1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ በውጭ አገር የሥራ ስምሪት እገዳ ማንሳቷ

Merga Yonas Bula
ረቡዕ፣ ጥር 23 2010

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ጽሕፈት ቤት ለአራት ዓመታት የዉጭ አገር የስራ ስምሪት ላይ ጥሎ የነበረዉን እገዳ  እንዳነሳ ለሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል። አገዳዉ ሕገወጥ ጉዞን አባብሷል የሚል ትችት ሲቀርብበት ቆይቷል።

https://p.dw.com/p/2rrkh
Saudi Arabien Arbeiter kehren nach Äthiopien zurück
ምስል DW/S. Shiberu

Ethiopia lift ban on foreign employment - MP3-Stereo

 

አሁን መነሳቱ ለሠራተኞችም ሆነ ለሀገሪቱ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለዉ በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የኮሙኒኬሼን ጉዳዮች ክፍል ሃላፊ አቶ ባሳዝን ደርቤ ለዶቼቬለ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ መንግስት በወሰነው መሰረት ለአራት ዓመት የዉጭ አገር የስራ ስምሪት ላይ ጥሎ የነበረዉ እገዳ የተነሳው ከትንንት አንስቶ ነው። ስለ ውሳኔውም ነገ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥ ለዶቼቬለ የተናገሩት በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የኮሙኒኬሼን ጉዳዮች ሃላፊ አቶ ባሳዝን ደርቤ እገዳው ለዚህን ያህል ጊዜ ለምን እንደተጣለና አሁን ለምን እንደተነሳ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ለዜጎቹ የዉጭ አገር የስራ ስምሪት የከለከለው ዲፕሎማሲያዊ  ዝግጅቶችን ለማድረግ እናና ከቀጣሪ አገሮች ጋር የሠራተኛ ስምምነት ለመፈራረም መሆኑንም አቶ ባሳዝን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ከመካከለኛ ምስራቅ አገራት ጋር ማለትም ከዮርዳኖስ፣ ከኩዌት፣ ከሊባኖስ፣ ከዩናይትድ አረብ ኤምሬቶች ከባህሬን እና ከሳዑዲ አረቢያ ጋር የሁለትዮሽ የሥራ ስምሪት ቅጥር ስምምነትን ኢየፈጸመች እንደምተገኝ የሀገር ውስጥ ዘገባዎች ያመለክታሉ።

Äthiopien Addis Abeba Rückkehrer
ምስል DW/Y. Gebireegziabhe

እገዳው ብዙ ሲያነጋግር ቆይቷል። የተለያዩ ትችቶችም ሲቀርቡበት ነበር። እርምጃው ለሕገወጥ ጉዞ መንገድ ከፍቶ ነበር ሲሉ የሚከራከሩ ጥቂት አልነበሩም። ሕጋዊ ፍቃድ ሳይኖራቸዉ በሳዑድ አረብያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የውጭ ዜጎች በቅርቡ አገሩን ለቀው እንዲወጡ መደረጉ ይታወሳል። ወደ አገራቸዉ የተመለሱትን መንግስት እንዴት እየተቀበላቸው እንደሆነ አቶ ባሳዝን ደርቤ ይናገራሉ።  

አቶ ባሳዝን ይህን ቢሉም በተለያዩ ጊዜያት ዶቼቬለ ያነጋገራቸው ተመላሾች ወደ ሀገራቸው ሳይገቡ የተሰጣቸው ተስፋ እና ከተመለሱ በኋላ የገጠማቸው ፈጽሞ የሚገናኝ እንዳልሆነ ይገልጻሉ። ከሁለት ዓመት በፊት የፀደቀዉ የኢትዮጵያ የውጭ አገር የሥራ ስምሪት አዋጅ ቁጥር 923 ለሥራ ወደ ውጭ አገር የሚሄድ ማንኛውም ሠራተኛ ቢያንስ የስምንተኛ ክፍል ትምህርት ያጠናቀቀ እና  በሚቀጠርበት የሥራ መስክ አግባብ ካለው የምዘና ማዕከል የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ማስረጃ የያዘ፣ መሆን እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ መንግስት ለሥራ ወደ ውጭ አገር ለመሄድ ፍላጎት ላላቸው ዜጎች ስለተቀባይ አገር ሁኔታ፣ በሚሰማሩበት የሥራ መስክ ሊኖራቸው ስለሚገባ ክህሎት፣ ስለመብታቸውና ኃላፊነታቸው የቅድመ-ስምሪትና የቅድመ-ጉዞ ግንዛቤ ማሳደጊያ ሥልጠና በመደበኛነት እንደምሰጥም አዋጁ ይጠቅሳል።

መርጋ ዮናስ

ሂሩት መለሰ