1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢንተርኔት እየተመኘ ያላገኘው ትውልድ

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 13 2010

በኢትዮጵያ ብቸኛው የኢንተርኔት እና ስልክ አገልግሎት አቅራቢ ህዝቡን በሚፈልገው መልኩ ተጠቃሚ ሊያደርግ አልቻለም። በአንድ በኩል የዋጋው ውድነት ሲሆን ከዛ የበለጠው ደግሞ ቢፈልግም ጨርሶ አገልግሎቱን አለማግኘቱ ነው።  

https://p.dw.com/p/2poqo
Äthiopien Addis Abeba Universität Kommunikation Internetsperre
ምስል DW/J. Jeffrey

የኢንተርኔት አገልግሎት እጦት

IT Web የተባለው የንግድ እና ቴክኖሎጂ መረጃ አቅራቢ ባለፈው ወር ባወጣው ዘገባ መሰረት ኢትዮጵያ ውስጥ ብቸኛው የኢንተርኔት እና ስልክ አገልግሎት አቅራቢ ኢትዮ ቴሌኮም 57,34 ሚሊዮን የሞባይል ስልክ ቁጥር ተጠቃሚዎች አሉት። ይህም እስከአሁን ከአፍሪቃ ቀዳሚ የነበረውን የናይጄሪያውን MTN ድርጅት እንዲበልጥ አድርጎታል። የኢትዮ ቴሌኮም በአሁኑ ወቅት ለ 62 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች አገልግሎት የመስጠት አቅም እንዳለውም ዘገባው አክሎ ገልጿል። በተግባር እንደሚታየው ከሆነ ግን ይህ አጠያያቂ ነው።
የስልክ ግንኙነቱ ከኢንተርኔት አገልግሎቱ ጋር ጎን ለጎን ሲታይ ግን የተሻለ ነው። እንደ ኢንተርኔት ወርልድ ስቴትስ መረጃ ከሆነ እስከ ባለፈው ሰኔ ወር ድረስ ከኢትዮጵያ ህዝብ መካከል የኢንተርኔት ተጠቃሚው ቁጥር 16 ሚሊዮን ወይም 15,4 ከመቶ ያህሉ  ነው።  ከመቶ ሚሊዮን ህዝብ በላይ ባላት ኢትዮጵያ የፌስቡክ ተጠቃሚው 4,5 ሚሊዮኑ ብቻ እንደሆነም መረጃው ይጠቁማል። ይህን ያህል ብዙ ያልሆነው የኢትዮጵያ የኢንተርኔት ተጠቃሚ ግን ብዙ ይገጥሙታል። ለዚህም ኢትዮ ቴሌኮም ኢትዮጵያ ውስጥ ተፎካካሪ የሌለው ብቸኛ ስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት አቅራቢ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚም መንግሥት በተለያዩ ምክንያቶች አገልግሎቱ እንዲቋረጥ ማድረጉ እንደ ምክንያት ይጠቀሳል።  የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡ በይፋ ባልተገለጸበት በአሁኑ ሰዓት እንኳን በርካታ የአገልግሎቱ ፈላጊዎች ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻሉ ይናገራሉ። ከነዚህ አንዱ በአዲስ አበባ የሚኖረው ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገው ወጣት ነው። « በተወሰነ ቦታዎችን እና ጎዜዎችን እየመረጠ ስለሚከሰት ታስቦበት የሚደረግ ይመስላል። ቴሌኮም በመንግሥት እጅ ነው። ተወዳዳሪም የለውም።» ይላል
ደቡብ ወሎ ውስጥ የሚኖረው ታዲዮስም በአካባቢው የኢንተርኔት አገልግሎት ችግር እንዳለ ገልጾልናል። በአሁኑ ወቅት አንዳንድ አፕሊኬሽኖች የማይሰሩት ወይም የታገዱበት ምክንያት በኔቶርኩ ችግር ነው ይላል። « አንዳንድ አፕሊኪሽኖችን ኔቶርኩ ከሚገባው በላይ አግዷቸዋል። ችግሩ የአፕሊኬሽኖቹ አይደለም»ታዲዮስ «የተጋነነ እውቀቱ ባይኖረኝም የ IT ተማሪ ስለነበርኩ እና አንዳንድ አማራጮችን ስለማውቋ ኢንተርኔት በታገደበት ወቅትም ከቀሪው አለም ጋር ለመገናኘት ችያለሁ» ይላል። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የኢንተርኔት ተጠቃሚም በሁለት ክፍል ይመድበዋል። በተማረ እና ባልተማረ። የኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎት በሚቋረጥበት ጊዜ ታዲዮስ እና ሌሎች አማራጩን ብሎም በሌላ ዘዴ መጠቀሙን ያወቁበት ሰዎች ኢንተርኔት ማግኘት ቢችሉም፤ በዚህ ወቅት የሚከፍሉት ገንዘብ ከመደበኛው አገልግሎት ከፍ ያለ ነው። ይህም አገልግሎቱን መጠቀም በሚፈልጉበት መጠን እንዳይጠቀሙ አድርጓቸዋል። 
የ26 ዓመቱ አብደላ እንደ ታዲዮስ ደቡብ ወሎ ውስጥ ነው የሚኖረው። ከከተማ ውጪ ስለሚኖር የሞባይል ስልኩ ኢንተርኔት ለመጠቀም ብቸኛ አማራጩ ነው። በአካባቢው ኢንተርኔት ካፌም ይሁን ነፃ የWIFI አገልግሎት የሚያገኝበት መንገድ የለም። አብደላ ኢንተርኔት መጠቀም ከጀመረ አምትስ ዓመት ሆነው። የኔቶርክ ችግሩ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ብሶበታል ይላል። መቆራረጡ አሰልቺ ባይሆንበት ኖሮ የተጠየቀውን ክፍያ ለመክፈል ዝግጁ ነው። 
ጀርመን ውስጥ በርካታ የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት ድርጅቶች ይገኛሉ። በዚህም ምክንያት ከፍተኛ ፉክክር አለ። ይህም ተጠቃሚው ጥሩ አገልግሎት እና ዋጋ እንዲያገኝ ወይም እንዲያማርጥ ረድቶታል። አገር ውስጥ በማንኛውም አገልግሎት አቅራቢ ወይም ፕሮቫይደር ላይ ደውሎ፣ ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት 24 ሰዓት አግኝቶ በወር የሚከፍለው  በብር 500 ወይም  ከዚያም በታች ሊሆን ይችላል።  ስሙን መግለጽ ያልፈለገው እና ያነጋገርነው ሌላው ወጣት በቅሬታ እንደገለፀልን የፈለገውን ያህል እንኳን ሳይጠቀም፤ ቢያንስ 50 እና 60 ብር በሳምንት ይከፍላል። አይመን አዲስ አበባ ውስጥ የሚኖር የ 23 ዓመት ወጣት ነው። ራሱን ብዙም የኢንተርኔት ተጠቃሚ አድርጎ አይመለከትም። ይሁንና እሱም ከ 10-15 ብር በቀን ለኢንተርኔት እንደሚከፍል ገልፆልናል። ህይወቱን ያለ ኢንተርኔትም ማሰብ ይከብደዋል።
አንዳንዶች ለኢንተርኔት አገልግሎቱ መክፈል እየፈለጉ ሌሎች ደግሞ ዋጋው ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ ምክንያት አጠቃቀማቸውን ለመቀነስ ወይም ጨርሶ ለማቆም ተገደዋል።  ይህ ችግር ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከሰሀራ በስተ ደቡብ ባሉ ሀገራትም በቶሎ መፍትሔ የሚያገኝ አይመስልም። እኢአ እስከ 2020 ዓም ድረስ የኢንተርኔት ተጠቃሚው ቁጥር 40 ከመቶ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ የ IT Web መረጃ ይጠቁማል።  77 ከመቶው ከ 35 ዓመት በታች በሆነባቸው ከሰሀራ በስተ ደቡብ ያሉ አፍሪቃውያት ሀገራት ወጣቶች የኢንተርኔት ፍላጎታቸው እስኪሟላ ድረስ ብዙ መጠበቅ ግድ ይላቸዋል።
ልደት አበበ 
አርያም ተክሌ

Symbolbild Virtual Private Network VPN
Symbolbild Cyber Sicherheit
ምስል Getty Images/L. Neal