕሬዚደንታዊ እና ምክር ቤታዊ ምርጫ ይካሄዳል።  ምርጫ ሊደረግ ጥቂት ሳምንታት በቀረው ባሁኑ ጊዜ በሺዎች የሚቆጠሩ የዚምባብዌ ተቃዋሚዎች ህብረት ደጋፊዎች ሰሞኑን በመዲና ሀራሬ  አደባባይ በመውጣት ገለልተኛው የአስመራጭ ኮሚሽን የምርጫ ተሀድሶ እንዲያደረግ ጠይቀዋል።

https://p.dw.com/p/2zBBc
Simbabwe Opposition Nelson Chamisa
ምስል picture-alliance/AP/T. Mukwazhi

የዚምባብዌ ተቃዋሚ ህብረት ፕሬዚደንታዊ እጩ ኔልሰን ቻሚሳ

ምርጫው የቀድሞው ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ ባለፈው ህዳር ወር፣ 2017 ዓም በጦር ኃይሉ ግፊት ስልጣናቸውን ከለቀቁ በኋላ የሚካሄደው የመጀመሪያ ነው። የዴሞክራሲያዊ ለውጥ ንቅናቄ፣ በምህጻሩ፣ ኤምዲሲ የተባለው ዋነኛው የተቃዋሚ ፓርቲ የገዢውን ዛኑ ፒኤፍ ፓርቲ የአራት አሰርተ ዓመት ገደማ አመራር ለማብቃት ይቻል ዘንድ ከሌሎች ትናንሽ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ህብረት ፈጥሯል። ህብረቱ በቀጣዩ ሐምሌ ወር የሚደረገውን ምርጫ ካሸነፈ ኤኮኖሚውን በማሳደግ እና የህዝቡን ኑሮ ለማሻሻሉ ተግባር ትኩረት እንደሚሰጥ አስታውቋል።  

ከሮበርት ሙጋቤ ስልጣን መልቀቅ ጥቂት ቀናት ቀደም ሲል ከተደረገው የአደባባይ ተቃውሞ ወዲህ የተካሄደው የመጀመሪያው ግዙፍ ነው በተባለው የተቃውሞ ሰልፍ የተሳተፉት ዚምባብዌ ዜጎች በአጠቃላዩ ምርጫ ላይ ለሁሉም እኩል የመወዳደሪያ እድል እንዲፈጠር  እና እኩል የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን እንዲያገኙ ነው ለአስመራጩ ኮሚሽን እና ለሀገሪቱ መንግሥት ባቀረቡት ጽሁፍ በግልጽ አስቀምጠዋል።

Gründe für Migration Hunger Getreidesammler Simbabwe Flash-Galerie
ምስል AP

ተዓማኒ ምርጫ ለማካሄድ በምርጫው ሕግ ላይ የሚደረገው ለውጥ ወሳኝ መሆኑን ያመለከቱት ዜጎች ካቀረቧቸው ጥያቄዎች መካከል አስመራጩ ኮሚሽን  በቅድሚያ ገለልተኛ ወገን አዲሱ የመራጮች ስም ዝርዝር የያዘውን  ሰነድ እንዲመረምር  እንዲፈቅድ፣ የምርጫ ወረቀቶችን የሚያሳትመውን  ኩባንያ ስም እንዲያሳውቅ ህትመት ላይ ግልጽ አሰራር እንዲኖር እና የምርጫውን ውጤት እንዲያስጠብቅ የሚሉት ዋነኞቹ ናቸው።  ዶይቸ ቬለ ያነጋገራቸው አንዳንድ የተቃዋሚ ደጋፊዎች የተባሉት ተሀድሶ ለውጦች ከምርጫው በፊት ካልተደረጉ ምርጫው ሊጭበረበር ይችላል በሚል መስጋታቸውን ገልጸዋል።

«ገዢው ዛኑ ፒ ኤፍ ፓርቲ እንቅፋቶች እየደቀነብን እንደሆነ ይሰማናል። እና እያልን ያለነው የፈለገውን እንቅፋት ቢደቅንም እና የጠየቅነውን ለውጥ ባያደርግም፣ እኛ ፣ ያንን ሁሉ ችግር እናልፋለን ነው። »

«በዚምባብዌ ትክክለኛ እና ነፃ ምርጫ ማየት እንፈልጋለን። ለይስሙላ ብቻ የሚቆሙ የምርጫ ጣቢያዎችን አንፈልግም፣ ምክንያቱም፣  የማጭበርበር ተግባር ሊፈጸምባቸው ይችላል። ይህን ምርጫ እንደምናሸንፍ እናውቃለን።  እና ያንን ለማደናቀፍ ካሁኑ እያጭበረበሩ ነው። »
የዚምባብዌ ምርጫዎች ወቀሳ ሲቀርብባቸው ያሁኑ የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። በጎርጎሪዮሳዊው 2002 ዓም ምርጫ ከጥቂት ጊዜ በፊት የሞቱት የዴሞክራሲያዊ ለውጥ ንቅናቄ፣ ፣ በምህጻሩ፣ ኤምዲሲ የተባለው  መሪ ሞርጋን ቻንጊራይ አሸንፈው እንደነበር፣ ግን፣ የቀድሞው ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ ስልጣኑን ለማስረከብ ፈቃደኛ ሳይሆኑ እንደቀሩ ነው የሚነገረው። 

በተቃውሞው ሰልፍ ላይ ንግግር ያሰሙት በፕሬዚደንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ አንፃር የሚፎካከሩት  የተቃዋሚዎች ቡድኖች ህብረት ፕሬዚደንታዊ ምርጫ እጩ የ40 ዓመቱ ኔልሰን ቻሚሳ የዚምባብዌ ዜጎች ግልጽነት እንዲኖር እስከጠየቁ ድረስ የማጭበርበር ተግባር ሊፈጸም እንደማይችል አስታውቀዋል።

«ይህ ምርጫ አይጭበረበርም። ያ እንዳይሆን እኛ የሚያስፈልገውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነን። ጥሩው ነገር ፣ የዚምባብዌ ሕዝብ ድጋፍ አለን። ምርጫ አያስፈራንም።  ለውጥ እንዲደረግ የጠየቅነው ምናንጋግዋን ስለምንወዳቸው ነው። ራሳቸውን እንዲያታልሉ አንፈልግም። ራሳቸውን በማታለል ለድል እንዲበቁ አንፈልግም። ራሳቸውን በሚያታልሉበት ጊዜ ሁላችንንም ነው የሚያታልሉት። እና ነፃ እና ትክክለኛ ምርጫ በማካሄድ ዛኑ ፒኤፍን ለማዳን እንፈልጋለን። »የአስመራጩ ኮሚሽን  የምርጫ ቀን ከተወሰነ በኋላ በምርጫ ሕግ ላይ ተሀድሶ ማድረግ እንeደማይቻል በማስታወቅ ዘግይቶ ቀርቧል ያለውን የተቃዋሚዎች ቡድን ህብረት ጥያቄን ውድቅ አድርጓል። 

Simbabwe Unabhängigkeitsfeier Präsident Emmerson Mnangagwa
ምስል picture-alliance/AP Photo/T. Mukwazhi

ፕሬዚደንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ የሀገሪቱን ወታደሮች የሲቭል ልብስ አስለብሰው   በገጠሩ አካባቢ ለገዢው ፓርቲ የምርጫ ዘመቻ እያካሄዱ ነው በሚል  የተቃዋሚው ወገን ካለማስረጃ ወቀሳ በመሰንዘር፣ የጦር ኃይሉ በፖለቲካው እና በሲቭል ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ እንዳይገባ አሳስበዋል።  ዛኑ ፒኤፍ ይህን ሀሰት ሲል አስተባብሏል፣ የጦር ኃይሉም ቀደም ባለ ጊዜ ማስተባበያውን አሰምቷል።

የአካባቢ  እና የአፍሪቃ ህብረት መሪዎችም በምርጫው ሕግ ላይ የተሀድሶ ለውጥ እንዲደረግ ግፊት እንዲያሳርፉ ቻሚሳ ጥረት እንደሚያደርጉ እና በመዲናዋ የታየውን ዓይነት ተቃውሞ በመላ ዚምባብዌ እንደሚያካሂዱ አስታውቀዋል።  ፕሬዚደንት ምናንጋግዋ ከሁለት አሰርተ ዓመት በኋላ አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም አቀፍ ቡድኖች የዚምባብዌን ምርጫ በታዛቢነት እንዲከታተሉ ጋብዘዋል።  

አርያም ተክሌ

ተስፋለም ወልደየስ