1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኤርትራውያን ስደተኞች ቤተሰቦች ፈተና

ማክሰኞ፣ ግንቦት 7 2010

«ኤርትራውያን ስደተኞች ቤተሰቦቻቸው ጀርመን እንዲመጡላቸው  ባለፈው ዓመት ካስገቧቸው ማመልከቻዎች ውስጥ  808 ቱ ታይተዋል። ሆኖም ከመካከላቸው ይሁንታ ያገኙት 394ቱ ወይም ደግሞ 48.8 በመቶው ብቻ ናቸው » የጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት

https://p.dw.com/p/2xlvU
Deutschland Berufsorientierungs- und Ausbildungsbörse (iBOB) in Cottbus
ምስል Imago/Rainer Weisflog

የኤርትራውያን ስደተኞች ቤተሰቦች ፈተና

ጀርመን ባለፉት ዓመታት በርካታ ኤርትራውያን ስደተኞችን ተቀብላለች ። እነዚህ ስደተኞች የቤተሰብ አባላቶቻቸውን ወደ ጀርመን የማምጣት መብት ቢኖራቸውም እንዲህ በቀላሉ ይሳካላቸዋል ማለት አይደለም። 5 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ እንዳላት የሚነገርላት ኤርትራ ብዙ ህዝብ ከሚሰደድባቸው የአፍሪቃ ሀገራት አንዷ ናት። በሀገራቸው የወደፊት እጣ ተስፋ የቆረጡ ፣አምባገነን አገዛዝን፣ ብሔራዊ ውትድርናን እና ድህነትን በመሸሽ በርካታ ወጣት ኤርትራውያን ህይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው ይሰደዳሉ። በሺህዎች የሚቆጠር ዮሮ እና ዶላር ለደላሎች ከፍለው ሰጥተው የሱዳን እና የሊቢያን በረሀ አቋርጠው በሜዴትራንያን ባህር በኩል አውሮጳ ከሚገቡት የአፍሪቃ ስደተኖች የኤርትራውያን ቁጥር ያመዝናል። ከመካከላቸው በጉዞ ላይ ለተለያዩ አደጋዎች የሚጋለጡ ያሰቡት ሳይደርሱ የበረሀና የውሐ ሲሳይ ሆነው የሚቀሩም ጥቂት የሚባሉ አይደሉም። እድል ቀንቷቸው የተለያዩ የአውሮጳ ሀገራትን ተሻግረው ጀርመን መግባት ከቻሉት ኤርትራውያን ስደተኞች አብዛኛዎቹ ተገን የማግኘት እድላቸው ከፍተኛ እንደሆነ ነው የሚነገረው። ከጎርጎሮሳዊው 2015 እስከ ጎርጎሮሳዊው 2017 ዓም  ጀርመን ከ35 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ኤርትራውያን ስደተኞች የመኖሪያ ፈቃድ ሰጥታለች። በአንዳንድ የጀርመን ከተሞችም ኤርትራውያን ስደተኞች እና ተገን ጠያቂዎች ከሥራ ፈላጊዎች ውስጥ አመዛኙን ቁጥር ይይዛሉ። እነዚህ ስደተኞች ቤተሰቦቻቸውን ወደ ጀርመን የማምጣት መብት ቢኖራቸውም ሂደቱ ግን ቀላል እንዳልሆነ ይናገራሉ። ከምክንያቶቹ ውስጥ አንዱ እና ዋነኛው ኤርትራ የሚገኘው የጀርመን ኤምባሲ የቪዛ ክፍል አለመኖሩ ነው። ከዚህ በተጨማሪም በጎረቤት አገራት የጀርመን ኤምባሲዎች ያለው ቢሮክራሲም የስደተኞች ቤተሰቦች ወደ ጀርመን የሚመጡበትን ሂደት በእጅጉ በማጓተት ይተቻል። ስለ ሂደቱ ጀርመን ለሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች መጠይቅ ያደረገው የጀርመኑ ተቃዋሚው የግራዎቹ ፓርቲ አሉ የተባሉትን ችግሮች ጠቅሶ ከሁለት ወር በፊት መልስ እንዲሰጥበት ጥያቄዎቹን ለጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አቅርቧል። ኡላ የልፕከ የግራዎቹ ፓርቲ የምክር ቤት አባል ናቸው። ርሳቸው እንዳሉት የኤርትራውያን ስደተኞችን ቤተሰቦችን ወደ ጀርመን የሚመጡበትን ሂደት ከሚያጓትቱት አሠራሮች ውስጥ በኤምባሲዎች ያለው ቢሮክራሲ አንዱ ነው። ከነዚህ ውስጥ የተራዘመ ቀጠሮ መስጠት ይገኝበታል።

Deutschland Migration junge Männer aus Eritrea
ምስል picture-alliance/dpa/M. Schutt

«ከኤርትራ የሚመጡ እና በጄኔቫው ስምምነት መሠረት እውቅና የተሰጣቸው ስደተኞች ቤተሰቦቻቸውን የማምጣት መብት አላቸው። ሆኖም በኤምባሲዎች ቀጠሮ ለማግኘት ረዥም ጊዜ መውሰዱና ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዳይቀላቀሉ ማድረጉ በጣም አናዶኛል። ወደ አሳዛኝ ሁኔታም እያመራ ነው። »  

ይህ ቪዛ ጠያቂዎች በጎረቤት አገራት የጀርመን ኤምባሲዎች ይገጥማቸዋል የተባለ አንዱ ችግር ነው ።ከዚያ በፊት ግን ጀርመን የመኖሪያ ፈቃድ ያገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች ቤተሰቦች ኤርትራ ውስጥ የቪዛ አገልግሎት ስለማይሰጥ ጀርመን መምጣት የሚያስችላቸው ቪዛ ለማግኘት ወደ ጎረቤት አገራት መሄድ ይኖርባቸዋል። የጀርመን ኤምባሲዎች የቪዛ አገልግሎት ወደ ሚሰጡባቸው ወደ ኢትዮጵያ ሱዳን  አለያም ኬንያ። ወደነዚህ ሀገራት መጓዙ ደግሞ ኤርትራውያን ስደተኞች እንደሚሉት ቤተሰቦችን ለተለያዩ አደጋዎች የሚያጋልጥ ከመሆኑም በላይ በህይወት መድረስ መቻላቸውንም እርግጠኛ መሆን አይቻልም። በዚህ የተነሳም አንዳንድ ኤርትራውያን ስደተኞች ተስፋ በመቁረጥ ቤተሰቦቻቸውን የማምጣት እቅዳቸውን እስከመሰረዝ ደርሰዋል። ይህን ከሚሉት አንዱ ዶቼቬለ ያነጋገረው ጀርመን የተቀበለችው እና ለቤተሰቡ ደህንነት ሲል ማንነቱ እንዲገለጽም ሆነ የሚናገረው እንዲቀረጽ ያልፈቀደ ተሞክሮውን ግን ያጋራን ስደተኛ ነው። ይኽው ስደተኛ እንደሚለው ጀርመን መግባት የሚያስችላቸው ቪዛ ለማግኘት ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ለመሄድ የሚነሱ ጀርመን ተገን የሰጠቻቸው ኤርትራውያን ስደተኞች ቤተሰቦች ህይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው ነው ጉዞ የሚጀምሩት። በዚህ ጉዞም ለሰው አሻጋሪ ደላሎች ጠቀም ያለ ገንዘብ መክፈል አለባቸው። ሦስት ሺህ ዩሮ እና ከዚያም በላይ የቤተሰብ አባላቱ ቁጥር ከፍተኛ ከሆነ ደግሞ እስከ 5 ሺህ ዶላር ሊጠየቁም ይችላሉ። በዚህ ጉዞ ኤርትራውያኑ ሁለት ድንበሮች መሻገር ይኖርባቸዋል። የኤርትራን ከዚያም የኢትዮጵያን ድንበር። መረብ ወንዝን መሻገር የሚያስፈልገው ይህን መሰሉ ጉዞ ህይወት ሊያሳጣ የሚችል እጅግ አደገኛ አማራጭ ነው እንደ ኤርትራዊው ስደተኛ። በዚህ ጉዞ ህጻናት ልጆችን ጭምር ይዘው የሚጓዙ ሰዎች በኤርትራ ድንበር ጠባቂዎች ከተያዙ መጨረሻቸው እሥር ቤት መወርወር ነው የሚሆነው። በወታደሮች ተተኩሶባቸው ሊገደሉም ይችላሉ። ከዚህ አምልጠው ኢትዮጵያ መግባት የቻሉት ኤርትራውያን በስደተኝነት ተመዝግበው ከ3 ወር በኋላ እንደ ልብ መንቀሳቀ የሚያስችላቸው መታወቂያ እንደሚሰጣቸው ስደተኛው ከራሱ ተሞክሮ በመነሳት ተናግሯል። የስደተኞቹ ቤተሰቦች ውጣ ውረድ በዚህ ብቻ አያበቃም በጎረቤት አገራት ኤምባሲዎችም መጉላላት ይደርስባቸዋል። የቀጠሮ መራዘም ሰነዶች አልተሟሉም መባል እና ሌሎችም ችግሮች ሊገጥሙዋቸው ይችላሉ። ቤተሰቦቻቸውን የማምጣት ጥያቄአቸው መልስ ሳይሰጠው የሚዘገይባቸው አጋጣሚዎች አሉ።

Äthiopien Flüchtlinge aus Eritrea in Tigray
ምስል DW/J. Jeffery

ምንም እንኳን ጀርመን ከጎርጎሮሳዊው 2015 እስከ ህዳር 2017 ድረስ 35,535 ኤርትራውያን ስደተኞችን ብትቀበልም ቤተሰቦቻቸውን ወደ ጀርመን የማምጣት ጥያቄአቸው ተቀባይነት ያገኘው ጥቂት ናቸው።  ስደተኞች ቤተሰቦቻቸው ጀርመን እንዲመጡላቸው  ባለፈው ዓመት ካስገቧቸው ማመልከቻዎች ውስጥ  808 ቱ ታይተዋል። ሆኖም ከመካከላቸው ይሁንታ ያገኙት 394ቱ ወይም ደግሞ 48.8 በመቶው ብቻ መሆናቸውን የጀርመን ምክር ቤት ከግራዎቹ ፓርቲ ለቀረበለት ጥያቄ በሰጠውና ገና በይፋ ባልወጣ መልስ አስታውቋል። ወደ ጀርመን ለመምጣት በጎረቤት ሀገራት ቪዛ የሚጠይቁ የኤርትራውያን ስደተኞች ቤተሰቦች በህጉ መሠረት ፓስፖርት ሊኖራቸው ይገባል። የትዳር አጋሮች ደግሞ የጋብቻውን ህጋዊነት የሚያረጋግጥ ማስረጃም ይጠየቃሉ፤ ጋብቻው በኤርትራ በይፋ መመዝገቡን ማረጋገጥ መቻል አለባቸው። የግራዎቹ ፓርቲ አባል ወይዘሮ ኡላ የልፕከ እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ምክንያታዊ አይደሉም ሲሉ ይከራከራሉ።

« የፌደራል ጀርመን መንግሥት ፣ሰዉ እነዚህን ሰነዶች ከወታደራዊ አምባገነን ወይም ከአምባገነኖቹ ባለሥልጣናት ያገኛሉ ብሎ ይጠበቃል። ይህ ግን የሚቻል አይደለም። በመሠረቱ ሰዉ ወደ ዚያ ለመሄድም ሆነ ዘመዶቹን እነርሱ ጋ ለመላክ ከፍተኛ ፍርሀት አለበት። ከሄዱም፣የሚሄደውን ሰው  ተጠያቂ የሚያደርግ ወንጀል ፈጽሜያለሁ የሚል እና ወደ ሀገራቸው በተመለሱ ጊዜ ሊያስጠይቃቸው የሚችል ሰነድ እንዲፈርሙ ይገደዳሉ። የጀርመን መንግሥት በእንዲህ ዓይነቱ አጠያያቂ ነገር ውስጥ  ራሱን ማስገባቱ አሳፋሪ ነው። »

Bildergalerie Flüchtlingscamp Tigray in Äthiopien SCHLECHTE QUALITÄT
ምስል Milena Belloni

የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዚህ ጉዳይ ከግራዎቹ ፓርቲ በኩል ለቀረበለት ጥያቄ በሰጠው መልስ  በአዲስ አበባው የጀርመን ኤምባሲ ፓስፖርት ይዞ መቅረብ ግዴታ አይደለም። የጋብቻ ማስረጃ ግን በቀላሉ ማግኘት እንደሚቻል አስታውቋል። ይሁን እና የጀርመን ፌደራል መንግሥት ቪዛ ማግኘት ምን ያህል ጊዜ እንደሚወስድ በትክክል ከመግለጽ  ተቆጥቧል። ለዚህ በሰጠው መልስ «ቪዛ እስከሚሰጥ የሚወስደውን ጊዜ ለማወቅ አይቻልም የሚል ነው ያለው። የልፕከ ይህንንም ተችተዋል።

«የፌደራል ጀርመን መንግሥት የፖሊሲ አፈጻጸምን በተለይም ቢሮክራሲያዊ አሠራርን የሚመለከቱ መመሪያዎችን ያወጣል። ሆኖም ስለነዚህ ጉዳዮች ምንም ዓይነት መረጃ አይሰጥም። የሚይዙት መረጃ ከ6 ወር በኋላ ይሰረዛል። ግን ምንም የሚቀይረው ነገር የለም። ሰዎቹ ምን ያህል ጊዜ እንደጠበቁ ግን መረጃ መያዝ አለባቸው። የሚገርመኝ ነገር 3 ከተሞች ውስጥ ይህን ስራ ሊሰሩ የሚችሉ እፍኝ እንኳን የማይሞሉ ሰዎች አለመኖራቸው ነው።»

መንግሥት የግራዎቹ ፓርቲ ላቀረባቸው ጥያቄዎች በሰጠው መልስ ቤተሰቦችን ወደ ጀርመን ለማምጣት በርካታ ማመልከቻዎች በቀረቡበት ባለፈው ዓመት አዲስ አበባ በሚገኘው የጀርመን በኤምባሲ በኩል ቀጠሮ የመስጠት ችግር ነበር ሲል ገልጿል። ከ20 ብዙም የማይበልጡ ሠራተኞች ብቻ የቪዛ ጉዳይ እንደሚከታተሉ እና እነርሱም የኤርትራውያን ስደተኞች ቤተሰቦችን ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ማመልከቻዎች የሚያዩ መሆናቸውን አስታውቋል።

ዶቼቬለ ያነጋገረው ጀርመን የሚገኝ ኤርትራዊ ስደተኛ ቤተሰቦቹን የማምጣት መብት ቢኖረውም ቤተሰቡ ፣ እነዚህ በመሳሰሉ ውስብስብ ውጣ ውረዶች ውስጥ እንዳይወድቅ እና ህይወታቸውንም ለአደጋ ላለማጋለጥ ሲል ባሉበት መቆየታቸውን መርጫለሁ ብሏል። እዚህ ውሳኔ ላይ ያደረሰውም ከአንድ ዓመት በፊት የወንድሙ ሚስት 2 ልጆቿን ይዛ የሱዳንን ድንበር ለመሻገር ስትሞክር ህይወትዋ በማለፉ ነው። ሆኖም እርሱ እንደሚለው ኤርትራ ያሉ የስደተኞች ቤተሰቦች ግን ጀርመን ለመምጣት ካላቸው ጉጉት የተነሳ ይህን መሰሉን ስጋት መስማት አይፈልጉም። ርሱ ግን ህይወት ከሚጠፋ በሥጋ ተለያይቶ በመንፈስ አንድ ሆኖ መኖርን በአጭሩ «ከመሞት መሰንበት» በሚለው አቋሙ ጸንቷል።  

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ