1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አምስተኛው ዓለም አቀፍ የካካዎ ጉባኤ የደሐ ገበሬዎችን ሕይወት ይቀይር ይሆን?

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 12 2016

ለቸኮሌት ምርት ዋነኛ ግብአት የሆነው የካካዎ ምርት ባለፉት ጥቂት ወራት ዋጋው በዓለም ዙሪያ በሦስት እጥፍ ጨምሯል ። ገበሬዎች ከፍተኛ ክፍያ እንዲፈጸምላቸውን እና ከድህነት እንዲወጡ ይሻሉ ። ሲታይ ቀላል የሚመስለው ጉዳይ ግን የዚያን ያህል ቀላል አይመስልም ።

https://p.dw.com/p/4ezMy
Osterhase aus Schokolade | Confiserie Felicitas GmbH
ምስል Patrick Pleul/dpa/picture alliance

በደሐ ሃገራት ገበሬዎች የድሕነት ጫንቃ መረማመድ የለባቸው

ለቸኮሌት ምርት ዋነኛ ግብአት የሆነው የካካዎ ምርት ባለፉት ጥቂት ወራት ዋጋው በዓለም ዙሪያ በሦስት እጥፍ ጨምሯል ። ገበሬዎች ከፍተኛ ክፍያ እንዲፈጸምላቸውን እና ከድህነት እንዲወጡ ይሻሉ ። ሲታይ ቀላል የሚመስለው ጉዳይ ግን የዚያን ያህል ቀላል አይመስልም ።

የቅርብ ጊዜ ዋጋ እንደሚያመለክተው ከሆነ አንድ ሜትሪክ ቶን ካካዎ 10,000 ዶላር አውጥቷል ። ያ ማለት በተመሳሳይ መጠን ከሚገመት የመዳብ ዋጋ በ1,300 ዶላር ግድም ከፍ ያለ ነው ።  ከአንድ ዓመት በፊት አንድ ሜትሪክ ቶን ካካዎ ከዘንድሮው እጅግ ዝቃ ባለ ከ3,000 ዶላር በታች ይሸጥ እንደነበር የገበያ ጥናቶች ያመለክታሉ ።

ነገ የሚጀምረው አምስተኛው ዓለም አቀፍ የካካዎ ጉባኤ የገበሬዎቹ መሠረታዊ ጥያቄን በዋናነት ይመለከታል ተብሎ ይጠበቃል ። ጉባኤው ከነገ እሁድ ሚያዝያ 13 ቀን፣ እስከ ረቡዕ ሚያዝያ 16 ቀን 2016 ዓም ቤልጂየም ብራስልስ ከተማ ውስጥ ይከናወናል ። የዘንድሮ ጉባኤ ዋነኛ ትኩረቱ፦ «ለዘላቂ የካካዎ ምርት የበለጠ መክፈል» የሚል ነው ። ከባቢ አየርን በማይጎዳ መልኩ ካካዎ ለሚያመርቱ ሃገራት ከፍተኛ ክፍያ መፈጸም ስለሚቻልበት መንገድም በዋናነት ያጤናል ተብሏል ጉባኤው ።

እያበበ የመጣው ዓለም አቀፍ የካካዎ ገበያ በተቃራኒው አስቸጋሪ ጉዳዮችንም ከጀርባው ሸሽጓል ። በቸኮሌት ምርት ዳጎስ ያለ ገቢ የሚያገኙ ሃብታም ሃገራት በደሐ ሃገራት ገበሬዎች የድሕነት ጫንቃ መረማመድ የለባቸው የሚለው ድምፅም እያስተጋባ ነው ።

ሐብታም ሃገራት ገቢያቸው በእጥፍ ሲጨምር የካካዎ አምራች ገበሬዎች ግን ከዓመት ዓመት የዕለት ሕይወትን መግፋት ተስኗቸው ይንገታገታሉ
ሐብታም ሃገራት ገቢያቸው በእጥፍ ሲጨምር የካካዎ አምራች ገበሬዎች ግን ከዓመት ዓመት የዕለት ሕይወትን መግፋት ተስኗቸው ይንገታገታሉምስል Godong/picture alliance

ሐብታም ሃገራት ገቢያቸው በእጥፍ ሲጨምር የካካዎ አምራች ገበሬዎች ግን ከዓመት ዓመት የዕለት ሕይወትን መግፋት ተስኗቸው ይንገታገታሉ ። ከዓለማችን የካካዎ ምርት ሁለት ሦስተኛው መገኛ የሆኑት የምዕራብ አፍሪቃ  ሁለት ሃገራት ናቸው ። አይቮሪ ኮስት እና ጋና ። ለእነዚህ ድሐ ገበሬዎች ከፍተኛ ክፍያ መፈጸም የህጻናት ጉልበት ብዝበዛን ሊያስቀር ይችላልም ይላሉ ተንታኞች ። የምእራቡ ዓለም ነጋዴዎች ደግሞ የድሐገ በሬዎችን ጥቅም ማስጠበቅ እና የጉልበት ብዝበዛን ማስቀረት የዘላቂ ልማት ዋነና ግብ ነው  ይላሉ ። የህጻናት የጉልበት ብዝበዛውም፤ የካካዎ አምራች ገበሬዎች የድህነት ኑሮም ከንግግር ባሻገር ጠብ ያለለት ነገር የለም ። 

አራተኛው ዓለም አቀፍ የካካዎ ጉባኤ በዓለም አቀፍ የካካዎ ድርጅት (ICCO) አዘጋጅነት እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2018 ጀርመን ቤርሊን ከተማ ውስጥ ሲከናወን ከመላው ዓለም 65 ሃገራት የተውጣጡ በካካዎ ምርት ላይ የሚሳተፉ ከ1,500 በላይ ታዳሚያንን አሰባስቦ ነበር ። ምናልባት የዘንድሮው 5ተኛ ጉባኤ እንደተባለው የአፍሪቃውያኑን ሕጻናት የጉልበት ብዝበዛ እና የድሀ ገበሬዎች ሕይወት ይቀይር ይሆን? ወደፊት የሚታይ ነው ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሠ