1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ታሪክ

ንግሥተ-ሣባ ጥበብን ፍለጋ

ሐሙስ፣ ግንቦት 30 2010

ከሦስት ሺህ ዓመታት በፊት ንግሥተ-ሣባ ወደ እሥራኤል እየሩሳሌም ከተማ አቅንታ ንጉሥ ሰለሞንን እንደጎበኘችው ይነገራል። በሺህዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት የተጻፉ ሠነዶችም ይኽንኑ ያጠናክራሉ። የንግሥተ-ሣባ ታሪክ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ማንነትን ከመሠረቱት አንዱ መኾኑንም የታሪክ ተመራማሪዎች ይመሰክራሉ።

https://p.dw.com/p/2z62C
Königin von Sheba
ምስል Comic Republic

ጥበብን ፍለጋ ሺህ ኪሎ ሜትሮችን የተጓዘችው ንግሥት

ከሦስት ሺህ ዓመታት በፊት ንግሥተ-ሣባ ወደ እሥራኤል እየሩሳሌም ከተማ አቅንታ ንጉሥ ሰለሞንን እንደጎበኘችው ይነገራል። በሺህዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት የተጻፉ ሠነዶችም ይኽንኑ ያጠናክራሉ። እነዚህ ሠነዶች በተለያዩ መልኮች ተሠንደዋል። በመጽሐፍ ቅዱሥ እና በቁርአን ንግሥቲቱ የተለያዩ ስሞችን ይዛ ትገኛለች። የንግሥተ-ሣባ ታሪክ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ማንነትን ከመሠረቱት አንዱ መኾኑንም የታሪክ ተመራማሪዎች ይመሰክራሉ። የንግሥቲቱ ታሪክ፦ በዓለም ዙሪያ ለበርካቶች የውበት፣ የፍቅር፣ የሠላም ብሎም ዕውቀትን የመሻት ጉጉት ተምሳሌት ተደርጎ ይወሰዳል፤ ለኢትዮጵያውያን ግን የታሪክ የጀርባ አጥንት ነው። የንግሥተ-ሣባ ታሪክ በኢትዮጵያ ቢያንስ ለሰባት መቶ ዓመታት (ከ1270-1966 ዓ.ም) እንደ ሕገ-መንግሥት ተደርጎ ተወስዷል።  የታሪክ ተመራማሪዎችን በማነጋገር ማንተጋፍቶት ስለሺ ቀጣዩን ዘገባ አዘጋጅቷል። እነሆ የንግሥተ-ሣባ ታሪክ፦

በብዙ ክብርና ግርማ፣ በከፍተኛ ስንቅና ደስታ ለመሄድ ተዘጋጀች። ሰባት መቶ ዘጠና ሰባት የግመል ባዝራዎች ተጫኑ። ቁጥር የሌለው በቅሎና አህያም ተጫነ። ወርቅ፣ ውድ ማዕድናት እና ቅመማ-ቅመማት በገፍ ተሸከፈ። የ«ደቡቧ ንግሥት» ወደ እየሩሣሌም ረዥሙን ጉዞ ተያያዘች።   

Königin von Saba
ምስል Comic Republic

እነሆ ለሺህ ዓመታት ታላቅ አሻራውን የጣለው አሁንም ድረስ የበርካታ አድማጮችን ቀልብ የሚስበው አፈ-ታሪክ። ኃያሏ፣ ደም ግባቷ ያማረው ውቧ፣ ንግሥተ-ሣባ፤ ጥበቡ፦ ከግዛቱ ባሻገር ሩቅ በዝና የሚነገርለት ንጉሥ ሰለሞንን ለማግኘት ረዥሙን እና አደገኛውን የበረሃ ጉዞ ተያያዘች። ንግሥቲቱ ይኽን አስቸጋሪ ጉዞ ስለማድረጓ በበርካታ መዛግብት የሚገኙ ሠነዶች ያጠናክራሉ። ንግሥቲቱ የተለያዩ ስሞች አሏት። በመጽሐፍ ቅዱስ በብሉይ ኪዳን ንግሥተ-ሣባ ተብላለች። በአዲስ ኪዳን «የደቡብ ንግሥት» ተብላ ተጠቅሳለች። በቁርአን «ቢልቅስ» ትባላለች። በኢትዮጵያ ቢያንስ ሰባት መቶ ዓመታትን ባስቆጠረው ክብረ-ነገሥት መጽሐፍ ደግሞ «ማክዳ» መጠረያዋ ነው።    
የግእዙ ክብረ-ነገሥት ከሰባት መቶ ዓመት በፊት በዓጼ አምደ-ጺዮን ዘመነ መንግሥት እንደተተረጎመ ይነገራል።ከብሉይ ኪዳን፣ ከዓረብ መዛግብት እና ከኢትዮጵያ ጥንታዊ ጽሑፎች ተውጣጥቶ የተዋቀረው ክብረ-ነገሥት ንግሥቲቱ ንጉሥ ሰለሞን እንዴት እንደጎበኘች በዝርዝር ይተርካል።  

ንጉሥ ሰለሞን በቤተ-መንግሥቱ ታላቅ ድግስ ደግሶ ራት ጋበዛት። ለእርሱ ቅርብ ከኾነው ቤተ-መንግሥት ውስጥም ቤት ሰጣት። ዘወትርም ትሄድና ትመለስ፤ ጥበብንም ትሰማ፣ በልቧም ትጠብቀው ነበር። እሱም ወደ እሷ ይሄድ፣ የጠየቀችውንም ሁሉ ይነግራት ነበር። «እስከ ንጋቱ ድረስ ስለ ፍቅር እዚሁ ተጽናኚ» አላት። «እንዳትደፍረኝ በአምላክህ በእስራኤል አምላክ ማልልኝ» አለችው።  «እንዳልደፍርሽ እምልልሻለሁ። ነገር ግን አንቺም በቤቴ  ውስጥ ያለውን ሁሉ እንዳትደፍሪ ማይልኝ» አላት። «ንጉሡም በአንድ በኩል ወደ መኝታው ወጣ። ለእሷም ደግሞ በሌላው በኩል መኝታ አዘጋጀላት።» ንግሥቲቱም ጥቂት ተኛች።» እናም ነቃች። «በብልሃት የሚያስጠሙ ምግቦችን አስጋብዟት ነበርና በነቃች ጊዜ አፏ በጥማት ደረቀ።» ውኃውን ለመጠጣት መሃላዋን አፍርሳለች እና ከሰለሞን ጋር አደረች።  

...እናም ንግሥተ-ሣባ ለሰለሞን ወንድ ልጅ ወለደችለት። «በይነ-ልህለም» ስትል ስሙን ጠራችው። ዳዊት የሚሉትም አሉ። አንዳንዶች «ኢብን ኣልሃክም ብለው ይጠሩታል። እሱም ቀዳማዊ ምንሊክ የሚባለ ንጉሥ ነው። እንደ ክብረ-ነገሥት  ከኾነ ንግሥተ-ሣባ ከጠቢቡ ሰለሞን የወለደችው ቀዳማዊ ምንሊክ ዕድሜው 12 ሲሞላ ስለ አባቱ መጠየቅ ጀምሯል። ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስም ዐሥርቱ ትእዛዛት የተቀረጸበት ታቦተ-ጽዮን አብሮት በመምጣቱ በወቅቱ በሀገሪቱ የአይሁድ እምነት ተዋውቋል። የቀዳማዊ ምንሊክ በኢትዮጵያ መንገሥ በሀገሪቱ ለሺህ ዓመታት የዘለቀው ሰለሞናዊ ሥርወ-መንግሥት ጅማሬ ኾኗል። ያም በመኾኑ ንግሥተ ሣባ በኢትዮጵያ ታሪክ አንድምታው ልዩ ሥፍራ እንዳለው በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ተመራማሪው ዶ/ር አየለ በከሪ ያብራራሉ።    

ንግሥቲቱን ከኢትዮጵያ ውጪ የእኛ ናት የሚሉም አሉ። ሸባ የሚለው ስያሜ አሁን የመን ተብሎ በሚጠራው ሀገር የሳባ የዓረብ ንጉሣዊ ግዛት መጠሪያ ነው ሲሉ የጻፉ አሉ። ለኢትዮጵያውያን ንግሥተ-ሣባ ከእነ ስሟ ማክዳ ትባላለች። የኢትዮጵያ ስለመኾኗም የታሪክ ተመራማሪዎች የአክሱም ሥልጣኔ ቅሪቶችን፣ እንዲሁም በአክሱም ጺዮን ይገኛል የሚባለውን ታቦተ ጺዮን እንደ ማስረጃ ያቀርባሉ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የየግእዝ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ተመራማሪ አቶ ሥርግው ገላው ንግሥተ-ሣባ የእና ናት ሲሉ የሚከራከሩ ቢኖርም በኢትዮጵያውያን የሚቀርበውን ማስረጃ እንዲህ ይተነትናሉ።     

ክርክሩ እንዳለ እንዳለ ኾኖ አንድ ነገር ግን በእርግጠንነት መናገር ይቻላል። የንግሥተ-ሣባ ታሪክ በዓለም ዙሪያ የበርካቶችን ቀልብ ስቧል፤ የብዙዎችን ልብ ማርኳል። 

ንጉሠ ነገሥት ዓጼ ኃይለ ሥላሴ በ1966ቱ አብዮት ከሥልጣናቸው ሲወገዱ ግን ለሦስት ሺህ ዘመናት የዘለቀው ሰለሞናዊ ሥርወ-መንግሥት አስተዳደር በኢትዮጵያ ማብቂቃው ኾነ። እንዲያም ቢኾን ግን የንግሥተ-ሣባ አለያም የማክዳ ታሪክ ዛሬም ድረስ ሕያው ነው። 

Königin von Saba
ምስል Comic Republic

ይኽ ዘገባ ተጽፎ የተዘጋጀው በማንተጋፍቶት ስለሺ ሲኾን፤ አፍሪቃዊ ሥረ መሠረት በሚል ከጌርዳ ሔንክል ተቋም ጋር በመተባበር የሚቀርብ ልዩ ዝግጅት አካል ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ