1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለአዲስ መንጃ ፍቃድ አውጪዎች የፀደቀው ሕግ

ዓርብ፣ ጥር 25 2010

ኢትዮጵያ በርካታ የመኪና አደጋ ከሚደርሱባቸው ሃገራት ተርታ ትሰለፋለች። ይህንን ችግር ያሻሽላል በሚል የኢትዮጵያ ትራንስፖርት ባለስልጣን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበው ረቂቅ ሀሳብ ከብዙ ክርክር በኋላ ባለፈው ሳምንት ጸድቋል።

https://p.dw.com/p/2rqFY
Äthiopien Addis Ababa Bushaltestelle
ምስል DW/Eshete Bekele Tekle

ጥር 15 ቀን 2010 ዓም የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያፀደቀው ረቂቅ አዋጅ በተለይ ለንግድ የተሰማሩ ተሽከርካሪዎችን መንዳት የሚፈልጉ ወጣቶች ይመለከታል። እናም 10ኛ ክፍልን ማጠናቀቅ እንደ መስፈርት መቀመጡ አንዳንዶችን ሲያስደስት ሌሎቹን አስቆጥቷል። ጀርመን ሀገር ነዋሪ የሆነው ወልደፃዲቅ አዲስ የፀደቀው ሕግ ኢትዮጵያ ውስጥ የመኪና አደጋ የሚያስከትለውን ሞት ይቀንሳል ብሎ አያምንም።ሳውዲ አረቢያ የሚኖረው ኢብራሂምም ቢሆን ይህንኑ ሀሳብ የሚጋራ ነው። እሱ እንደሚለው አዲሱ ሕግ ጭራሽ ወጣቱ ሠርቶ እንዳይበላ የሚያደርግ ነው።

የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫው አዋጅ በኢትዮጵያ ትራንስፖርት ባለስልጣን አማካኝነት በ2009 ዓም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበ ሲሆን ባለፈው ማክሰኞ ፀድቋል። ረቂቁን ያቀረበው የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ዋና ዳሬክተር አቶ ካሣሁን ኃይለ ማሪያም « ህዝብን የሚያጓጉዝ ትራንስፖርት ላይ የተሰማራ አሽከርካሪ የትምህርት ደረጃን መነሻ 10ኛ ክፍል ያደርጋል።» ይላሉ።  

ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት 10 ዓመታት መንጃ ፍቃዱን ለማውጣት እንደመስፈርት ተቀምጦ የነበረው 8ኛ ክፍልን ላጠናቀቁ ነበር። ይህ ግን አቶ ካሣሁን እንደሚሉት በተለያዩ ምክንያቶች ወደ 10ኛ ክፍል ከፍ እንዲል ተደርጓል። ይህም በጥናት ላይ ተመርኩዞ እንደሆነ የባለስልጣኑ ዋና ዳሬክተር አቶ ካሳሁን ይናገራሉ።  የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫው አዋጅ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከመድረሱ በፊት ባለስልጣኑ ከአሽከርካሪዎች ማህበራት፣ ማሰልጠኛ አካላት እና ኅብረተሰቡ ጋር ተወያይቷል። ከባለ ድርሻ አካላቱ አንዱ የነበሩት የአስኮ ጥላ ታክሲ ማሕበር ሊቀ መንበር አቶ አስማማው ናቸው። ማሕበራቸው አዲስ የፀደቀውን ሕግ ያወድሳል።

Äthiopien Addis Ababa Bushaltestelle
ምስል DW/Eshete Bekele Tekle

ኢትዮጵያ ውስጥ በብዛት የታክሲ አሽከርካሪዎች ወጣቶች ናቸው። አልፎ አልፎም ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደዚሁ ሙያ የገቡ እና የ10ኛ ክፍልን ያላጠናቀቁ ይገኙበታል። ታድያ ይህ ሕግ ተግባራዊ ሲሆን የነዚህ አሽከርካሪዎች እጣ ፋንታ ምን ይሆናል? የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ዋና ዳሬክተር አቶ ካሣሁን እነሱን አይነካም ይላሉ። « በቀጣይ ወደ ስራ የሚገቡትን ነው እንጂ የሚመለከተው ዛሬ በስራ ላይ ያሉ እና ይህንን አገልግሎት እየሰጡ ያሉት ባሉበት ነው የሚቀጥሉት።»  

ቀደም ሲል ታክሲ በመንዳት ይተዳደር የነበረው ፍቃዱም ቢሆን አዲሱን ሕግ ይደግፋል። ያኔ መንጃ ፈቃድ ሲያወጣ የ8ኛ ክፍል ተማሪ ነበር። አሸብር ደግሞ አሁንም ታክሲ ነጂ ነው። አሁን የፀደቀው ሕግ በቀጥታ አይመለከተውም። ይሁንና እሱ መንጃ ፈቃድ ሲያወጣ የ7ኛ ክፍል ተማሪ ነበር። መንጃ ፍቃድ ለማውጣት 10ኛ ክፍል የጨረሰ መባሉ በእድሜ እና በእውቀት ደረጃ እየበሰሉ ለመሄድ  ወሳኝ ነው ይላል።

የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫው አዋጅ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቢፀድቅም በ 67 ተወካዮች ዘንድ ተቃውሞ ሲገጥመው 30 ደግሞ ድምፀ  ተአቅቦ ገጥሞታል። ይህም የአሽከርካሪውን ዕድሜ ወይም የትምህርት ደረጃ በሚመለከት ሳይሆን በሌላ ምክንያት ነው። ይህም የክልል እና የፌደራል ስልጣንን በሚመለከት ነው። በዚህም መሠረት አዲስ የሚሰጠው መንጃ ፈቃድ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሦስት ወር ገደማ በኋላ ተግባራዊ ይሆናል።

ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሰ